ሴሪና ዊልያምስ በመድኃኒት እገዛ ክብደት መቀነሷ ከውፍረት መድኃኒት ጋር የተያያዘ መጥፎ ዕይታን ይቀይር ይሆን?

ሴሪና ዊልያምስ

የፎቶው ባለመብት, XNY/Star Max/Getty Images

በዓለማችን ምርጥ ከሚባሉ አትሌቶች አንዷ የሆነችው ሴሪና ዊልያምሰ ክብደት ለመቀነስ በመድኃኒት መታገዟን ከሰሞኑ አስታውቃለች።

አትሌቷ መድኃኒት የመጠቀሟን ጉዳይ ለመናገር የፈለገችውም ውፍረት ለመቀነስ ከሚሰጡ መድኃኒቶች ጋር የተያያዙ መጥፎ አመለካከቶችን ለመቀየር ነው ብላለች።

ሴሬና በግልጽ እንዲህ መናገሯ መድኃኒቱን እየተጠቀሙ ላሉ ሰዎች የመተማመን ስሜታቸውን ያዳብረው ይሆን? በእሷ ላይ የሚሰጡ ትችቶችንስ ዝም ያሰኛቸው ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች መንሸራሸራቸው አልቀረም።

የ43 ዓመቷ ሴሪና ዊልያምስ የምንጊዜንም የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ናት።

በርካታ ክብረ ወሰኖችን በመስበር፤ 23 ጊዜ የታላቁ የቴኒስ ውድድር ሻምፒዮን በመሆን ዓለማችን ካፈራቻቻው ታላላቅ አትሌቶች አንዷ በመሆን ታሪክ መዝግቧታል።

ሴሪና የጽናት፣ የአካል ብቃት እንዲሁም የአትሌትነት ብቃት መገለጫ መሆኗን በርካቶች ይመሰክሩላታል።

ሆኖም ልጆች ከወለደች በኋላ የጨመረችውን ክብደቷን ለመቀነስ እንደ ሌሎች መታገሏን አምናለች።

በስተመጨረሻም ሴሪና ይህንን የጨመረችውን ክብደት እንደ "ተፎካካሪዋ" ለማየት ውሳኔ ላይ መድረሷን 'ቱደይ ሾው' ለተሰኘው የአሜሪካ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ተናግራለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ክብደቷን ለመቀነስ "በሩጫ፣ በሶምሶማ፣ ብስክሌት በመጋለብ፣ ደረጃ በመውጣት" በየዕለቱ ለአምስት ሰዓታት ልምምድ ብታደርግም፤ ክብደቷን እንደ ተፎካካሪዎቿ መርታት አልቻለችም።

ይህንን ሁሉ አድርጋ ክብደት መቀነስ የተሳናት ሴሪና "የተለየ ነገር ከመሞከር" በስተቀር ሌላ አማራጭ "አልነበረኝም" ብላለች።

በርካታ ጓደኞቿ ክብደታቸውን ለመቀነስ ውፍረትን ለመቀነስ የሚረዱ የተለያዩ መድኃኒቶችን የያዘው በጥቅል ስሙ ጂኤልፒ- 1 የተሰኘውን መድኃኒት የሚወስዱ ሲሆን ይህንኑ ለመሞከር ወሰነች።

ሴሪና ጂኤልፒ-1 ከተሰኙት መድኃኒቶች የትኛውን እንደምትወስድ ግልጽ ባታደርግም መድኃኒት መውሰድ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም ትላለች።

ባለፉት ስምንት ወራት 14 ኪሎ የቀነሰችው ሴሪና መድኃኒት "አቋራጭ መንገድ" አይደለም ስትል ታስረዳለች።

የቴኒስ ኮከቧ መድኃኒት እየተጠቀመች ስለመሆኑ በግልጽ ለማውራት ይህንን ጊዜ ለምን መረጠች? የሚለው ላይ አንዳንድ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው አልቀረም።

ይህ ጥርጣሬ መነሻውም ጂኤልፒ-1 በሚባል ጥቅል የምርት ስም የውፍረት መቀነሻ መድኃኒቶች የሆኑት ዌጎቪ፣ ዜፕባውንድን (ወይም በዩኬ አጠራሩ ሞንጃርኖ) ለሚያመርተው ሮ ለተሰኘው ኩባንያ ሴሪና በቅርቡ ቃለ አቀባይ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ነው።

ባለቤቷም በኩባንያው አንድ ባለሃብት (ኢንቨስተር) ነው።

መድኃኒቶቹ የሚያስከትሉት የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉ ሆነው አትሌቷ መድኃኒት ስለመጠቀሟ በግልጽ መናገሯ ማወዛገቡ አልቀረም።

በርካታ ሴቶች ውፍረት ለመቀነስ ይህንን መድኃኒት በመጠቀማቸው የሚሰማቸውን እፍረት ለመቅረፍ እየሞከረች መሆኗንም አትሌቷ አስረድታለች።

