ከወለድ ነጻ ባንክ ሥርዓት ለሚሰጠው 'ብድር' እንዴት ትርፍ ያገኛል?

የፎቶው ባለመብት, Hijra Bank/Zamzam Bank
የሼሪያ ሕግን መሰረት አድርጎ ሥራውን የሚያከናውነው እስላማዊ ወይም ከወለድ ነጻ የባንክ ሥርዓት ገንዘብ ሰጥቶ፣ አትርፎ መቀበልን ያወግዛል።
ይህም በባንኩ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በቅዱስ ቁርዓንም የተከለከለ በመሆኑ በቀዳሚነት የእስልምና እምነት ተከታዮችን ያገለግላል። ሆኖም የእምነቱ ተከታዮች ላልሆኑ ደንበኞችም ክፍት ነው።
በተቃራኒው መደበኛው የባንክ ሥርዓት፣ የቁጠባ ሂሳብ ለሚከፍቱ ወለድ እየከፈለ ገንዘባቸውን ሲያስቀምጥ፣ ለሚያበድረው ገንዘብ ደግሞ ወለድ ይቀበላል።
ይህም የመደበኛ ባንኮች ዋነኛ የትርፍ ምንጭ እና መንቀሳቀሻ ነው። ታዲያ ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ለሚያቀርቡት ገንዘብ እንዴት ትርፋማ ይሆናሉ?
ከሦስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው ሂጅራ ከወለድ ነጻ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙባረክ ሸሞሎ እንዲሁም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነጻ ባንክ የሆነው የዘምዘም ባንክ የቢዝነስ ስትራቴጂ እና ኢኖቬሽን ዳይሬክተር ከድር አባስ ከወለድ ነጻ ባንክን ትርፋማ የሚያደርጉት በርካታ አስራሮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ።
ከወለድ ነጻ ባንክ ምንም እንኳን በእስልምና አስተምህሮት መሰረት ቢንቀሳቀስም የማትረፍ ዓላማ ያለው ነው። የዚህ የባንክ ሥርዓት ሥራዎች በሙሉ በባንኩ እና በደንበኛው መካከል ትርፍ እና ኪሳራን መጋራትን መሰረት የሚያደርግ ነው።
"ደንበኞች ወደ እኛ ሲመጡ ትርፍንም ኪሳራንም ለመጋራት ወስነው ይመጣሉ ማለት ነው" ሲል የሚያስረዳው ሙባረክ "ደንበኞች የሚያስቀምጡት ገንዘብ ባንኩ የተፈቀዱ ቢዝነሶች ላይ ፋይናንስ አድርጎ ያ ፋይናንስ ትርፍ ካመጣ ከደንበኛው ጋር ትርፍ ይጋራል፤ ኪሳራ ይዞ ከመጣም ኪሳራን ነው የሚጋራው" በማለት ያብራራል።
ይህም በተለያየ የባንኩ ሥርዓቶች የሚተገበር ሲሆን ደንበኞች ትርፍም ኪሳራም የማይጋሩበት እና ገንዘባቸውን በአደራ የሚያስቀምጡበትም አሰራር አለ።
የባንክ ሥርዓቱ አሰራር ደንበኞች የሚፈልጉትን ዕቃ ወይም አገልግሎት ገዝቶ ከማቅረብ፣ ከባለሀብቶች ጋር በጋራ ኢንቨስት እስከማድረግ የሚዘልቅ ነው።
የሽያጭ ውል ፋይናንሲንግ
ከወለድ ነጻ ባንክ 'የሽይጭ ውል ፋይናንሲንግ' በተሰኘው የብድር ሥርዓቱ፣ ባንኩ ደንበኛው ወይም 'ተበዳሪ' የሚፈልጋቸውን ንብረቶች ገዝቶ ያቀርባል።
የባንኮቹ አመራሮች በሸሪአ ሕግ ወለድ የተከለከለ ቢሆንም ነግዶ ማትረፍ የተፈቀደ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ወይም ቀደም ብሎ ከገዛቸው ንብረቶች ደንበኞች በዱቤ የሚወስዱበት አሰራር መሆኑን ጠቅሰዋል።
የተገዛውን ንብረት ባንኩ ለደንበኛው ሲያቀርብ ከተገዛበት ዋጋ ጨምሮ እንደማንኛውም ንግድ የሚያተርፍ ይሆናል።
