የእናቷን ህይወት ለመታደግ የህክምና ታሪክ የሰራችው ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Aliana Deveza
አሊያና ዴቬዛ የ19 ዓመት ታዳጊ እያለች የእናቷን ህይወት ለማትረፍ ታሪካዊ የተባለ የቀዶ ህክምና ተደረገላት።
የቀዶ ህክምናውን ታሪካዊ ያደረገው አሊያና በቤተሰቦች መካከል የሚደረገውን የአካል ልገሳ ታሪክ በመቀየሯ ነው።
አሊያና ለእናቷ ኩላሊት መስጠት ባለመቻሏ የእናቷ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የቀዶ ህክምናን ለማሳካት የተወሰነ ጉበቷን ለሌላ ግለሰብ መስጠት ነበረባት።
ሁለት እህትማማቾችን አግኝታ፣ አንደኛዋ ለእናቷ ኩላሊት ስትሰጣት፣ አሊያና ደግሞ በለውጡ ለሌላኛዋ እህት ጉበቷን በቅያሪ ለገሰች።
በአሜሪካ ቤተሰብ ያልሆኑና የማይዛመዱ ለጋሾች የሌላቸውንና የሚያስፈልጋቸውን የአካል ክፍል እርስ በርስ እንዲቀያየሩ ሁለት እህትማማቾችን በማምጣትና ሆስፒታሉን ማሳመን በመቻሏ ታሪክ ሰርታለች ተብሏል።
"መጀመሪያ ከእንቅልፌ ስነቃ የጠየቅኩት እናቴ እንዴት ነች? ደህና ነች? ተረፈች?" ነበር ያልኩት ትላለች ቀዶ ህክምና ከተደረገላት በኋላ በነቃችበት ወቅት ያለችውን ስታስታውስ።
"የሚሰማኝ ህመም ቀለል እንዲለኝ ትኩረት ብሰጥም፤ ስለ ራሴ ብዙም አልተጨነቅኩም ነበር። ሁሉም ከቀዶ ህክምናው በሰላም እንደወጡ ስሰማ መተንፈስ ቻልኩኝ" ትላለለች አሊያና።
አሊያና ስትናገር ስለራሷና እና ስለ እናቷ ብቻ አይደለም የምታወራው ምክንያቱም ሌሎች ሁለት እህትማማቾችም ቀዶ ህክምና እየተደረገላቸው ነበር።
አሊያና የጉበቷ የተወሰነ ክፍል ለአንደኛዋ እህት የተለገሰ ሲሆን የሌላኛዋ እህት ኩላሊት ደግሞ ለአሊያና እናት ተለግሷል። በነዚህም ቀዶ ህክምናዎች የሁለት ሰዎች ህይወትን መታደግ ተችሏል።
ሁለት የማይተዋወቁ ግለሰቦች፣ አንደኛዋ የአንደኛዋን ቤተሰብ ለማዳን አካል ተለዋውጠው በህይወት ተረፉ።
እነዚህን ቀዶ ህክምናዎች ማከናወንም ቀላል አልነበረም፤ ግለሰቦቹንም ለማገናኘትም ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሊያና ለዓመታት የኩላሊት ዲያሊሲስ ሲያደርጉ ከነበሩትና የመኖር ተስፋቸው እየተመናመነ መሆኑ የተነገራቸውን እናቷን ህይወት አተረፈች። እሱ ብቻ አይደለም ለማታውቃት ሴት ጉበት በመለገስ አዲስ ተስፋን ሰጠቻት።
ኩላሊት በህይወት ያሉ ሰዎች ለሌላው ከሚለግሷቸው የሰውነት አካል ክፍሎች ውስጥ አንዱ ነው። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ከሁለት ኩላሊት ጋር ቢወለድም በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልገው ግን አንድ ብቻ ነው።
ምንም እንኳን ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆን ኩላሊት የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ሁልጊዜ ከቤተሰብና ከዘመድ መውሰድ አይችሉም።
በአውሮፓውያኑ 2019 በዓለም ዙሪያ ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ የአካል ክፍሎች በንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና ከአንድ ሰው ወደ ሌላ እንዲተላለፉ ተደርጓል።
አልቪን ሮት በአውሮፓውያኑ 2012 በርካታ ሰዎች ኩላሊት እንዲሰጡ እና እንዲያገኙ የሚረዳ ዘዴ በመቀየስ ከኖቤል ፋውንዴሽን የምጣኔ ሀብት ሽልማትን አግኝተዋል።
"ከሌሎች አካሎች በተለየ ለሚወዱት ሰው ኩላሊት ሰጥቶ ህይወት ማትረፍ ይቻላል" ሲሉ ይናገራሉ።
