ማርቲን ሉተር ኪንግ ማነው? ለምንስ እስከ ዛሬ ይታወሳል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ሕልም አለኝ' የሚለው የማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር አሜሪካ ውስጥ ያለውን የዘር ጭቆና እና የእኩልነት መብት አለመከበር የሚቃወም ነበር።
በርካቶችን ለተሻለ አስተሳሰብ አነሳስቷል፤ ታዋቂና ቀንደኛ ሰዎችን አከራክሯል፤ ዘንድሮም ድረስ የሚነገርለት ሐሳብ ሆኗል።
ነገር ግን ዛሬም ላይ እነዚህ ጉዳዮች አልባት አላገኙም።
ጥቁርና ድሀ ማኅበረሰቦችን ለማግለል ተብለው የሚወጡ የምርጫ እገዳዎችና ሌሎችም ተግባራት ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲታገልለት የነበረው ጭቆና አሁንም ድረስ ስለመኖሩ ማሳያ ነው።
ማርቲን ሉተር ኪንግ ማነው?
ነሐሴ ወር 1963 ላይ እስከ 250 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች ዋሽንግተን ዲሲ ወደሚገኘው ታዋቂው ሊንከን ሜሞሪያል ተምመው ነበር። ይሄ ሁሉ ሰው ታዲያ አንድ ሰው ንግግር ሲያደርግ ለማዳመጥ ነበር።
ስሙም ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ይባላል። ንግግሮቹ ዛሬም ድረስ በመላው ዓለም እንደ ነጻነት ማብሰሪያ ይታያሉ።
ማርቲን ሉተር ኪንግ በደቡባዊ ጆርጂያ ግዛት ከአንድ የሃይማኖት አባት ነው የተወለደው። አባቱ እሳቸው ካለፉበት የሕይወት ዓይነት በተለየ መልኩ ልጆቻቸው እንዲሄዱ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።
ዘርና ቀለምን መሠረት ያደረገ መድልዎ በመላው ደቡባዊ አሜሪካ ተንሰራፍቶ ነበር። በርካታ ይህንን የሚደግፉ ሕጎችም ተግባራዊ ይደረጉ ነበር።
ጥቁር ሰዎች እና ነጭ ሰዎች በተለያየ አካባቢ ነበር የሚኖሩት። እንዲገናኙ አይፈለግም።
ጥቁሮች ለጥቁሮች ብቻ ተብለው በተሰሩ ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ብቻ ነበር የሚዝናኑት።
ሌላው ቀርቶ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንኳን ጥቁሮች ለብቻው እጅግ ባረጁ መኪናዎች እንዲጠቀሙ ተደርጓል።
በአጠቃላይ ጥቁሮች ምንም ያህል ጥሩ ሥራ ቢሠሩም ከነጮች ያነሰ ክፍያ እንዲሰጣቸው ሕጎች ነበሩ።
የጥቁሮች ትምህርት ቤት፣ የጥቁሮች የጤና ተቋማት እና የጥቁሮች መንደር እየተባለ መከፋፈል በጊዜው የተለመደና ተቀባይነት ያለው ተግባር ነበር።
በፖለቲካው ዘርፍ ደግሞ ጥቁሮች እነሱ የፈለጓቸውን መሪዎች እንዳይመርጡ በተጠና እንዲሁም በተዘዋዋሪ መልኩ ሲሠራ ነበር።
ነገር ግን አሁን ላይ የማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልሞች በሙሉ ተሳክተዋል ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል።
የእርሱ ቤተሰቦች እንደሚሉት በተለይ በቅርብ ወራት እየተስተዋሉ ያሉ ነገሮች ከማርቲን ሕልም በእጅጉ የራቁና የተቃረኑ ናቸው።