ይህም በተለያየ መንገድ ይቀርባል፤ ለአብነት 'ሙራብሃ' የተሰኘው አገልግሎት ደንበኛው የሚፈልገውን አገልግሎት ወይም ምርት ባንኩ የገዛበትን ዋጋ እና የሚያተርፈውን በግልጽ አስታውቆ የሚያቀርብበት ሥርዓት ነው።
የተገዛው ንብረት ወይም አገልግሎት በባንኩ ስም ሆኖ፣ ትርፉም ምርቱ ወይም አገልግሎቱ በጊዜ ውስጥ ሊኖረው በሚችል ዋጋ የሚሰላ ይሆናል።
ይህ አገልግሎት በእስላማዊ ባንክ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚሸፍን ሲሆን ይህም እንደ ተሽከርካሪ እና ቤት ያሉ ንብረቶች የሚጠቃለሉበት ነው። ታዲያ እንደ ሙባረክ ገለጻ "ባንኮች እንደ ነጋዴ ገበያ ወጥተው በሽያጭ ያስተላልፋሉ ማለት ነው።"
በሌላ በኩል 'ባይሰለም' የሚባለው አገልግሎት ደግሞ ለግብርና ሥራዎች የሚቀርብ ሲሆን ከወለድ ነጻ ባንኩ ለአርሶ አደሮች ገንዘብ በማቅረብ ትርፍ ወይም ኪሳራ የሚጋራበት ነው። በሌሎች አገራት ለማኑፋክቸሪንግ ሥራዎች ፋይናንስ የሚቀርበው ከዚሁ የባንክ አገልግሎት ነው።
'ኢስቲስና' የተሰኘው አገልግሎት ደግሞ በጊዜ ሂደት ለሚሻሻል ቢዝነስ የሚቀርብ ፋይናንስ ሲሆን፣ እንደ ህንጻ ግንባታ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ያካትታል።
ለአብነት ህንጻ መገንባት የሚፈልግ ሰው ከወለድ ነጻ ባንክ ገንዘብ ወይም 'ብድር' በሚፈልግበት ወቅት የህንጻውን ሙሉ እቅድ ያቀርብና ባንኩ ካመነበት ጨረታ አውጥቶ ያስገነባለታል። ከግንባታው በኋላም ባንኩ አትርፎ መልሶ ለደንበኛው የሚሸጥበት ነው።
የሽርክና ፋይናንስ
ይህ ሥርዓት ባንኩ ደንበኞች ላሏቸው የቢዝነስ ሃሳቦች ገንዘብ በማቅረብ ወደ ተግባር የሚቀይርበት ሲሆን፣ ባንኩ በድርሻ ወይም በውል ትርፍ ወይም ኪሳራ የሚጋራበት ነው። በዚህ አሰራር ኢንቨስትመንቶቹ ላይ የጋራ አመራር ሊሰጡም ይችላሉ።
በዚህ ውስጥም 'ሙዳራባህ' ተጠቃሽ ነው። ይህ አገልግሎት ባንኩ ለደንበኛው ፋይናንስ የሚያቀርብበት ሲሆን ትርፍ ካለ በስምምነታቸው መሰረት በጋራ ይካፈላሉ። ኪሳራ ካለ ግን የባንኩ ብቻ ይሆናል።
'ሙሻራካህ' ደግሞ ከወለድ ነጻ የባንክ ፋይናንስ ዓይነት ሲሆን ደንበኛው ያለውን ካፒታል በማወጣት ከባንኩ ጋር ኢንቨስት የሚያደርጉበት ሲሆን፤ በጊዜ ሂደት ባንኩ ከንግድ ሥራው የሚያገኘው የትርፍ ድርሻ ሊቀር የሚችልበት ነው።
በተጨማሪም እስላማዊ የባንክ ሥርዓት የተለያዩ አግልግሎቶች ወይም ምርቶችን በማከራየት፣ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ በመሰማራት ወይም በሌሎች መንገዶች ትርፍ ሊያሰባስብም የሚችልበት መንገድ አለ።
በእነዚህ ሂደቶች ሁሉ በዚህ ሥርዓት ስር ያሉ ባንኮች ገንዘብ ተቀበለው ያለምንም አገልግሎት ወይም ሽያጭ 'ገንዘብ ላይ ገንዘብ ጨምረው' እንዲሁም ከቅዱስ ቁርአን ጋር በማይጻረር መልኩ አለመስራታቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል።
ከወለድ ነጻ ባንክ 'ብድር' መመለስ ያልቻሉ ሰዎችን አይቀጣም። ፋይናንስ የቀረበለት ሰው በተለያዩ ምክንያቶች ከባንኮቹ የወሰደውን ገንዘብ መመለስ ባይችል ወይም በሚጠበቅበት ጊዜ ባይመልስ "ቅጣት የሚባል መርህ የሼሪአ ሕጉ አያውቅም" በማለት ሙባረክ ይገልጻል።
