በስዊድን የመጀመርያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር በተመረጡ በሰዓታት ውስጥ ሥልጣን ለቀቁ

ማግዳሊና አንደርሰን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በስዊድን ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ለቀቁ፡፡

ማግዳሊና አንደርሰን ሥልጣን የለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ በሰዓታት ውስጥ ነው፡፡

ትናንትና ረቡዕ መሪ ሆነው መመረጣቸው ይፋ ከሆነ ከሰዓት በኋላ ነው አንደርሰን የለቀቁት፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ከርሳቸው ፓርቲ ጋር ጥምረት የፈጠረው የፖለቲካ ድርጅት ከጥምረቱ በመልቀቁና የሳቸው ፓርቲ ሶሻል ዲሞክራት ያቀረበው የበጀት ጥያቄ በምክር ቤቱ ሊያልፍ ባለመቻሉ ነው፡፡

ከዚያ ይልቅ ምክር ቤቱ፣ የቀኝ አክራሪ ጸረ- ስደተኛ አቋም ያለው ፓርቲ ያቀረበው በጀት ላይ ድምጽ ሰጥቷል፡፡

‹‹በዚህ ጊዜ ለአፈጉባኤው ሥልጣን ብለቅ እመኛለሁ ብዬ ነገርኩት›› ብለዋል አንደርሰን ለጋዜጠኞች፡፡

ከርሳቸው ፓርቲ ጋር ጥምረት የፈጠረው ግሪንስ ፓርቲ ‹‹በቀኝ አክራሪዎች የቀረበን በጀት አልቀበልም ሲል ነበር ከጥምረቱ የለቀቀው፡፡

አንደርሰን በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል እንደማይፈልጉና የገዛ ፓርቲያቸው በአብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግሥት ሲመሰርት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጥ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ አካሄድ የጥምር መንግሥት ከተመሠረተና አንድ ፓርቲ ከጥምረቱ ከወጣ መንግሥት ሥልጣን ይለቃል፤ በእንዲህ ሁኔታ ቅቡልነቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መንግሥትን መምራት ደግሞ አልፈልግም›› ብለዋል አንደርሰን፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አንደርሰን ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ የፓርቲ መሪዎችን እንደሚያነጋግሩ ይጠበቃል፡፡

አንደርሰን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስዊድንን እንዲመሩ ድምጽ ያገኙት ትናንትና ነበር፡፡

በስዊድን ሕግ አብዛኛዎቹ የተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴዎች በተቃውሞ ድምጽ ካልሰጡ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ያደርጋል፡፡

ሪክስዳግ የሚባለው የስዊድን ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 349 አባላት አሉት፡፡

ከነዚህ ውስጥ አንደርሰንን የተቃወሙት 174ቱ ናቸው፡፡ ይሁንና 117ቱ ድምጽ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ከዚህ አንጻር እንዴት ተመረጡ ሊያስብል ቢችልም 57ቱ ድምጽ ተአቅቦ ማድረጋቸው በስዊድን ሕገ መንግሥት ከምክር ቤት አባላት በድምሩ ብዙ ተወካይ ባይመርጣቸውም ስላልተቃወማቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡

አንደርሰን በዚህ የተነሳ አንድ ተጨማሪ ድምጽ አግኝተው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት፡፡

በስዊድን ሴቶች ድምጽ መስጠት ከጀመሩ ከመቶ ዓመታት በኋላ የ54 ዓመት ሴት አንደርሰን ሶሻል ዲሞክራትን በመምራት ጠቅላይ ሚኒስትር መሆናቸው ሲበሰር የምክር ቤቱ አባላት ቆመው ነበር ያጨበጨቡላቸው፡፡

በዩኒቨርስቲ ሲቲ ኡፕሳላ የአዳጊዎች የውሃ ዋና ሻምፒዮን የነበሩት አንደርሰን ፖለቲካ ውስጥ የገቡት በ1996 የጠቅላይ ሚኒስትር ጎራን ፐርሰን አማካሪ በመሆን ነበር፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት ደግሞ በገንዘብ ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡

ማግደሊና አንደርሰን በሕዝብ እንደራሴዎች ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ድምጽ ከማግኘታቸው በፊት ስዊድን ከኖርዲክ አገሮች ሁሉ ብቸኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ኖሯት የማያውቅ አገር ሆና ቆይታለች፡፡

ስዊድን የጾታ እኩልነት ከፍ ባለ ደረጃ የምታከብር ብልጹግ አገር ናት፡፡