የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ የሚውለው 'ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ' ጠቃሚ ወይስ ጎጂ?

የፎቶው ባለመብት, The San Francisco Chronicle via Getty Images
የሰውነትን ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል በቀን ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ምግብ ሳይበሉ የሚቆይበት 'ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ'፤ያለፈው አስር ዓመት ዝነኛ የአመጋገብ ስርዓት ሆኗል።
በዚህ ዘዴ፤ምን አይት ምግቦችን መመገብ አለብኝ የሚለው ሳያስጨንቅዎት፤ በቀላሉ ምግብ የሚወስዱበትን ሰዓት በመቀየር ብቻ ሰውነትዎን ማስተካከል እንደሚችሉ ይነገራል።
ታዋቂ የቴክኖሎጂ ባለሀብቶች 'ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ' እንደጠቀማቸው ምለው ይገዘታሉ። የሆሊዉድ ኮከቦች በዚህ ዘዴ የተነሳ ወገባቸው ችቦ ሳይሞላ መቆየቱን ያስረዳሉ። የብሪታንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ጭምር በአንድ ወቅት በሳምንት 36 ሰዓት ለመጾም ማሰባቸውን ሲናገሩ ተደምጠው ነበር።
እስካሁን ድረስ ሳይንስ ይህንን ዘዴ የሚደግፈው ይመስላል።ጥናቶች፤ምግብ ሳይወሰድ የሚቆይበትን እንደ ሌሊት ያለ ጊዜን ማራዘም ወደ ሰውነት የገባው ምግብ ወደ ኃይል የሚቀየርበትን ስርዓት (ሜታቦሊዝም) ሊያሻሽል፣ህዋሳት ራሳቸውን የሚጠግኑበትን ሂደት ሊረዳ እና ምናልባትም ዕድሜንም ጭምር ሊያራዝም እንደሚችል ያመለክታሉ።
የስነ ምግብ ባለሙያዎች ግን ምግብ ሳይወስዱ መቆየት አንዳች ተዓምራዊ ለውጥ የሚያመጣ ዘዴ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ስር የሰደደ ሕመም ላለባቸው ሰዎች አደገኛ ሊሆን እንደሚችልም ለረጅም ጊዜ ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል።
ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ፤ ምግብ የሚወስዱበትን ጊዜ የሚያራዝሙበት ዘዴ ነው።
አብዛኛውም ጊዜም በየስምንት ሰዓቱ እንዲመገቡ የሚመከር ሲሆን ይህ አካሄድም በቀን ውስጥ ለ16 ሰዓታት ያህል ምግብ ሳይወስዱ እንዲቆዩ ማድረግን ያካትታል።
በጉዳዩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ መጠነ ሰፊ ጥናት ግን ይህንን የአመጋገብ ስርዓት መከተል ሊያስከትል የሚችላቸውን አሳሳቢ ጉዳቶች ዘርዝሯል።
ከ19,000 በላይ ከሆኑ አዋቂ ሰዎች የሰበሰቡትን መረጃ የተነተኑት ተመራማሪዎች፤ በቀን ውስጥ ምግብ የሚመገቡበት ጊዜ ከስምንት ሰዓት በታች የሆነ ሰዎች በቀን ውስጥ ከ12 እስከ 14 ሰዓት ለሚደርስ ጊዜ ከሚመገቡ ሰዎች በበለጠ ለጤና ችግር እንደሚጋለጡ ደርሰውበታል።
ምግብ የሚያገኙበትን ሰዓት ከ8 ሰዓት በታች ያደረጉ ሰዎች፤ ከልብ እና ከደም ቧንቧ ጋር በተያያዙ በሽታዎች ሕይወታቸው የማለፍ እድሉ 135 በመቶ እንደሚጨምር የተመራማሪዎቹ ግኝት አሳይቷል።
ከፍ ያለ የልብና የደም ቧንቧ አደጋ ማለት በግለሰቡ ጤና፣ በአኗኗር ዘይቤ እና በሕክምና መረጃ ላይ በመመርኮዝ በጥናቱ ውስጥ ከሌሎቹ ይልቅ እንደ የልብ ድካም ወይም እንደ ስትሮክ ያሉ ከልብ ጋር የተዛመዱ ችግሮችን የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ከሌሎች በተለየ እንደ ልብ ድካም እና ስትሮክ ባሉ በሽታዎች የመጠቃት እድላቸውም ከፍ ያለ መሆኑንም ጥናቱ አመልክቷል።
