የአፍሪካ ዋንጫ፡ ከዋሊያዎቹ ጋር የተመደቡት ቡድኖች ሲቃኙ

ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎቹ የአልጄሪያ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎቹ የአልጄሪያ ቡድን

በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሳምንት በኋላ እሑድ ጥር 01/2014 በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ይጀምራል።

ኢትዮጵያ በምድብ 'ሀ' ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቬርድ ጋር ተደልድላለች። ካሜሩን በመጀመሪያው ጨዋታ ቡርኪና ፋሶን ስታስተናግድ፤ ዋሊያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን እሑድ ጥር 01 ምሽት ከኬፕ ቬርድ ያደርጋሉ።

ሐሙስ ጥር አምስት ኢትዮጵያ ሁለተኛ ጨዋታዋን ከአዘጋጇ ካሜሩን ጋር ስታደርግ በዚያኑ ቀን ኬፕ ቬርድ ቡርኪና ፋሶን ትገጥማለች።

በሦስተኛውና በመጨረሻው የምድቡ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡርኪና ፋሶን ስትፋለም ካሜሩን ደግሞ ከኬፕ ቬርድ ትገጥማለች።

ኢትዮጵያ (ካሌብ ሞገስ፣ ከቢቢሲ አማርኛ እንደጻፈው)

ዋሊያዎቹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዋሊያዎቹ
መስመር
  • የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ: ለ11ኛ ጊዜ
  • ቅጽል ስም: ዋሊያዎቹ
  • አሰልጣኝ: ውበቱ አባተ
  • አምበል: ጌታነህ ከበደ
  • በአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘገበችው ውጤት: አሸናፊ(1962)
  • በፊፋ ያላት ደረጃ: 137
መስመር

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫ የደረሰችው ከዘጠኝ ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው።

በ1962 (እአአ) የአህጉሪቱን ትልቁን ዋንጫ ያነሱት ዋሊያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ ይህኛው ለ11ኛ ጊዜ ነው።

በዓለም እግር ኳስ 137ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተና በአምበሉ ጌታነህ ከበደ እየተመራች ወደ ያውንዴ አቅንታለች።

ይህ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለአሠልጣኝ ውበቱ አባቱና ለቡድኑ አባላት ከአፍሪካ ዋንጫ መሥራቾች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ያላትን ተሰጥዖ የሚያሳዩበት መድረክ እንደሚሆን ይገመታል።

ውበቱ ለዓይን ገዥ የሆነውን ኳስ እግር ላይ ሳይቆዩ እየተቀባበሉ መጫወትን የሚመርጥ አሠልጣኝ ነው።

የመሃል ሜዳው ሞተር ሽመልስ በቀለና አጥቂው ጌታነህ ከበደ ከወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር ጋር በመጣመር ለተቀናቃኞቻቸው አደጋ ሊሆኑ ይችላሉ።

ውበቱ በሚመርጠው የ4-3-3 አሠላለፍ ማለትም 4 የኋላ ደጀን ሦስት አማካዮችና ሦስት አጥቂዎች ተመርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

ብሔራዊ ቡድኗን በውበቱ አባተ እያጠናከረች ያለችው ኢትዮጵያ ወደ ዙር 16 መሻገር እንደ ትልቅ ውጤት ቢታይ የሚገርም አይሆንም።

አልፎም ብሔራዊ ቡድናቸው በአፍሪካ ትልቁ ውድድር ሲሳተፍ ማየት ለጓጉ ኢትዮጵያዊያን ይህ ትልቅ ዕድል ነው።

ካሜሩን (የካሜሩን ራድዮ ቴሌቪዥን የስፖርት ክፍል ኃላፊ ኒጂዬ ኢናው እንደፃፈው)

ቪንሰንት አቡባከር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቪንሰንት አቡባከር
መስመር
  • የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ: ለ20ኛ ጊዜ
  • ቅጽል ስም: የማይበገሩት አናብስት
  • አሰልጣኝ: አንቶኒዮ ኮንሴያኮ
  • አምበል: ቪንሴንት አቡባካር
  • በአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘገበችው ውጤት: አሸናፊ (1984, 1988, 2000, 2002, 2017)
  • በፊፋ ያላት ደረጃ: 50ኛ
መስመር

በፈረንጆቹ 2017 ካሜሩን ግብፅን በመርታት የአፍሪካ ዋንጫን ስታነሳ የማሸነፊያዋን ግብ ያስቆጠረው ቪንሴንት አቡበከር ነበር።

የአፍሪካ ዋንጫን አምስት ጊዜ ያነሳችው ካሜሩን በውድድሩ የምትሳተፈው ለ20ኛ ጊዜ ነው። በአሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንሴያኮና በአምበሉ ቪንሲኔት አቡበከር ትመራለች።

በዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ 50ኛ ላይ የተቀመጠችው ካሜሩን የምትዘጋጀውን ዋንጫ በማንሳት የአፍሪካ ዋንጫ ቁጥሯን ወደ ስድስት ለማሳደግ ነው።

ኳስን ይዞ በመጫወት የሚታወቁት ፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ አንቶኒዮ ኮንሴያኮና ቡድኑን የተረከቡት መስከረም 2019 ነበር።

አንቶኒዮ ቡድኑን ከተረከቡት በኋላ ካሜሩን ጫና በማሳደር የምትጫወት ሲሆን በግራና በቀኝ ክንፍ የሚሰለፉ ተጫዋቾች በማጥቃትና በመከላከል የጎላ ሚና እንዲኖራቸው ይጠበቃል።

