ከስድስት አገራት ሴት ሐኪሞች ጋር የዓመቱ ጀግና የተባለችው ኢትዮጵያዊት ዶ/ር ሩት ድሪባ

የፎቶው ባለመብት, Ruth Diriba
'ሕልሜ ሳይማር ያስተማረኝን ማኅበረሰብ ማስተማር ነው' የሚለው አባባል በተደጋጋሚ ይሰማል።
ለአንዳንዶች አባባሉ ከአባባል የዘለለ አይደለም። እንደ ዶ/ር ሩት ድሪባ ላሉ ባለሙያዎች ግን አባባሉ ትልቅ ትርጉም አለው። ይህንንም ተግባሯ ይመሰክራል።
ዶ/ር ሩት ወጣት ሐኪም ናት።
ተወልዳ ያደገችው ሐሮማያ ነው። ሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ፊት ለፊት የሚገኘው ባቲ መንደር ውስጥ።
ከ2004 ዓ. ም. ጀምሮ ለስድስት ዓመታት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ተምራለች። ተማሪ ሳለች ሕልሟ አንድና አንድ ነበር። ገጠር ሄዶ መሥራት።
በቀድሞው ደቡብ ክልል፣ በአሁኑ ሲዳማ ክልል ሥር ያለው ለኩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስትመደብ ታዲያ በደስታ ነበር የተቀበለችው።
ዶ/ር ሩት በሕፃናት ከዚያም በድንገተኛና ተመላላሽ ሕክምና ክፍል ሠርታለች። የሴቶች ጤና ትኩረት ከምትሰጣቸው ዘርፎች አንዱ ነው።
አሁን ላይ 'ላስት ማይል ኸልዝ' በሚባል ተቋም ውስጥ በኮሮናቫይረስ መከላከል ላይ እየሠራች ትገኛለች።
ለሙያዊ አበርክቶዋ በጎርጎሮሳውያኑ 2021 የዓመቱ ጀግና የጤና ባለሙያ ተብላለች።
እውቅናውን የሰጣት 'ዊሜን ኢን ግሎባል ኸልዝ' ነው። ከእሷ ጋር የኬንያ፣ የሊባኖስ፣ የሕንድ፣ የፓናማ፣ የፓኪስታን እና የሴራሊዮን ሴት የጤና ባለሙያዎች ተመስግነዋል።
ሰባቱ ሴቶች፣ ለሴቶች ጤና እንዲሁም ለጾታ እኩልነት ባበረከቱት አስተዋጽኦ ነው ጀግኖች የተባሉት።
ከዓለም አጠቃላይ የጤና ሥርዓት 70 በመቶው የሚሸፈነው በሴቶች ቢሆንም፣ ሴቶች በዓመት ለጤናና ማኅበራዊ ዘርፉ በአማካይ ወደ 3 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ ቢያስገኙም፣ በማኅበረሰብ ተኮር ጤና ጉልህ ድርሻ ቢኖራቸውም ሲመሰገኑ፣ ሲሞገሱ፣ ሲከበሩም አይስተዋልም።
ስለዚህም 'ዊሜን ኢን ግሎባል ኸልዝ' በየዓመቱ፣ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ሴት የጤና ባለሙያዎችን ያወድሳል።
ዶ/ር ሩት እውቅናውን ካገኘች በኋላ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ "ሳይማር ያስተማረኝን ማኅበረሰብ ላስተምር የሚለው ለአንዳንዶቻችን አንዲሁ አባባል ነው። ማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ችግር እስከምንረዳው ድረስ" ነበር ያለችው።
በለኩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የነበራት ቆይታ በሴቶች እና በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ እንድትገፋ እንዳበረታታትም ትናገራለች።
"መጀመሪያ ደነገጥኩ፤ ከዚያ ደስ አለኝ"
ዶ/ር ሩት የዓመቱ 'Heroine of Health' [የጤናው ዘርፍ ጀግና] ተብላ እንደተመረጠች ስትሰማ ምን ተሰምቷት ይሆን?
