አሜሪካውያን የመብት ታጋዩን ጆን ሊውስ ሞት እየዘከሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የቀድሞ መሪዎችና የተለያዩ አገራት መሪዎች ከሰሞኑ አገሪቱ ያጣቻቸውን ቁንጮ የመብት ታጋዩን ጆን ሊውስን እየዘከሩ ነው።
በጣፊያ ካንሰር በ80 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈው የመብት ታጋይ በጎርጎሳውያኑ 1960ዎቹ ላይ ለነፃነት የሚደረጉ ተቃውሞዎችን ካስተባበሩና ከመሩት መካከል አንዱ ናቸው።
እሳቸውን ጨምሮ ማርቲን ሉተር ኪንግ የተካተተቱበት "ስድስቱ ታላላቅ" በመባል የሚታወቁ ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 1963 ላይ በዋሽንግተን የተደረገውን ታሪካዊውን የነፃነት ሰልፍም አስተባብረዋል፤ መርተዋል።
በ60ዎቹና 70ዎቹ ጥቁር አሜሪካውያን ነፃነታቸውን እንዲጎናፀፉ በከፍተኛ ሁኔታ አስተዋፅኦ ያደረጉት የመብት ታጋዩ በኋላም ጆርጂያን በመወከል የምክር ቤት አባል ሆነውም አገልግለዋል።
በባለፈው አመት ጆን ሊውስ የካንሰር ህመማቸው ወደከፋ ደረጃ መድረሱን አስታውቀው ነበር።
"ህይወቴን በሙሉ ለነፃነት፣ እኩልነትና መሰረታዊ ለሚባሉ ሰብዓዊ መብቶች ታግያለሁ። እንዲህ አሁን እንደገጠመኝ ትግል ግን ፈተና የሆነብኝ የለም" በማለትም በወቅቱ ተናግረው ነበር።
ጥቁር አሜሪካውያን በከፍተኛ ሁኔታ ለነፃነት በሚያደርጉት ትግል ሰላማዊ የተማሪዎች እንቅስቃሴን መስርተዋል እንዲሁም ሊቀ መንበርም ሆነው ለሶስት አመታት አገልግለዋል።
ታሪካዊው 'አይ ሃቭ ኤ ድሪም' (ህልም አለኝ) የሚለውን የማርቲን ሉተር ኪንግ የተናገረበት የተቃውሞ ሰልፍን ካስተባበሩትና ከመሩት ሰዎች መካከል ጆን ሊውስ አንዱ ናቸው።
በወቅቱም ጥቁር አሜሪካውያን ላይ የተጫነውን መዋቅራዊ ዘረኝነት፣ ስራ አጥነትና ለነፃነት የሚደረገውንም ትግል በተመለከተም ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ መሪ ባራክ ኦባማ የሰሯቸውን ስራዎች በመናገር ታላቅነታቸውን እንዲሁም ያስቀመጡትን አሻራ ዘክረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የወቅቱ የአሜሪካ መሪ ዶናልድ ትራምፕም በጆን ሊውሰ ሞት ማዘናቸውን ገልጸፀዋል።
ሰንደቅ አላማ ዝቅ ተደርጎ እንዲውለበለብ የተደረገ ሲሆን ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስም "አሜሪካን በቆራጥነት ያገለገለ ፅኑና ደፋር ሰው አጣን" ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ታጋዮች እንዲሁ በጆን ሊውስ ሞት የተሰማቸውን መሪር ሃዘን ገልፀዋል።
"የአርበኝነትና በድፍረት የመታገል ተምሳሌት ነው" ያሉት የመብት ታጋዩ ቄስ ጄሲ ጃክሰን ሲሆኑ ለመጀመሪያ ጊዜም የተዋወቁት በ1960ዎቹ በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች አብረው በመታገል ነው።
የማርቲን ሉተር ኪንግ ትልቅ ልጅም ለሲኤንኤን እንደተናገረው "በዚህ ታሪካዊ የመብት ትግል ውስጥ ታላቅነትን ከተጎናፀፉ መካከል ጆን ሊውስ አንዱ ነው። በሰራው ስራ ታላቅነት ምን እንደሆነ አሳይቶናል" ብሏል።
የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የውጭ አገራት መሪዎችም በመብት ታጋዩ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአላባማ የሚገኝ አንድ ድልድይ በስማቸው እንዲጠራም ከ40 ሺህ በላይ ፊርማ ተሰባስቧል።
ይህ ድልድይ በጎርጎሳውያኑ 1965 ላይ ጆን ሊውስና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ወደ ሞንቶጎመሪ ለመሄድ የተላለፉበት ነው።
በወቅቱም የአሜሪካ ፖሊሶች ጆን ሊውስ የደበደባቸው ሲሆን ጭንቅላታቸውም ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸዋል። ከሳቸውም በተጨማሪ በርካቶች በመገደላቸው እለቷ "ደመኛዋ እሁድ" ትባለላለች።












