የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ጠንሳሿ መስከረም ታደሰ

መስከረም ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, Meskerem Tadesse

የምስሉ መግለጫ, መስከረም ታደሰ

ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ቶታልኤነርጂስ ካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ከሁለት ሳምንታት በፊት በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ተጀምሯል። ፍፃሜው ደግሞ ዛሬ አርብ ኅዳር 10/2014 ዓ.ም ይሆናል።

የቶታልኤነርጂስ ካፍ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን 32 የአፍሪካ ክለቦች ቀጣናዊ የማጣሪያ ውድድር አድርገው ነበር። ይህንን ቀጣናዊ ውድድር ያሸነፉ ስምንት የአፍሪካ የሴቶች እግር ኳስ ክለቦች በዚህ ታሪካዊ ውድድር ላይ ተሳትፈዋል።

የማሊ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሞሮኮና አስተናጋጇ ግብፅ ክለቦች በዚህ የ15 ቀናት ውድድር ላይ ተፋልመው የመጨረሻዎቹ ሁለቱ ተለይተዋል።

ያለፈው ዓመት የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ አሸናፊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ኬንያ አቅንታ የማጣሪያ ውድድር ማድረጓ አይዘነጋም።

ታድያ በዚህ ታሪካዊ ውድድር ኢትዮጵያን ለመወከል ከጫፍ ደርሳ የነበረችው ንግድ ባንክ በማጣሪያው የፍፃሜ ጨዋታ በኬንያዋ ኢሂጋ ኩዊንስ ተሸንፋ መውደቋ ይታወሳል።

ምንም እንኳን ንግድ ባንክ በዚህ ውድድር ላይ አገሯን መወከል ባትችልም ዋና ዳኛ ሊድያ ታፈሰ ወደ ግብፅ በማቅናት ኢትዮጵያን ወክላለች። የፍፃሜውን ጨዋታ እንደምትዳኝም ይጠበቃል።

ለመሆኑ አፍሪካ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እንታዘጋጅ ካደረጉት መካከል አንዷ የሆነችው መስከረም ታደሰ ማናት?

መስከረማ ታደሰ ጎሽሜ

"ያው ፈረንጆቹ በአያቴ ስም ጎሽሜ ብለው ነው የሚጠሩኝ [ፈገግታ. . .] ተወልጄ ያደግኩት ደግሞ አዲስ አበባ ነው። ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የኳስ ፍቅር ያደረብኝ።"

ኢትዮጵያዊቷ መስከረም ታደሰ ጎሽሜ ይህን ታሪካዊ ውድድር ደፋ ቀና ብለው ካዘጋጁ የአፍሪካ እግር ኳስ አስተዳዳሪ [ካፍ] ሰዎች መካከል አንዷ ናት።

የመጀመሪያ ድግሪዋን በስፖርት ሳይንስ ይዛለች። ሁለተኛ ድግሪዋን ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእግር ኳስ ትምህርት አግኝታለች። በወቅቱ ብቸኛዋ በእግር ኳስ የማስተርስ ድግሪዋን የሠራች ሴት እንደነበረች መስከረም ታወሳለች።

ከዚያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ልማት ኃላፊ ሆና ተቀጠረች። እሷ ይህንን ክፍል በምትመራበት ወቅት የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፋለች። የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ተጠንስሷል። አልፎም እነ ሎዛ አበራን የመሳሰሉ ከዋክብት የፈለቁበት የሉሲ ማቀጣጠያ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

መስከረም ቀጥላ ያመራችው ወደ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ነበር። የስፖርት ሳይንስና የስፖርት ማኔጅመንት ትምህርቶችን ከማስተማር ባለፈ የዩኒቨርሲቲው የሴቶች ቡድን አሠልጣኝም ነበረች።

ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በመቀጠል መስከረም ፊቷን ወደትምህርት መልሳ የፊፋ ማስተርስ ፕሮግራምን ወሰደች።

በፊፋ ስፖርንሰርነት ሴንተር ፎር ስፖርት ስተዲስ በተሰኘ ተቋም የሚሰጠው ይህ የማስተርስ ድግሪ ፕሮግራም በእንግሊዟ ሌስተር፣ በስዊትዘርላንድ፣ በጣልያኗ ሚላን በሚገኙ ሦስት የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጥ ነው።

መስከረም ይህንን የማስተርስ ፕሮግራም ካጠናቀቀች በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ እንዲሁም በአንድ ወቅት ጊዜያዊ ዋና ፀሐፊ ሆና አገልግላለች።

መስከረም ቀጥላ ወደ አፍሪካ እግር ኳስ የበላይ ወደሆነው ካፍ አመራች። አሁን በካፍ የሴቶች ቢሮ ነባር ማኔጀር በመሆን በማገልገል ላይ ትገኛለች።

መስከረም ታደሰ

የፎቶው ባለመብት, Meskerem Tadesse

የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ እንዴት ተጠነሰሰ?