"መጀመሪያ ደነገጥኩ። ከዚያ ደስ አለኝ። ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጥል ሽልማት ነው። ከሠራሁት ሥራ በላይ ለወደፊት የበለጠ መሥራት እንዳለብኝ አሳይቶኛል። እውቅና ስለተሰጠኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ሽልማቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ ታታሪ ሠራተኞች፣ ለጥሩ ሥራቸው እውቅና የሚሰጥ ነው።"
ሽልማቱ በየዓመቱ ከተለያዩ አህጉሮች፣ በጤና አገልግሎት የተሰማሩ ሴቶችን ያካትታል። የዘንድሮው ትኩረት ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሠሩ ሴት ባለሙያዎች ናቸው።
ዶ/ር ሩት አሁን የምትሠራበት 'ላስት ማይል ኸልዝ' ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በላይቤሪያ፣ ኡጋንዳ እና ማላዊ ይሠራል። ከእነዚህ አገራት ባለሙያዎች ከታጩ በኋላ ነው እሷ ከኢትዮጵያ ያሸነፈችው።
የዓመቱ ጀግና የጤና ባለሙያ የተባለችው በዚህ ተቋም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መተግበሪያ የተመረኮዘ ማሠልጠኛ በማዘጋጀት ነው። የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን በበይነ መረብ በማሠልጠንም ትሳተፋለች።
"ሽልማቱ ብዙ መንገዶችን ይከፍትልኛል"
በላስት ማይል ኸልዝ ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ስለ ኮቪድ-19 መተግበሪያ-መር ሥልጠና ስትሰጥ ያስተዋለችው ትልቅ ክፍተት የሴቶች ተሳትፎ ውስን እንደሆነ ነው።
"ይህ ማለት ሴቶች በይነ መረብን አይጠቀሙም ማለት አይደለም። ሥልጠና ሲሰጥ ግን ቁጥራቸው ያንሳል። ትኩረቴ እንዴት ይህን ቁጥር እንጨምር? የሚለው ነው።"
ከወጣት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ብዙዎቹ ሴቶች ናቸው። በሥልጠናው ያላቸው ተሳትፎ ግን ይህንን አያንጸባርቅም።
ዶክተሯ፤ ዓለም አቀፍ ሽልማት ማግኘቷ ችግሩን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዛት ታምናለች።
"ሽልማቱ ከእውቅና ባለፈ የተለያዩ ዕድሎችን ይከፍታል። በእነዚያ ዕድሎች ራስን ከማሳደግ ባለፈ ማኅበረሰብን መጥቀም ይቻላል" ትላለች።
ዶ/ር ሩት ሽልማቱ በሚከፍትላት መንገዶች፤ በሙያዋ የምታያቸውን ችግሮች መፍትሔ ማበጀትን ትመኛለች። ለዚህም ነው ሽልማቱ "እንድናገርም እንድሠራም ያደርገኛል" የምትለው።
"የሴቶች ጤና ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር ብቻ የተገናኘ አይደለም"
የሴቶች ጤና ሲባል በአብዛኛው ከእርግዝና እና ወሊድ ጋር ለተያያዙ የጤና እክሎች ትኩረት ይሰጣል። ነገር ግን ሕመም የሚገጥመው በእነዚህ ወቅቶች ብቻ አይደለም።
ዶ/ር ሩት እንደ ፌስቱላ እና የማሕፀን ወደ ውጭ መውጣት ያሉ ሕመሞች ትኩረት እንዲቸራቸው ትመክራለች።
ከእርግዝና እና ከወሊድ ወይም ልጅን ከማሳደግ ባለፈ የሴቶች ጤና ሲባል የጡት ካንሰር፣ የማሕፀን ካንሰር እና ሌሎችም ሕመሞች በደንብ ሊሠራባቸው እንደሚገባ ታክላለች።
"በተለይ በደቡብ ክልል በብዛት የሚገጥመው የማሕፀን ወደ ውጭ መውጣት ነው። ትልልቅ ነገር ማንሳት፣ ቆጮ በሚሠራበት ጊዜ ሆድ ላይ የሚያርፈው ጫና እና ብዙ ልጅ መውለድ የችግሩ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ላይ መሠራት አለበት" ትላለች።
ሌላው ችግር ሴቶች ዕድሜያቸው ሳይደርስ ሲያገቡ ከትምህርት ገበታ መሰናከላቸው ነው።
ሴት ታዳጊዎች ከገጠር ወደ ከተማ ለትምህርት ቢሄዱም እንኳን፤ በቆይታቸው እርግዝና ከዚያም ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሲከሰት ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።
ይህም ወደ ሁለተኛ ደረጃ እና ወደ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ሴቶችን ቁጥር ይቀንሳል።
ዶክተሯ የምትመክረው በየአካባቢው የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት በተለይም በሴቶች ላይ ተተኩሮ እንዲሰጥ ነው። የጤና ተቋሞች የሥነ ልቦና ድጋፍ በመስጠትም ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