"ምንም እንኳን እርስዎ ጤነኛ ቢሆኑና ህይወት ማዳን ቢፈልጉም የሚለግሱት ሰው ኩላሊትዎን ሊወስዱ የማይችሉበት ሁኔታ አለ። ለምወደው ሰው ኩላሊት መስጠት እፈልጋለሁ ነገር ግን አልችልም። ስለዚህ ምናልባት የእኔ ኩላሊት ለሌላ ታካሚ ሊሰራ ይችላል የሌላኛው ለጋሽ ደግሞ ከእኔ ታካሚ ጋር ሊጣጣም ይችላል" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Nobel Media
ሁለት ለጋሽ ጥንዶች የሚጣመሩበት እና እያንዳንዱ ታካሚ ተስማሚ የሆነ ኩላሊት የሚያገኙበት ቀላሉ የኩላሊት ልውውጥ ሥርዓት ነው።
የአልቪን ሮት እና የሥራ ባልደረቦቹ ጅማሮ የኩላሊት መለዋወጥን ቁጥር ለመጨመር የሚያስችል ሥርዓት አስገኝቷል። ይህም ሥርዓት አሁን በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት መታደግ አስችሏል።
ነገር ግን እነዚህ የአካል ልውውጦች በሁሉም ቦታ እስካሁን ሕጋዊ አይደሉም። ለምሳሌ በጀርመን ውስጥ አካልን መለገስ የሚቻለው በቅርብ ቤተሰብዎ ላለ ሰው ብቻ ነው።
በዚህ ላይ አንዱ ስጋት ገንዘብ ያጠራቸው ሰዎች በገንዘብ ለመሸጥ ይወተወቱ ይሆናል የሚለው ነው።
በዚህ ተጠቃሚ የሚሆኑት ጥንዶች ብቻ አይደሉም። በአንዳንድ ሁኔታዎች የሚለገሱ ኩላሊቶች እንዲጣጣሙ በሚልም በርካታ ሰዎች ተሰባስበው የሚመጡበት አጋጣሚም አለ።
በአንድ አጋጣሚም 70 ለጋሾች ለ35 ግለሰቦች ኩላሊት ለመለገስ ተሰባስበው የመጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 35 ለጋሾች መለገስ ችለዋል።
አሊያና ኩላሊቷን ከእናቷ ጋር መቀያየር አልቻለችም ምክንያቱም ዶክተሮቹ እናቷ ያጋጠማት የኩላሊት ችግር በዘር የሚተላለፍ ሊሆን ይችላል ብለው ስለፈሩ አሊያናም ሊኖርባት ይችላል ብለው በመስጋታቸው ነው።
እናቷ አዲስ ኩላሊት እንድታገኝ ብትፈልግም እሷ ማድረግ አልቻለችም። ስለዚህ በርካታ ምርምሮችን አድርጋ በኩላሊት ጉበት መቀየር እንደሚቻል ተረዳች።
"አንድ ሰው በህይወት እያለ የሚለገሱ የአካል ክፍሎችን አይነት ምርምር ማድረግ ጀመርኩ። እናም በርካታ ጊዜ የተጠቀሰው ጉበት ነው" ትላለች።
አሊያና ይህ እሳቤ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ያለ እንጂ መደበኛ ቀዶ ህክምና እንዳልሆነ አላወቀችም።
አሊያና ጥቂት ሆስፒታሎች ጋር በደወለችበት ወቅት ምን ለማለት እንደፈለገች እንዳልተረዱ ትናገራለች "ጥቂት ሆስፒታሎች አስከሬን ክፍል እንዳናግር ያስተላልፉኝ ነበር። ምክንያቱም ስለምን እንደምናገር ስላልገባቸው ነው" ትላለች።
በመጨረሻም ለሥራው ትክክለኛውን ሰው አገኘች። በሳንፍራንሲስኮ ውስጥ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የቀዶ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ጆን ሮበርትስን አገኘች።
"ሃሳቤን አላጣጣሉትም። የ19 ዓመት ልጅ ነበርኩኝ፤ እና ጤነኛ አልመሰልኳቸው ይሆን? እኔ እንጃ። ቤተሰቦቼ አደጋ እንዲደርስብኝ ስላልፈለጉም ጣልቃ እንድገባ አልፈለጉም" በማለት የነበረውን ታስታውሳለች።
በሆስፒታሉ እርዳታ ከአሊያና እና ከእናቷ ጋር በልገሳ የሚጣመሩ ሁለት እህትማማቾች ተገኙ። አንደኛዋ እህት የአሊያናን ጉበት ከፊል አገኝች፣ እና የአሊያና እናት ከሌላኛው እህት አዲስ ኩላሊት ተለገሰች።
አሊያና ባደረገችው ተግባር ምንም አልተጸጸተችም። እንዲያውም "በርካቶች ይህንን የማይተገብሩት ለምን ይሆን?" በማለት ትጠይቃለች።
ከቀዶ ህክምናም ሆነ ከንቅለ ተከላ ጋር በተያያዘ ካለው ፍራቻ ጋር ተያይዞ በርካቶች የሰውነት አካል መለገስ የሚለውን ሃሳብ ሊነኩት የሚፈልጉት አይመስልም።
"የንቅለ ተከላ ቀዶ ህክምና በርካታ ጥንቃቄን የሚጠይቅና ከባድ ህክምና ነው። በእርግጥ ከሱም ጋር ተያይዞ ብዙ አደጋዎች አሉ። ነገር ግን እሱን መረዳት እና በሂደቱ ውስጥ ከእርስዎ ጋር የሚቆም ቡድን ማፍራቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጥቅም አለው" ትላለች።