የተመራማሪዎቹ ጥናት በቀን ውስጥ ለትንሽ ሰዓታት ብቻ መመገብ ለሞት ይዳርግ እንደሆን ባደረጉት ምርመራ ያገኙት ውጤት ጠንካራ እና ወጥ ያልሆነ ነው። ነገር ግን ይህንን ዘዴ በሚጠቀሙ በየትኛውም እድሜ፣ጾታ እና የሕይወት ዘይቤ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከልብ ጋር በተያያዙ በሽታዎች የመጠቃት እድላቸው ከፍ እንደሚል ጥናቱ በተደጋጋሚ አሳይቷል።
ተመራማሪዎቹ፤ ጥናቱ መንስኤ እና ውጤት እንደማያረጋግጥ አጽንኦት ሰጥተዋል። ነገር ግን በጥናቱ ውጤት የታየው ምልክት፤ 'ኢንተርሚነተንት ፋስቲንግ ወደ የተሻለ ጤንነት የሚያደርስ አደጋ ነጻ ዘዴ ነው' የሚለውን አመለካከት ለመፈተን በቂ ማሳያ ነው።
አጥኚዎቹ ለስምንት ዓመታት አሜሪካውያን አዋዊ ሰዎችን ሲከታተሉ ቆይተዋል። የአመጋገብ ልምዶቻቸውን ለመረዳት እንዲያስችልም፤በሁለት ሳምንት ልዩነት ውስጥ በተለያዩ ሁለት ቀናት የበሉትን እና የጠጡትን በሙሉ እንዲያስታውሱ ተጠይቀዋል።
ተመራማሪዎቹ ከያዟቸው "የአመጋገብ ማስታወሻዎች" በመነሳት እያንዳንዱን ሰው አማካይ የመመገቢያ ሰዓት በመገመት፤የረጅም ጊዜ ልማዳቸውን ለመረዳት እንደ ወካይ መረጃ ተጠቅመውበታል።
ጥናቱ እንዳመለከተው፤ በቀን ውስጥ ምግብ የሚያገኙት ለስምንት ሰዓት ብቻ የሆነ ሰዎች በቀን ውስጥ ከ12 እስከ 14 ሰዓት በላይ ለሆነ ጊዜ ምግብ የሚወስዱ ሰዎች በበለጠ በልብ እና በደም ቧንቧ በሽታ የመሞት ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸዋል።
በተለይም ሲጋራ በሚያጨሱ፣ በስኳር በሽታ በተጠቁ ወይም ቀድሞውኑ የልብ በሽታ ባለባቸው ሰዎች ላይ ይህ አደጋ እንደሚጨምርም ደርሰውበታል።
በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፤ የአመጋገባቸውን ጥራት እንዲሁም ምግብ የሚወስዱበትን ጊዜ ድግምግሞች እና ሌሎች ምክንያት የሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎችን ከተስተካከሉ በኋላም እንኳ ለዚህ አደጋ የመጋለጥ እድል ፀንቶ መቆየቱን ተመራማሪዎቹ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images
የአመጋገብ ስርዓት የስኳር በሽታ እና የልብ ሕመም ዋነኛ መንስኤ በመሆኑ ከልብ እና የደም ቧንቧ ጋር በሽታ ሞት ጋር መያያዙ ያልተጠበቀ ነገር እንዳልሆነ የጥናቱ ዋና ጸሐፊ ቪክቶር ዌንዜ ዦንግ ያስረዳሉ።
ተመራማሪዎቹ ያልጠበቁት ግን ሰዎች የሚወስዱት ምግብ ብቻ ሳይሆን የሚመገቡበት ሰዓት ማጠር በልብ እና የደም ቧንቧ በሽታ የመሞት ዕድልን ከፍ ማድረጉ እንደሆነ በቻይና የሻንጋይ ጂያኦ ቶንግ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ዦንግ ተናግረዋል።
ይህ ግኝት ከዚህ ቀደም ከጥቂት ወራት እስከ አንድ ዓመት ብቻ በቆዩ የአጭር ጊዜ ጥናቶች ሲደገፍ የነበረውን በጊዜ የተገደበ አመጋገብ የልብና የሜታቦሊክ ጤናን ያሻሽላል የሚል እምነት የሚቃረን እንደሆነ አክለዋል።
ከዚሁ ጥናት ጋር የተያያዘ ጽሑፍ ያሳተሙት የኢንዶክሪኖሎጂ ባለሙያው አኑፕ ሚስራ ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እና የሚያስከትላቸውን አደጋዎች ይገልጻሉ።
እንደ ባለሙያው ገለጻ በርካታ የጥናት ሙከራዎች እና ትንታኔዎች ይህ ዘዴ ክብደትን ለመቀነስ፣ የሰውነት የኢንሱሊን አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የደም ግፊትን ለመቀነስ እንደሚረዳ እንደ ደረሱበት አስታውሰዋል።