"የመራቢያ አካል ሕመሞች እንደ ነውር ይቆጠራሉ"
ዶ/ር ሩት እንደምትለው፤ ከማሕፀን ወይም ከመራቢያ አካላት ጋር የተያያዙ ሕመሞች ማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ 'ነውር' ይቆጠራሉ።
እናም ሴቶች ስለ በሽታዎቹ ከማውራት፣ ወደ ሕክምና ከመሄድም ይቆጠባሉ። ሆስፒታል የሚሄዱትም ሕመሙ በጣም ውስብስብ ደረጃ ደርሶ፣ ቁስለት ወይም ኢንፌክሽን ሲከሰት ነው።
ማኅበረሰቡ ሕመሞቹ 'የእግዜር ቁጣ' ናቸው ብሎም ያምናል። ይህ የተዛባ አመለካከት ተቀርፎ ሴቶች ወደ ሕክምና እንዲሄዱ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ታስረዳለች።
በማሕፀን ሕክምና እና በቀዶ ሕክምና የሚሠሩ ተቋሞች በጥምረት ንቅናቄ እንዲፈጥሩ ትመክራለች።
ከለኩ እስከ ላስት ማይል ኸልዝ
በለኩ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለሁለት ዓመታት ሠርታለች። ማኅበረሰብን ማገልገልን በተግባር የተረዳችበት ወቅት ነው።
አዲስ የጤና ምሩቅ ሆና የመሥራት ፍላጎት እና አቅም ይዛ ነበር ወደ ለኩ ያቀናችው።
ሴቶች ግላዊነታቸው ተጠብቆ ምርመራ የሚያደርጉበት ክፍል እንዲኖር ማስቻል አንደኛው ጥያቄዋ ነበር። ሌላው ደግሞ የሕፃናት ሕክምና ክፍሎች ልጆችን ያማከሉ እንዲሆኑ በሥዕል እና መጫወቻ ማሳመር።
"በጤናው ዘርፍ መስተካከል ስላለባቸው ነገሮች መጠየቅ ተነሳሽነትን ያላሽቃል። ግን በተደጋጋሚ መጠየቅ ያስፈልጋል። የለኩ ቆይታዬ ይህን ዓይነት ጽናት አስተምሮኛል" ትላለች።
በሌላ በኩል ሴት የጤና ባለሙያዎች ከመደበኛ ሠራተኛነት እስከ አመራር ባለው ደረጃ ተካታች እንዲሆኑ ትጠይቃለች።

የፎቶው ባለመብት, Ruth Diriba
ከለኩ በኋላ የተቀጠረችው በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ነው። ለሁለት ዓመታት ያህል አዲስ ሕመም ሲከሰት በመመርመር እና በድንገተኛ ጊዜ ክፍል ጥናት በመሥራት ቆይታለች።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በብሔራዊ ደረጃ ለመገናኛ ብዙኃን መረጃ በመስጠት ማኅበረሰብ አሳታፊ የንቅናቄ ሥራ ትሠራ ነበር።
አሁን በላስት ማይል ኸልዝ ቴክኖሎጂ-መር የጤና ዘርፍ አገልግሎት ላይ ትገኛለች።
በቀላሉ መከላከል የሚቻሉ ሕመሞች በተመለከተ በበቂ ሁኔታ አለመሠራቱን ከግምት በማስገባት በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ላይ አተኩራ ትሠራለች።
"ለምሳሌ በቀላሉ ንጽሕናን በመጠበቅ ልናስወግዳቸው የምንችላቸው ሕመሞች አሉ። ሰዎች ሲታመሙ ግን ብዙ ብር ያወጣሉ። ይህም የምጣኔ ሀብት ላይ ጫና ይፈጥራል" ትላለች።
የማኅበረሰብ ጤና መነሻ ነጥብ ላይ ያሉትን የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ማብቃት አንዱ መፍትሔ እንደሆነም ታክላለች።
በሥርዓተ ጤናው ምን ይሻሻል?
ዶ/ር ሩት ሥርዓተ ጤናውን ለማሻሻል ዘርፉን በባለሙያዎች ማስተዳደር እና አስተማማኝ የጤና መድኅን መፍጠርን ትመክራለች።
የጤናው ዘርፍ የገንዘብ፣ የባለሙያ፣ የመሣሪያ እጥረትና የአመራር ክፍተት እንዳለበት ሙያተኞች ይናገራሉ።
"በተለይም በክልል ከተሞች የጤና ተቋም የሚመሩ ሰዎች የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች ላይሆኑ ይችላሉ። የአመራር ብቃት ቢኖራቸውም የጤና ባለሙያ ካልሆኑ የጤና ዘርፍን ያላገናዘበ ውሳኔ ይሰጣሉ። ያ ባለሙያውን ያናድዳል" በማለት ታብራራለች።
ከምንም በላይ ታማሚዎችን ማዳን ግቡ የሆነ ባለሙያ በእውቀቱ ሕክምና መስጠት የሚያስችል ግብዓት ሲያጣም ተስፋ ያጨልማል።
የጤና ዘርፉን የሚመለከት ውሳኔ ሲሰጥ አልያም በጀት ሲመደብ ባለሙያዎች መካተት እንደሚገባቸው ትናገራለች።
አስተማማኝ የጤና መድኅን መዋቅር አለመዘርጋቱ ሌላው ክፍተት ነው።
በተለይ በገጠር ሕሙማን ሀብት ንብረታቸውን ሸጠው ነው የሚታከሙት። እንደ ኩላሊት እጥበት ካሉ ሕክምናዎች በኋላ እንዴት ኑሮን ይገፋሉ? የሚል ጥያቄም ያጭራል።
"የጤና መድኅን ሲኖር ለታካሚው ብቻ ሳይሆን ለጤና ሥርዓቱም ይጠቅማል። ለምሳሌ በመንግሥት ሆስፒታሎች ሰው በአነስተኛ ዋጋ ይታከማል። ይህ ለታካሚው ጥሩ ቢሆንም የጤና ሥርዓቱን ግን ይጫናል። የሕክምና ክፍያ ታማሚውንም የጤና ሥርዓቱም በማይጎዳበት መንገድ ለማስቀጠል የጤና መድኅን ያስፈልጋል" ትላለች።