"የፌዴሬሽኑ ፀሐፊ በነበርኩበት ወቅት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ቻምፒዮን ደደቢት ነበረች። ኃላፊዎች መጥተው ቻምፒዮን እንደመሆናችን አፍሪካ ውድድሮች ላይ አንሳተፍም ወይ ብለው ጠይቁን" ትላለች መስከረም።

"የአፍሪካ ውድድር የለም እኮ ስንላቸው በጣም ነው የገረማቸው። ነገር ግን ይህንን ጉዳይ በጣም ብዙ ጊዜ ለካፍ እናነሳ ነበር።"

በአፍሪካ ሴቶች የሚሳተፉበት ብቸኛው አህጉራዊ ውድድር የአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ብቻ ነበር ትላለች መስከረም።

"እኔ ካፍን የተቀላቀልኩት በፈረንጆቹ ኅዳር 2018 ነበር። ከዚያ በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል በአፍሪካ አገራት እየተዟዟርን የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስን ለመረዳት ጥረት ስናደርግ ነበር። ምን ያስፈልገዋል? ከምን ተነስተን ነው ወደፊት የምንሄደው? ምክንያቱም ስትራቴጂ መንደፍ እንዳለብን አውቀናል።"

እነ መስከረም በየአገራቱ ተዟዙረው ከተጫዋቾች፣ ከአሠልጣኞች፣ ከፌዴሬሽኖች እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር መክረውና ዘክረው ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚመራ ስትራቴጂ ነደፉ።

መስከረምና የሥራ ባልደረቦቿ ማከናወን ከሻቷቸው ተግባራት መካከል አህጉራዊ የሆነ የክለቦች ውድድር ማዘጋጀት አንዱ ነበር።

"ይህን ማድረግ የፈለግነው እያንዳንዱ አገር በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ ከፈለገ የሴቶች ሊግ ጠንክሮ መሥራት እንዳለበት ስለምናውቅ ነው" ትላለች መስከረም።

"38 የአፍሪካ አገራት የሴቶች ፕሪሚዬር ሊግ ውድድር እንዳላቸው ካረጋገጥን በኋላ ነው የመጀመሪያውን የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ለማዘጋጀት ዝግጁ እንደሆንን የተረዳነው።"

የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ዓላማ

"ዋናው ዓላማችን የሴቶች እግር ኳስ ውድድርን ወደፊት ማምጣት ነው። ሌላኛው ደግሞ ለሴቶች ዕድል መክፈት ነው። ከዚህ በፊት ብሔራዊ ቡድናቸውን መወከል ያልቻሉ ተጫዋቾች በፕሮፌሽናል ደረጃ ለመጫወት ዕድሉን አያገኙም ነበር። ተጫዋቾችን የሚታዩበት አንደኛው መድረክ ነው ይህ ቻምፒዮንስ ሊግ።"

መስከረም አክላ ይህ ውድድር ተጫዋቾች አገራቸውንም የሚወክሉበት መልካም አጋጣሚ ነው ትላለች።

ለአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ለማለፍ ክለቦች ቅድሚያ ቀጣናዊ ውድድር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ማድረግ ያስፈለገው አብዛኞቹ ክለቦች ከአንድ አገር ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ የሚጫወቱበት አቅም ስሌላቸው እንደሆነ መስከረም ታስረዳለች።

"ለምሳሌ ንግድ ባንክን አንዴ ታንዛኒያ አንዴ ኬንያ ለመላክ አቅም አይፈቅድም። አብዛኞቹ ክለቦች ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅም የላቸውም። ለዚህ ነው በየቀጣናው አድርገን አሸናፊዎች ወደ ቻምፒዮን ሊግ እንዲያልፉ ያደረግነው።"

መስከረም ወደፊት ውድድሩ እየጠነከረ ሲመጣ የተለያዩ ስፖንሰሮችን ማግኘት፣ እንዲሁም ከጨዋታ አስተላላፊዎች ጋር ውል መግባት [ብሮድካስቲንግ ራይትስ] ዓላማቸው እንደሆነ ትናገራለች።

አልፎም የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር በመጨመር ውድድሩ በአፍሪካ ካሉ ትላልቅ የእግር ኳስ ፍልሚያዎች አንዱ የማድረግ የካፍ ዓላማ እንደሆነ ትናገራለች።

መስከረም የአፍሪካ ሴቶች እግር ኳስ ከወንዶቹ ቀድሞ ዓለም አቀፍ ስኬት እንደሚለባስ እምነት አላት።

"እኔ የሚታየኝ አፍሪካ ከወንዶች በፊት በሴቶች የዓለም ዋንጫን እንደምታነሳ ነው። ነገር ግን ይህ እንዲሆን ድጋፍ ያስፈልገናል። ስፖንሰርሺፕ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሴቶች ያላቸውን ተሰጥዖ እያየነው ነውና።"

