የሩሲያ ኤምባሲ አዲስ አበባ የተረጋጋች በመሆኗ ሠራተኞቼን የማስወጣት ዕቅድ የለኝም አለ

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa City Press Secretary/FB
በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በከተማዋ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ በመሆኑ ሠራተኞቹንና ቤተሰቦቻቸውን የማስወጣት ዕቅድ እንደሌለው አስታወቀ።
የኤምባሲው ፕሬስ አገልግሎት በይፋዊ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ በኩል ባሰራጨው መግለጫው እንዳለው በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን አመልክቶ የተለመደ ሥራው እንደቀጠለ ገልጿል።
በመላው አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ ባለው የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ለውጥ እንዳልታየ አመልክቷል።
ኤምባሲው ጨምሮም በከተማዋ ውስጥ ባሉ የመንግሥት ህንጻዎች፣ የአየር ማረፊያና በመሳሰሉት ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት አካባቢ የተጠናከረ የደኅንነት ጥበቃ እንዲሁም በጎዳናዎች ላይ ቅኝት እንደሚደረግ ጠቅሷል።
የአዲስ አበባው ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተለመደ ሥራውን እያከናወነ መሆኑንና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በቅርቡ እንዳለው በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ በረራዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑንም ኤምባሲው አስታውሷል።
ስለዚህም በአዲስ አበባ ያለው የሩሲያ ፌዴሬሽን ኤምባሲም የተለመደ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ገልጾ፣ በኤምባሲው ውስጥ የሚያገለግሉ ሠራተኞችንም ሆነ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ከአገሪቱ እንዲወጡ ለማድረግ እንዳላቀደ አመልክቷል።
ነገር ግን ለአስቸኳይ ጉዳይ አስፈላጊ ሆኖ አስካላገኙት ድረስ የሩሲያ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
በሰሜን ኢትዮጵያ እተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ በመጣበት ባለፉት ሳምንታት በርካታ የምዕራብ አገራት ዜጎቻቸውና ዲፕሎማቶቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን፣ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ተመሳሳይ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑ ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባለፈው ማክሰኞ ተቀማጭነታቸውን በከተማዋ ላደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዲፕሎማቶች በአገሪቱ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ በከተማዋና ዙሪያዋ አስተማማኝ ሰላም እንዳለ ገልጸው፤ ለዚህም የከተማው የፀጥታ ኃይል ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከሪፐብሊካን ዘብ፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ እና ከሌሎች የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል።