በተጨማሪም ሰዎች ያለ በጥብቅ መንገድ ወደ ሰውነታቸው የሚገባውን ካሎሪ ሳይቆጣጠሩ በደም ውስጥ የሚኖረውን ስኳር እንዲቆጣጠሩ ሊረዳቸው እንደሚችል እንዲሁም ከባህላዊ ወይም ከሃይማኖታዊ የጾም ልምዶች ጋር በቀላሉ እንደሚጣጣም እና ልምድ ለማድረግ ቀላል መሆኑን ያነሳሉ።
ፕሮፌሰር ሚስራ፤ "ሊያስከትል የሚችላቸው ጉዳቶች በአንጻሩ የምግብ እጥረት፣ የኮሌስትሮል መጠን መጨመር፣ ከልክ ያለፈ ረሃብ፣ የመበሳጨት ስሜት፣ በቶሎ መቆጣት፣ ራስ ምታት እና ከጊዜ በኋላ የአካል ብቃት መቀነስ ናቸው" ሲሉ የዘዴውን ሌላኛውን ገጽ ዘርዝረዋል።
"የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች በአግባቡ ክትትል ያልተደረገበት ጾም ውስጥ ሲገቡ የደም ስኳር መጠን አደገኛ በሆነ መጠን እንዲቀንስ ሊያደርግ ይችላል፤እንዲሁም በሚመገቡበት ወቅት ጤናማ ያልሆኑ ምግቦችን እንዲመገቡ ያበረታታቸዋል። በዕድሜ የገፉ አዋቂዎች ወይም ስር የሰደደ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ መጾማቸው የጡንቻ ድካም ሊያባብስ ወይም የጡንቻ መጎዳትን ሊያፋጥን ይችላል" ሲሉም አክለዋል።
ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ ከበድ ያለ ትችት ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
በ2020 'ጃማ ኢንተርናል ሚዲስን' በተባለው የምርም መጽሔት ላይ በታተመ የሦስት ወራት ጥብቅ ጥናት ላይ የተሳተፉ ሰዎች በዚህ ዘዴ መቀነስ የቻሉት የሰውነት ክብደት መጠን አነስተኛ መሆኑን አረጋግጦ ነበር። አብዛኛው ክብደት የቀነሰውም ከጡንቻዎች ሊሆን እንደሚችልም ጥናቱ ጠቁሞ ነበር።
ሌላ ጥናት ደግሞ ኢንተርሚተንት ፋስቲንግ እንደ ድካም፣ ረሃብ፣መጠማት፣ራስ ምታት እና ትኩረት የማድረግ ችግር ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል አሳይቷል።
ፕሮፌሰር ሚስራ፤ አዲሱ ጥናት፤ ይህ ዘዴ ከፍ ያለ የልብ እና የደም ቧንቧ አደጋ እንደሚያስከትል ማሳየቱን በመጥቀስ አዲስ የበለጠ አሳሳቢ ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሰዎች ከዚህ ጥናት ግኝት ምን ድምዳሜ ቢወስዱ ጥሩ ነው ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር ዦንግ፤ የልብ ሕመም ወይም የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች በቀን ለስምንት ሰዓት ብቻ የመመገብ ልምድን ሲተገብሩ መጠንቀቅ አለባቸው ብለዋል።
ግኝቶቹ የጤና ሁኔታን እና በተለዋዋጭ ማስረጃዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ "የግል" የአመጋገብ ምክር አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያሳዩም አንስተዋል።
"በአሁኑ ሰዓት የተገኙት ማስረጃዎች ሰዎች ምግብ የሚወስዱበት ጊዜ ላይ ከማተኮር ይልቅ ለሚመገቡት ምግብ ትኩረት መስጠታቸው አስፈላጊ መሆኑን የሚያመላክቱ ይመስላል" ሲሉም ያስረዳሉ።
አዲሱ ግኝት የሚያመለክተው ሙሉ በሙሉ ስለ ጾምን ሙሉ በሙሉ መተውን ሳይሆን እያንዳንዱ ግለሰብ ካለበት የጤና ስጋት ጋር እንዲስማማ መደረግ አለበት የሚለውን ነው።
ይህንን ዘዴ የተመለከቱ ማስረጃዎች ይበልጥ ግልጽ እስከሚሆኑ ድረስ አስተማማኙ አካሄድ፤ ከምግብ ሰዓቱ ይልቅ እና የምግብ ሳህኑ ላይ ምን አለ የሚለው ላይ ማተኮር ሊሆን ይችላል።















