አየር መንገዶች አዲሱ የ5ጂ ኔትዎርክ በበረራ ሥርዓት ላይ መስተጓጎል ይፈጥራል አሉ

አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ግዙፍ 10 አየር መንገዶች 5ጂ (አምስተኛው ትውልድ) የሞባይል ኔትዎርክ በበረራዎች ላይ "ጉልህ የሆነ መስተጓጎል" ይፈጥራል ሲሉ አስጠነቀቁ።

አየር መንገዶች ይህን ማስጠንቀቂያ ያወጡት ቬሪዞን እና ኤቲ ኤንድ ቲ የተባሉት የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎትን ይፋ ለማድረግ ሰዓታት ሲቀራቸው ነው።

አየር መንገዶቹ የ5ጂ ኔትዎርክ በተለይ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ ውስጥ የአውሮፕላን በረራ ሥርዓትን ያውካል የሚል ስጋት አላቸው።

ይህ የ5ጂ ሞባይል ኔትዎርክ በአውሮፕላን የበረራ ሥርዓት ላይ ሊስክትለው የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ማስጠንቀቂያ የተላከው ለአሜሪካ አቪዬሸን ባለሥልጣናት ነው።

ዴልታ አየር መንገድ፣ ዩናይትድ አየር መንገድ እና አሜሪካን አየር መንገድን ጨምሮ 10 አየር መንገዶች በማስጠንቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ በመንገደኞች የበረራ አገልግሎት ላይ ጉልህ መስተጓጎል ሳይከሰት አስቸኳይ የሆነ ጣልቃ ገብነተ ያስፈልጋል ብለዋል።

አየር መንገዶቹ የቴሌኮም አግልግሎት አቅራቢዎች ከአየር ማረፊያዎች ቢያንስ በ3 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የ5ጂ ኔትዎርክ አገልግሎት እንዳይኖር ይጠይቃሉ።

5ጂ ኔትዎርክ በአውሮፕላን የበረራ ሥርዓት ላይ ሊያስከትላው የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖን በተመለከተ የቀረበው ስጋት በግዙፎቹ አውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ቦይንግ እና ኤርባስ ጭምር ተስተጋብቷል።

የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅቶች እጅግ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት የኔትዎርክ ዝርጋታቸው ከ5ጂ ኔትዎርክ ሥርዓት ጋር ለማጣጣም ሰርተዋል።

የአሜሪካ ገመድ አልባ ኮሚኒኬሽን ማኅበር ከዚህ ቀደም የ5ጂ ኔትርዎርክ ሥርዓት በአውሮፕላኖች የበረራ ሥርዓት ላይ ምንም ችግር እንደማያስከትል በመግለጽ፤ አየር መንገዶች ሥርዓቱን በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እያስተጋቡ ነው ሲል ቅሬታውን አቅርቦ ነበር።

የዚህ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሜሬዲዝ ቤከር ከጥቂት ወራት በፊት የ5ጂ አገልግሎት ወደ ሥራ በፈጥነት እንዳይገባ ማድረግ 50 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ምጣኔ ሃብታዊ ኪሳራ እንደሚያስከትል አስጠንቅቀው ነበር።

5ጂ እጅግ ዘመናዊና ፈጣን የሆነ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ብዙዎች እየተጠቀሙበት ካለው የ4ጂ ኢንተርኔት 5ጂ በሃያ እጥፍ ገደማ የፈጠነ ነው ተብሏል።

የ5ጂ የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት ሥርዓት በይፋ ሥራውን የሚጀምርበት ጊዜ አየር መንገዶች በተደጋጋሚ ባቀረቡት የበረራ ደኅንነት ስጋት ምክንያት ሲራዘም ቆይቷል።