የማይበገሩት አናብስት መሃል ላይ የናፖሊውን አንድሬ-ፍራንክ ዛምቦ አንጊሳን አሰልፈው ኳስ ይዘው እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

የባየር ሙኒኩን ኤሪክ ቹፖ-ሞቲንግ እንዲሁም የሊዮኑ ካርል ቶኮ ኢካምቢ የማጥቃት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ።

ለአንድ ዓመት ያክል በቅጣት ምክንያት ከእግር ኳስ ርቆ የነበረው የአያክስ አምስተርዳሙ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና የአንቶኒዮ ምርጫ እንደሚሆን እሙን ነው።

ቡርኪና ፋሶ (የስፖርት ጋዜጠኛው ማሳቫዎ ቢላ እንደፃፈው)

ለአስተን ቪላ የሚጫወተው የቡርኪና ፋሶ አጥቂ በርትራንድ ትራዎሬ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ለአስተን ቪላ የሚጫወተው የቡርኪና ፋሶ አጥቂ በርትራንድ ትራዎሬ
መስመር
  • የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ: ለ12ኛ ጊዜ
  • ቅጽል ስም: ፈረሶቹ
  • አሰልጣኝ: ካሙ ማሎ
  • አምበል: ኢሱፉ ዳዮ
  • በአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘገበችው ውጤት: ሁለተኛ (2013)
  • በፊፋ ያላት ደረጃ: 60ኛ
መስመር

የቡርኪና ፋሶው አጥቂ በርትራንድ ትራኦሬ ለሁለት ወራት ያክል በጉዳት ከሜዳ ርቆ ባለፈው ሳምንት ነበር ለአስተን ቪላ የተሰለፈው።

በአሠልጣኝ ካሙ ማሎና በአምበሉ ኢሶፉ ዳዮ የምትመራው ቡርኪና ፋሶ ለ12ኛ ጊዜ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው በ2013 (እአአ) ለዋንጫ ደርሳ መረታቷ አይዘነጋም።

ልክ እንደተቀሩት የምድቡ ቡድኖች ቡርኪና ፋሶ ወደ ቀጣዩ ዙር ልታልፍ ትችላለች የሚል ግምት ተሰጥቷታል።

በወጣት ተጫዋቾች የተሞላው የካሞ ቡድን እነ ሀርቬ ኮፊ፣ ኤድሞንድ ታፕሶባ፣ ኢሳ ካቦሬ እንዲሁም በርትራንድ ትራኦሬና ጉስታቮ ሳንጋሬ ጎልተው የሚወጡት ውድድር ሊሆን ይችላል።

ከዚህም በተጨማሪ ቡርኪና ፋሶ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የመንፈስ ጥንካሬ በማለት የሥነ-ልቡና አማካሪ ይዘው ነው ወደ ካሜሩን የሚያቀኑት።

ኬፕ ቬርድ (የቀድሞው የኬፕ ቬርድ አሠልጣኝ ሉሲዮ አንቱኔዝ እንደፃፉት)

ከአምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኬፕ ቬርድ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከአምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው የኬፕ ቬርድ ቡድን
መስመር
  • የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ: ለ3ኛ ጊዜ
  • ቅጽል ስም: ሰማያዊ ሻርኮች
  • አሰልጣኝ: ቡቢስታ
  • አምበል: ሪያን ሜንዴስ
  • በአፍሪካ ዋንጫ ያስመዘገበችው ውጤት: ሩብ ፍጻሜ (2013)
  • በፊፋ ያላት ደረጃ: 73
መስመር

ኬፕ ቨርድ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈችው በፈረንጆቹ 2015 ነበር።

ለሦስተኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሳተፈው ኬፕ ቬርድ በአሠልጣኝ ቡቢስታና በአምበሉ ሪያን ሜንዴዝ ትመራለች።

ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፉ በአፍሪካ እንዲሁም በአውሮፓ መነጋገሪያ የነበሩት ሰማያዊ ሻርኮቹ፣ በዓለም የብሔራዊ ቡድኖች ደረጃ 73ኛ ላይ ተቀምጠዋል።

ካቦ ቬርድን በእግር ኳስ ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ቆርጦ የተነሳው የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህ ተሳክቶለት በፊፋ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ከነበረበት 126ኛ ደረጃ ወደ 73ኛ ማሳደግ ችሏል።

ምንም እንኳ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ለአፍሪካ ዋንጫ አዲስ ቢሆኑም የውድድሩ ክስተት ሊሆን እንደሚችሉ እገምታለሁ።

ኬፕ ቨርድ ያለችበት ምድብ ጠንካራ ቢሆንም በአሠልጣኙ ልምድ በመታገዝ ጥሩ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንሚችሉ ይገመታል።

ለካሜሩን ቡድን ከፍያለ ግምት ያላቸው ሲሆን፣ ከቡርኪና ፋሶ ጋር በመፎካከር ከምድቡ የሁለተኛ ደረጃን የማግኘት ፍላጎት አላቸው። ይህም ሆኖ የኢትዮጵያ ቡድንን የሚንቁት አይደለም።

በዚህም ከምድብ ውድድር ባሻገር ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋን የያዙት ኬፕ ቬርዶች ከዚያም ያለፈ ውጤት ለማስመዝገብ የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።