የጋዳፊ ልጅ ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ታገዱ

የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ ጋዳፊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ ጋዳፊ ከሳምንታት በኋላ በሀገሪቱ ከሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውድድር ውጪ ሆነዋል።

የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊን ጨምሮ በርካታ እጩዎችን "በህጋዊ ምክንያቶች" በምርጫው እንዳይሳተፉ እንዳገደ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

አል ኢስላም ጋዳፊን አባቱ የሰሜናዊቷን አፍሪካዊ ሀገር ሊቢያን በሚያስተዳደሩበት ወቅት በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጦር ወንጀል እና በነፍስ ግድያ የሚፈለግ ሰው ነበር።

በዚህም ሳቢያ የጋዳፊ ልጅ ለፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደሩ ከተሰማ በኋላ ውዝግብ አስነስቷል።

በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስ የቀረበባቸው ዝነኛው ካሊፍ ሃፍታር ለምርጫ ለመወዳደር መዘጋጃታቸው በሀገሪቱ ውስጥ ውዥንብር ፈጥሯል።

ነገር ግን ምርጫ ኮሚሽኑ ከፕሬዝዳንታዊው ምርጫ ያድርጋቸው አይድርጋቸው የታወቀ ነገር የለም።

የሊቢያ ወታደራዊ አቃብያነ ህግ የጋዳፊ ልጅ እና የሃፍታር በቀረበባቸው ክስ ላይ ተገቢ መልስ እስኪያቀርቡ ድረስ የምርጫ ኮሚሽኑን በእጩነት ለማሳተፍ የሚያደርገውን ሂደት እንዲያቆም ጠይቀው ነበር።

ሰኞ በተጠናቀቀው የእጩዎች ምዝገባ ስልሳ ሰዎች ሊቢያን በፕሬዝዳንት ለመምራት የተመዘገቡ ሲሆን የ46 ዓመቷ የሴቶች መብት ተሟጋች ሊላ ቤን ካሊፋ ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ናቸው።