ኤዲኤችዲ ምንድን ነው? ይህ ችግር ያለባቸው ሕፃናት ምን ዓይነት ምልክት ያሳያሉ?

የተለያዩ የአእምሮ ክፍሎችን የሚያሳይ ገላጭ ምስል

በእንግሊዝ የኤዲኤችዲ መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ ሆኗል። የሀገሪቱ የጤና አገልግሎት ሰዎችን ለማከም እጁን ከአቅሙ በላይ እየዘረጋ እንደሆነ ይናገራል።

ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ የኤዲኤችዲ መድኃኒት የሚወስዱ እንግሊዛዊያን ቁጥር ሶስት እጥፍ አድጓል። የቢቢሲ ጥናት እንደሚጠቁመው ደግሞ መድኃኒት ለማግኘት የተመዘገቡ ሰዎችን ለማዳረስ ስምንት ዓመት ሊወስድ ይችላል።

ባለፈው ዓመት ብሔራዊው የጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ድረ-ገፅ ላይ ብዙ ሰዎች የጎበኙት ርዕስ ኤዲኤችዲ ነበር። ይህ ያሰጋው ኤንኤችኤስ አንድ ራሱን የቻለ ክፍል አቋቁሟል።

ይህ ቁጥር እየጨመረ የመጣው ለምንድነው? ኤዲኤችዲ ምንድን ነው?

በዚህ ቁጥር መጨመር ታካሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የጤና ባለሙያዎችም ተደናግጠዋል። በእንገሊዝ እንኳ ይህ ሁኔታ እውቅና ያገኛው ከ16 ዓመታት በፊት ነው።

ኤዲኤችዲ በእንግሊዝኛው ፍቺው አቴንሽን ዴፊሲት ሃይፐርአክቲቭ ዲስኦርደር ነው። እኩያ የአማርኛ ፍቺ ትኩረት የማጣት እና የመረጋጋት ችግር ነው ይላሉ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስ ዶ/ር ሄኖክ ዘውዱ።

ዶ/ር ሄኖክ ሐኪም በተሰኘው የፌስቡክ ገፅ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ እክል በተለይ ልጆች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ

“አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ከሌሎች በተለየ ትዕግስት የለሽ ፣ ቀዥቃዣና አስቸጋሪ ሆነውባቸው መፍትሔ ሲፈልጉ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ህፃናት የሚይዙት የሚጨብጡት የሚጠፋባቸው ፣ አንድ ነገር ጀምረው አፍታም ሳይቆዩ ሌላ የሚያምራቸው ፣ ለመናገርና ለመጠበቅ ትዕግስት የማይኖራቸውና ችኩል ናቸው” ሲሉ የኤዲኤችዲን መለያዎች በፅሑፋቸው ያስረዳሉ።

በዶ/ር ሄኖክ ትንታኔ መሠረት “ይህ ትኩረት ማጣት እና ትዕግስት አልባ መሆን የሕፃናትን የትምህርት አቀባበልና አረዳዳቸውን በእጅጉ ይጎዳዋል።”

ዶ/ር ሙለር ሴድግዊክ በዩናይትድ ኪንግደም ኤዲኤችዲ ያለባቸው አዋቂዎች ቁጥር ከጠቅላላው ሕዝብ 3 ወይም 4 በመቶ ይሆናል ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ዶ/ር ሄኖክ በተለይ በሕፃናት ላይ የሚታዩ የኤዲኤችዲ ምልክቶችን እንዲህ ይዘረዝራሉ። አንድ ነገር ጀምረው ለመጨረስ መቸገር፣ ትምህርት ላይ ግዴለሽ መሆንና ቀላል ስኅተት መፈፀም፣ የማዳመጥ እና ትዕዛዝ የመቀበል ችግር፣ ትዕግስት ማጣት፣ መዘንጋት፣ እረፍት አልባ መሆን፣ በቀላሉ መበሳጨት እና መናደድ።

ለኤዲኤችዲ ጥቅም ላይ ከሚውሉ መድኃኒቶች መካከል አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ይህ ችግር አለብን ብለው ወደ ሆስፒታል እየመጡ የሚመረመሩ ሰዎች ቁጥር ከፍ በማለቱ ነው።

የሕፃናት እና አዋቂዎች የሥነ-ልቡና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሚሊ ሲሞኖፍ ደግሞ በዩኬ ካሉ ሕፃናት ከ5-7 በመቶው ይህ የአእምሮ እክል እንዳለባቸው ይገላፃሉ።

አክለው ይህ ቁጥር በዩኬ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሀገራት ተመሳሳይ እንደሆነ በማስረዳት በተለይ ከኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ በኋላ ከፍ እያለ እንደሆነ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰሯ እንደሚሉት በዩናይትድ ኪንግደም ከ3-4 በመቶ ሕፃናት መድኃኒት ቢያስፈልጋቸውም መድኃኒት እያገኙ ያሉት ግን ከ1-2 በመቶው ናቸው ይላሉ።

ቲያ ስታይን የዘርፉ ባለሙያ ሲሆኑ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ሰዎች ስለእከሉ ያላቸው ግንዛቤ እየጨመረ በመምጣቱን ለመመርመር ፈቃደኛ በመሆናቸው መሆኑን ነው የሚገልፁት።

እሳቸው ተስፋ እንደሚያደርጉት ከሆነ በለተይ ወደፊት ማኅበረሰቡ ግንዛቤው እያደገ ሲመጣ ሕፃናትን በጊዜ ማስመርመር ይጀምራል። ይህ ደግሞ ልጆች በልጅነታቸው እርዳታ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል።

እርግጥ ነው ኤዲኤችዲ የሚለው ስያሜ የቅርብ ጊዜ ሊሆን ይችላል። ትኩረት ማጣት ግን ከሰዎች ጋር የኖረ ጥንታዊ ችግር ነው። በ1798 ስኮትላንዳዊው ዶክተር አሌክሳንደር ክሪችቶን “የትኩረት በሽታ” ሲሉ ፅፈው ነበር።

ኤዲኤችዲ ግን ትኩረት ማጣት አሊያም ከልክ በላይ ንቁ መሆን ብቻ አይደለም። ይህ እክል ያለባቸው ሰዎች ስሜታቸውን መቆጣጠር ሊሳናቸው ይችላል። የዚህ ተጠቂ ሰዎች ለዕፅ ሊዳረጉ እና የገንዘብ ችግር ውስጥ ሊገቡ አልፎም ወንጀል የመፈፀም እና የመኪና አደጋ የማጋጠም ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ዶ/ር ሄኖክን ጨምሮ ሁሉም የጤና ሙያተኞች የሚስማሙበት አንድ ጉዳይ ቢኖር ኤዲኤችዲን በጊዜ ተመርምሮ ሕክምና ማገኘት በጣም ጠቃሚ ነው።

አሁን ለኤዲኤችዲ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የሕክምና መንገዶች መድኃኒት እና ቴራፒ ናቸው። ነገር ግን ሌሎችም አማራጮች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።

በዩናይትድ ስቴትስ ሕፃናት ሲተኙ ጭንቅላታቸው ላይ የሚያጠልቁት መሣሪያ ገበያ ላይ ውሏል። ይህ መሣሪያ ዩኬ ውስጥ ጥቅም ላይ ባይውልም ሙከራ እየተደረገበት ይገኛል።