በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ የኮኬይን ናሙናዎች ተገኝተዋል መባሉ አነጋጋሪ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም ፓርላማ ውስጥ አደገኛ ዕጽ ተጠቃሚዎች ካሉ በሚል ፍተሻ ሊደረግ ነው።
የፓርላማው፣ (ሐውስ ኦፍ ኮመን) አፈ ጉባኤ ሰር ሊንዚ ሆይል በጉዳዩ ላይ ፖሊስ ምርመራ እንዲያደርግ እንደሚተባበሩ አስታውቀዋል።
አፈ ጉባኤው ይህን ያሉት በፓርላማው መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ የኮኬይን ናሙናዎች መገኘታቸውን በሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ መዘገቡን ተከትሎ ነው።
አፈ ጉባኤው "ዘገባው ይዞ የወጣው ጉዳይ እጅግ አሳስቦናል" ብለዋል። ከከተማው ፖሊስ ጋር በጉዳዩ ላይ አብሮ ለመሥራትም ያላቸውን ዝግጁነት ገልጠዋል።
ሰር ሊንዜ ሆይል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሕግን እያወቁ የጣሱ ቅጣት ይገባቸዋል።
ይህ ጉዳይ የተነሳው ዛሬ ሰኞ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት ከአደገኛ ዕጽ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚውል የ700 ሚሊዮን ፓውንድ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ዕለት ነው።
ይህ ገንዘብ በሱስ የተያዙ ሰዎች ሊያገግሙ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የሚያበረታታ ነው።
ሰንደይ ታይምስ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት ከፓርላማው 12 መጸዳጃ ቤቶች በ11ዱ ላይ የኮኬይን ናሙና እንደተገኘ አስነብቧል።
ይህን ተከትሎም ዌስትምኒስተርን የሚያስተዳድረው የሐውስ ኦፍ ኮመንስ ኮሚሽን ከከተማው ፖሊስ ጋር በመተባበር አነፍናፊ ውሾች ወደ ቅጥር ግቢው እንዲገቡ ለማድረግ እቅድ ይዟል።
አፈ ጉባኤ ሰር ሊንዚ በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ሰንደይ ታይምስ ያወጣው ዘገባ አሳሳቢ ነው ካሉ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት ከከተማው ፖሊስ ጋር በሚኖረኝ ቆይታ ጉዳዩ በዋናነት የማነሳው ይሆናል ብለዋል።
አክለውም፣ ፓርላማው ለእንደራሴዎችም ሆነ ለፓርላማው ሠራተኞች ከአደገኛ ዕጽ ሱስ ጋር በተያያዘ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሚያደርግ ቢሆንም ድጋፉ የሚደረገው ግን ሱሰኛ እንደሆኑ ራሳቸውን ላጋለጡ ዜጎች ነው። አደገኛ ዕጽ በመጠቀም ሕግን በሚጥሱ ላይ ግን አይቀጡ ቅጣት ይጣላል ብለዋል።
በዩኬ ኮኬይንን የመሰሉ ደረጃ አንድ ላይ የሚቀመጡ የአደገኛ ዕጾችን የተገኘባቸው ግለሰቦች እስከ ሰባት ዓመታት እሰር ይጠብቃቸዋል። ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣትም ይቀጣሉ። አደገኛ ዕጽ አቅራቢዎች ደግሞ እስከ እድሜ ልክ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ባደረገው ጥናት ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 59 ካሉ 11 ግለሰቦች መካከል አንዱ አደገኛ እጽ ተጠቃሚ ነው።