በእነማርቲን ሉተር ኪንግ ዘመን ጥቁሮችን በግልጽ ያገልሉ የነበሩ ሕጎች አሁንም መልካቸውን ቀይረው እንዳሉ ናቸው።
የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊ ፖለቲከኞች አሁንም ድረስ የአናሳ ቡድኖች በተለይም የጥቁር ማኅበረሰቦችን ስም የማጠልሸትና ከሌላው ማኅበረሰብ በመለየት በምርጫ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ መቀነስን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
ለዚህ እንደ ማሳያ የሚጠቀሰው ጥቁሮች ብሔራዊ መታወቂያ የሚያገኙበትን መንገድ ማጥበቃቸው ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሰዎች ለምርጫ በሚሰለፉበት ወቅት የሚቀርቡ ምግብና መጠጦችን መከልከልም ይጠቀሳል።
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በምርጫ አሸንፈው ዋይት ሀውስን ከተቆጣጠሩ በኋላ መሰል ሕጎች እንደ ፍሎሪዳ፣ ቴክሳስ እና አሪዞና ባሉ ግዛቶች በስፋት ተግባራዊ ተደርገዋል።
አሜሪካ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግን በምታስታውስበት የፈረንጆቹ ጥር 17/2022 የታዋቂው ነጻነት ታጋይ ልጆች፤ ሰዎች ዝም ብለው በደፈናው ስሙን ብቻ አስበው እንዳይውሉ ጠይቀዋል።
ቀኑን ማክበር ብቻ ሳይሆን የእሱን ፈለግ በመከተል የጥቁር ሕዝቦችን ነጻነትና እኩልነት የሚያረጋግጡ ሕጎች እንዲወጡ ለማስገደድ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ሴት ልጁ በርኒስ ኪንግ "እኛ የማርቲን ሉተር ኪንግን በዓል እያከበርን ሲሆን እናንተም በተመሳሳይ እንድታከብሩት እጠይቃለው። ነገር ግን የምርጫ መብታችን አደጋ ላይ ከወደቀ ሁላችንም ይህንን ቀን ምክንያት አድርገን እሱ ያደርገው የነበረውን ማስቀጠል አለብን" ብላለች።
"አባቴ የሚወዳት አገሩ በፍጹም ዴሞክራሲ እንድትመራ ይናገርና ያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ የአሜሪካ ሴኔት ላይ ጫና በማሳረፍ እንድናስቀጥለው እጠይቃለው።"
የጥቁሮች የምርጫ መብት ጥያቄ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ውዝግብን ያስነሳ ጉዳይ ነው።
ታዋቂው የሃይማኖት መሪ ሬቭረንድ አል ሻርፕተን 'የአሜሪካን ዴሞክራሲ የሚፈታተን ወሳኝ ጊዜ' ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የምርጫ መብት ጉዳይ የአሜሪካ የልብ ትርታ ነው ብለዋል የማርቲን ሉተር ኪንግ መነሻ በሆነችው አትላንታ ንግግር ሲያደርጉ።
"ከማርቲን ሉተር ኪንግ ጎን መሆን ነው የምትፈልጉት ወይስ ከጆርጅ ዋላስ?" ሲሉም ጥያቄ ሰንዝረዋል። ጆርጅ ዋላስ የቀድሞ የአለባማ ገዢ የነበሩና የጥቁሮችን የበታችነት የሚሰብኩ ሰው ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማርቲን ሉተር ኪንግ ምንድነው የሠራው?
ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ያንን ንግግር ሲያደርግ ክፍፍልን አምርሮ ይተች ነበር።
ነገር ግን ከነጭ ወግ አጥባቂዎች በኩል ያገኘው ምላሽ ከበድ ያለ ነበር። ቤተሰቦቹ በየዕለቱ የእንገድላችኋለን ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸው የነበረ ሲሆን ቤታቸውም በቦምብ ጋይቷል።
ኪንግ ምንም አይነት አመጽ ባልተቀላቀለበት የትግል መንገድ የሚያምን ሲሆን ሁሌም ቢሆን ሰዎች በንግግርና በኅብረት ብቻ ማሸነፍ እንደሚችሉ ያምናል።
ፕሮፌሰር ቤንቶ እንደሚሉት በርካቶች የእሱን መንገድ ደካማነትና ሽንፈትን እሺ ብሎ መቀበል ሊመስላቸው ይችላል። ነገር ግን ይህ ትልቅ ስህተት ነው ይላሉ።
"ኪንግ ከአመጽ የጸዳችና በመግባባት ላይ የተመሠረተች አሜሪካን ያስብ ነበር። ዘረኝነት የተወገደበት፣ እኩልና ነጻ ማኅበረሰብ ተፈጥሮ ማየት ትልቁ ሕልሙ ነበር።"
በአውሮፓውያኑ 1963 ማርቲን ሉተር ኪንግ በዋሺንግተን ያደረገውም ንግግር በነጻነት መብት ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው።
በወቅቱ ኪንግ ከአመጽ ነጻ በሆነ መልኩ እንዴት ለውጥን ማምጣት እንደሚቻልና የዘር አኩልነትን ማስፈን እንደሚገባ መርሑን በግልጽ አስቀምጧል።
በቀጣዩ ዓመት በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች ላይ ጥቁሮች እንዲሄዱ አልያም በሁሉም ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዲሠሩ የሚፈቅደው ሕግ ጸደቀ።
ነገር ግን ፍልሚያው ገና በጅምር በሚባል ደረጃ ላይ ነበር።
የእኩልነት ጠላቶች በወቅቱ ዘረኛ ፖሊሲዎች እንዲወጡ ከፍተኛ ጫና ያሳድሩ ነበር። በደቡባዊ ግዛቶችም ጥቁሮች በተለይ ምርጫ ላይ ያላቸውን ተሳተፎ በእጅጉ የሚቀንሱ ፖሊሲዎች ይጡ ነበር።
ኪንግም 1965 ላይ መሰል ሕጎች እንዳይወጡ የሚቃወመውን በአለባማ ሰልማ የተካሄደውን ሞንቶጎመሪ ሰልፍ አካሂዷል።
በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም ከፖሊስም ሆነ ከነጮች የጠበቃቸው ጭካኔ የተሞላበት ምላሽ ነበር። ነገር ግን ኪንግ አሁንም ከአመጽ የጸዳ በሚለው መርሑ በመመራት ጥያቄውን ሲያሰማ ነበር።
ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዴት ነው የሞተው?
ኪንግ በተለያዩ ጊዜያት 29 ጊዜ ታስሯል። ሚያዝያ 4/1968 አሪዞና ሜምፊስ በሚገኘው የሆቴል ክፍል በረንዳ ላይ ነው አንድ ነጭ ግለሰብ በጠመንጃ ተኩሶ የገደለው።
የኪንግ ግድያ ግን የእሱን ሥራዎች በአሜሪካ አላንኳሰሰውም። የኪንግ ትግልና የትግል መንገድ እንዲሁም ተጽዕኖው አሁንም ድረስ ቀጥሏል።
የኪንግን ግድያ ተከትሎ በርካታ የመብት ተሟጋቾች ፈርተዋል።
"የእሱ ሥራዎች ሁሌም ሕያው ሆነው ይቆያሉ። ማኅበራዊ ፍትሕን ለማስፈን ምን አይነት ተቃውሞና ኅብረት መታየት እንዳለበት አሳይቶናል" ይላሉ ፕሮፌሰር ቤንቶ።
የማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግሮች በሰው ልጆች ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በርካቶችን ካበረታቱ እና ለተሻለ ለውጥ ካነሳሱ ንግግሮች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው።
ለሰዎች አኩልነት ድምጹን ማሰማት አቁሞ የማያውቀው ማርቲን ሉተር ኪንግ ሁሌም የግል ደኅንነቱን ትልቅ አደጋ ላይ ጥሎ ነው ለዴሞክራሲ የታገለው።












