ማላዊ ማይክ ታይሰን የዕፀ-ፋርስ አምባሳደር እንዲሆናት ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማላዊ፤ እውቁ ተቧቃሽ ማይክ ታይሰን የሃገሪቱ ኦፊሴላዊ የዕፀ-ፋርስ አምባሳደር እንዲሆን ጠየቀች።
የግብርና ሚኒስትሩ ሎቢን ሎው ማይክ ታይሰን የዕፀ ፋርስ ወይንም ካናቢስ አምባሳደር እንዲሆን በግልፅ ደብዳቤ ጠይቀዋል።
ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ማላዊ ካናቢስን ሕጋዊ ማድረጓ አዲስ ዕድል ከፍቷል ብለዋል።
የቀድመው የዓለም ከባድ ሚዛን ቡጢ ሻምፒዮን ማይክ ታይሰን አሜሪካ ውስጥ ካናቢስ አምርቶ የሚሸጥ ድርጅት አለው።
የማላዊ ድርጊት ያላስደሰታቸው ሰዎች እንዴት በ1990ዎቹ የወሲብ ጥቃት ሰንዝሮ ለተፈረደበት ሰው አምባሳደርነት ይሰጣል ሲሉ ተችተዋል።
"ማላዊ ብቻዋን ልታደርገው ይከብዳት ይሆናል። ምክንያቱም ኢንዱስትሪው ትብብር የሚሻ ነው። ለዚህ ነው አቶ ማይክ ታይሰን የማላዊ ካናቢስ ቅርንጫፍ አምባሳደር እንድትሆን የምጠይቅህ" ይላል የሚኒስትሩ ደብዳቤ።
የዩናይትድ ስቴትስ ካናቢስ ማሕበር ማይክ ታይሰን አምባሳደር እንዲሆን ሁኔታዎችን እያመቻቸ እንደሆነ የግብርና ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
የማሕበሩ የማላዊ ቅርንጫ ኃላፊ ዌዚ ጋላሚላ የቀድሞው ቦክሰኛ ታይሰን ጥሪውን ተቀብሏል፤ በቅርቡም ማላዊን ሊገበኝ ይችላል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ታይሰን ከኛ ጋር የሚሠራበት ጊዜ ቅርብ ነው" ብለዋል ኃላፊዋ።
ማላዊ የዕፀ ፋርስ ቅጠልን አሳድጎ ለሕክምና እንዲውል ማድረግ ይቻላል ስትል ፈቃድ የሰጠችው ባለፈው ዓመት ነበር።
ነገር ግን ማላዊያን ካናቢስን ለግል ጥቅማቸው ማዋል አሊያም ጠቅልለው ማጨስ እስካሁን አልተፈቀደላቸውም።
የማላዊ ግብርና ሚኒስቴር ገበሬዎች ካናቢስን አምርተው ለሕክምና አገልግሎት እንዲያውሉ ያበረታታል።
የሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ግራሲያን ሉንጉ ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል ሲናገሩ ታይሰን ፈቃደኛነቱን ይፋ ካደረገ "ሌሎች ኢንቨስተሮችን ሊስብ ይችላል።"
ማላዊ ውስጥ የሚመረተው በቅፅል ስሙ ማላዊ ጎልድ የተሰኘው ካናቢስ ቅጠሉን ጠቅልለው በሚያጨሱ ተጠቃሚዎች ዘንድ ዝናው የናኘ ነው።
ታይሰን ዕፀ ፋርስ ማጨሱ የአእምሮ ጤናው ሰላም እንዲመለስ እንዲሁም ሕይወቱ እንዲቃና እንደረዳ ይናገራል። ነገር ግን አንዳንድ ጥናቶች ዕፀ ፋርስ መጠቀም ለአእምሮ ጤና አደጋ ሊሆን እንደሚችል ያሳያሉ።
ሴንተር ፎር ፐብሊክ አካውንቴቢሊቲ የተሰኘው የማላዊ ሲቪል ማሕበር የመንግሥትን ድርጊት ተቃውሟል።
ማሕበሩ የታይሰን የኋላ ታሪክ አመፀኝነት ለሚስተዋልበት መንግሥት የመረጠው ሰው ትክክለኛ አይደለም ሲል ይሞግታል።
የቀድሞው ሞገደኛ ቦክሰኛ ማይክ ታይሰን በፈረንጆቹ 1992 ኢኒዲያና ውስጥ የመድፈር ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ ታስሮ ነበር። ነገር ግን ከሶስት ዓመት በኋላ ከእሥር ተለቋል።