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ

የኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ቡድኖች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀጣናዊ ውድድሮች አመርቂ የሚባል ድል እያስመዘገቡ ነው።

በታሪካዊው የመጀመሪያው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ የተወዳደረችው ንግድ ባንክ እስከፍፃሜው ደርሳ በኬንያዋ ኢሂጋ ኩዊንስ ተሸንፋ ሳይካሳላት መቅረቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውድድር ላይ የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በፍፃሜው ውድድር በ10 ተጫዋቾች ከ2 ለምንም መመራት ተነስታ ዋንጫ ማንሳቷም አይዘነጋም።

ቢሆንም አሁንም የሴቶች እግር ኳስ የሚገባውን ያህል አድጓል ማለት የሚያስደፍር እንዳልሆነ ብዙዎች ይስስማሉ።

መስከረም ይህ ችግር አገራዊ ወይም አህጉራዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ነው ትላለች።

"በሜዳ ላይ የሚታየው ብቃት እያደገ ነው። የሚሰጠውም ትኩረት በተነፃፃሪ እያደገ ነው። ነገር ግን እኩል ትኩረት እየተሰጠው ነው ማለት አንችልም። ከሴቶች ይልቅ አሁንም ብዙ 'ኢንቨስትመንቶች'፤ ብዙ ስፖንሰሮች የሚሄዱት ወደ ወንዶች ውድድር ነው።"

"ነገር ግን በየቀጣናው ውድድሮች ሲኖሩ የማንሳተፍ ከሆነ፤ የወዳጅነት ውድድሮች ከሌሎች አገራት ጋር የማናደርግ ከሆነ ልናድግ አንችልም። ምክንያቱም እግር ኳስን የሚያሳድገው ውድድር ነው። ስለዚህ ይህ እስኪሳካ ድረስ መሥራት አለብን ብዬ ነው የማስበው" ትላለች መስከረም ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ስታወራ።

ኢትዮጵያ ዓመታዊውን የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ወደፊት ታዘጋጅ ይሆን ወይ?

"ሕምምም. . . አሁን ባለንበት ሁኔታ እንደምታውቀው የኛ ስታዲዬሞች ዓለም አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት ዝግጁ አይደሉም። ነገር ግን ወደፊት ከማዘጋጀት ምንም የሚያግደን ነገር ያለ አይመስለኝም። ፌዴሬሽኑና የስፖርት ሚኒስቴር ጠንክረው ከሠሩበት ሊሳካ ይችላል።"

ቢሆንም ትላለች መስከረም "ቢሆንም እግር ኳስ ውድድር ማዘጋጀት የፌዴሬሽን ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል። አገር ናት የምታዘጋጀው። ይህ ማለት ፌዴሬሽኑም ሆነ የስፖርት ሚኒሰቴር እንዲሁም ሁሉም የሚሳተፉበት ነው መሆን ያለበት። ቪዛ ለማዘጋጀት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስፈልጋል። ፋይናንሱን ለማቀላጠፍ የገንዘብ ሚኒስቴር መሳተፍ አለበት። ባሕላዊ እሴቶቻችንን ለማሳየት የባሕል ሚኒስቴር ሚና ወሳኝ። ለዚህ ነው ፌዴሬሽኑ ሳይሆን አገር ናት ውድድሩን የምትረከበው የምለው" ትላለች።

ከበፊት አሊያም ከአሁን የምታደንቂያት እግር ኳስ ተጫዋች?

"ከበፊቶቹ የማደንቃት ብርቱካን ገብረክርስቶስን ነው። አሁን ከሚታዩት ደግሞ ሎዛን [ሎዛ አበራ]። እኔ ሎዛን ሳውቃት ገና የ14 ዓመት ታዳጊ ነበረች። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ራሷን እያስተዋወቀች ያለች ናት።"

የወደፊት ዕቅድሽ?

"የምሠራቸው ሥራዎች የሌሎች ሰዎችን ሕይወት ሲቀይሩ ማየት ያስደስተኛል። ማስተማር እወድ የነበረው ለዚህ ነው። የወደፊት ምኞቴ እኔ የምመራው እግር ኳስ ክለብ ኖሮኝ ተጫዋቾችን ማፍራት፤ ማሳደግ ነው። ሌላው ሐሳቤ አገሬን በተለያዩ መንገዶች መርዳት ነው።"

"ሰው ወደፊፋ መሄድ ነው ይላል እኔ ግን ወደ አገሬ ተመልሼ የአንድ ወጣት ሕይወትን መቀየር ከቻልኩ ትልቅ ሥራ ነው ብዬ አስባለሁ።"

በመጀመሪያው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ የደረሱት የደቡብ አፍሪካ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና የጋና ሐሳካስ ሌዲስ

የፎቶው ባለመብት, CAF

የምስሉ መግለጫ, በመጀመሪያው የአፍሪካ የሴቶች ቻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ የደረሱት የደቡብ አፍሪካ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና የጋና ሐሳካስ ሌዲስ