"መለኮታዊ ትዕዛዝ ነው። ሰዎች ላበደሯቸው ብድር አታስጨንቁ የሚል ነገር አለ። ሳታስጨንቋቸው በተጨማሪ ደግሞ ከቻላችሁ ተዉላቸው የሚል አለ። ስለዚህ ያንን [ቅጣቱን] አያውቅም" ብሏል።
ሆኖም 'ለፍትሃዊነት' በሚል ዓለም አቀፍ የእስልምና ተቋማት የሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ድርጅት ገንዘቡን በወሰደው ሰው ፍላጎት የሚፈጸም ወይም ደንበኛው ራሱን የሚቀጣበት የ3 በመቶ ቅጣት ደንግጓል። የተገኘው የቅጣት ገንዘብ ደግሞ የባንኩ ገቢ ሳይሆን ለእርዳታ ተቋማት የሚበረከት መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል።
ከወለድ ነጻ ባንክ በኢትዮጵያ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ መልኩ የሚተገበረው ከወለድ ነጻ የባንክ ሥርዓት በመደበኛ ባንኮች ውስጥ በመስኮት፤ በመደበኛ ባንኮች በቅርንጫፍ ደረጃ፤ የመደበኛ ባንኮች እህት ኩባንያ በመሆን ወይም እንደ ዘምዘም እና ሂጅራ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነጻ ሆኖ ሊቋቋም የሚችልበት አማራጮች አሉት።
በኢትዮጵያ ይህ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ የተጀመረው ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ሙሉ በመሉ ከወለድ ነጻ የሆነ ባንክ ሥራ የጀመረው ግን ከወራት በፊት ነው።
በኢትዮጵያ መሰል አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ሳይኖር መቆየቱ ከ13 ዓመታት በፊት የተጠነሰሰው እና በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከወለድ ነጻ ባንክ የሆነው ዘምዘም፣ በብዙ ውጣ ውረድ እንዲያልፍ አስገድዷል። ይህም የፋይናንስ አካታችነት ላይ ጥያቄ ያስነሳ ነበር።
ይሁን እንጂ በ2011 ዓ. ም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ የተለያዩ ከወለድ ነጻ ባንኮች አክሲዮን መሸጥ የጀመሩ ሲሆን ሁለቱ ባንኮች ደግሞ ከወራት በፊት ሥራ ጀምረዋል።
ዘምዝዘም ባንክ ሥራ በጀመረባቸው አራት ወራት 30 ሺህ ደንበኞች እና 15 ቅርንጫፎች እንዳፈራ ከድር ገልጿል። ሂጀራ ባንክ ደግሞ በሦስት ወራት 14 ቅርንጫፎችን የከፈተ ሲሆን ከ22 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳገኘ ሙባረክ ይናገራል።
ነገር ግን ከወለድ ነጻ ባንኮች፣ አገልግሎቶችን በተመቻቸ ሁኔታ ለመተግበር የማያስችሏቸው ሁኔታዎች አሁንም መኖራቸውን የሚጠቅሰው ከድር፣ "ያለው የሕግ ማዕቀፍ ከመደበኛው ጋር የተቆራኘ ነው።...ከመንግሥት እሱን ከማስተካከል አኳያ ቀና ነገሮች አሉ" ብሏል።
ሙባረክ በበኩሉ በብሔራዊ ባንክ ደረጃ ከወለድ ነጻ ባንኮችን የሚከታተል እና ሸሪአን መሰረት ያደረገ ተቆጣጣሪ አካል ሊኖር ይገባል ብሏል።