እንደ ሴሪና ዊልያምስ ያለ ታላቅ አትሌት በመድኃኒት ዙሪያ በግልጽ መናገር እንደ "ታላቅ እመርታ" ሊታይ እንደሚገባ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሰቲ የፌሚኒስት ጥናቶች ረዳት ፕሮፌሰር ካሌብ ሉና ያስረዳሉ።

ክብደት ለመቀነስ መድኃኒት በመጠቀም "ቀላሉን መንገድ እየመረጡ" ነው ለሚሉ ተቺዎችም ሆነ እንዴት ተቀነሰ? ብለው ጥያቄ የሚያነሱትንም ዝም ለማሰኘት የሚረዳ እንደሆነ ምሁሩ ይናገራሉ።

"እነዚህን መድኃኒቶች መጠቀም የሚገባቸው ሰነፍ እና ብቃት የሌላቸው ወፍራም ሰዎች ናቸው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ያስወግዳል" የሚሉት ምሁሩ በዚህ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው አጽንኦት ይሰጣሉ።

ሆኖም ካሌብ እንደሚሉት ጂኤልፒ-1 የተሰኙትን መድኃኒቶች ለመጠቀም መምረጧ "አስፈሪ እና የሚያሳዝን ነው" ይላሉ። አትሌቷ ከጥንካሬዋ እና ከብርታቷ በላቀ መንገድ ውጫዊ ገጽታዋ ላይ ማተኮሯን የሚያመላክት ዕይታን የሚሰጥ ነው ይላሉ።

ሴሪና "በታሪካችንም ሆነ በቀደምቱ ጥቂቶች ብቻ መድረስ የሚችሉት ስኬቶችን ተጎናጽፋለች። እነዚህ ሁሉ ስኬቶች በሰውነት መጠን እየተሸፈኑ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ ክብደት እነዚህ ሁሉ ክብረ ወሰኖችን ከመስበር ስኬቶች ሁሉ የላቀ ይመስላል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሴሪና ዊልያምስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ጤናማ ክብደት"

በርካታ ጥቁሮች በማይደፍሩት የሜዳ ቴኒስ ታላቅነቷን ያስመሰከረችው ሴሪና ከመልኳ እና ከክብደቷ ጋር ተያይዞ በርካታ ሚዲያዎች ሲነቅፏት ታይተዋል።

በዓለማችን ታላቅ ከሚባሉ አትሌቶች አንዷ ብትሆንም ከሰውነት አቋሟ ጋር ተያይዞ ይመጡ የነበሩ አስተያየቶች ጫናቸው ከባድ ነበር።

ምንም እንኳን ክብደት ለመቀነስ በመድኃኒት መታገዟን በግልጽ የተናገረች ስመ ጥር አትሌት ብትሆንም ከዚህ ቀደም መድኃኒት ስለመጠቀማቸው የተናገሩ ታዋቂ ሰዎቸ አሉ።

ኦፕራ ዊንፍሬይ ጂኤልፒ-1 መድኃኒትን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ከጤናማ አመጋገብ ጋር በማጣመር ክብደት ላለመጨመር እንደምትጠቀም ተናግራለች።

ሌላኛዋ አሜሪካዊት ተዋናይት ውፒ ጎልድበርግ በመድኃኒት "የሁለት ሰዎችን ክብደት" ያህል እንደቀነሰች ተናግራለች።

ታዋቂዋ ሙዚቀኛ ኬሊ ክላርክሰንን ጨምሮ በርካታ ታዋቂዎች ውፍረት ለመቀነስ መድኃኒት ይወስዳሉ።

ሴሪና የሜዳ ቴኒስ ዓለምን ከሦስት ዓመት በፊት የተሰናበተች ብትሆንም አሁንም ድረስ የጥንካሬ ተምሳሌት ናት።

ሁለተኛ ልጇን አዲናን ከወለደች በኋላ ወደ "ጤናማ ክብደቷ" ለመመለስ እንደምትፈልግ ከዚህ ቀደም ተናግራ ነበር።

አትሌቷ ከቱደይ ሾው ጋር በነበራት ቆይታ "ሰውነቷ የሆነ የጎደለው ነገር እንዳለ" እንደተሰማትና በቀን ለበርካታ ሰዓታት ከፍተኛ ልምምድ ብታደርግም ምቾት በሚሰማት ሁኔታ ክብደቷን ለመቀነስ እንዳልቻለች ገልጻለች።

በዩኬ ሎውቦሮው ዩኒቨርስቲ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ፣ የጤና ሳይንስ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ክሌይር ማዲጋን የላቁ አትሌቶች ክብደታቸውን ለመቀነስ እንደሚቸገሩ ያስረዳሉ።

"በምግባቸው ከፍተኛ ካሎሪዎችን መመገብ ለምደው ከስፖርቱ ሲወጡ ይከብዳቸዋል፤ የባህርይ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ ተመራማሪዋ ይመክራሉ።

ዶክተሯ እንደሚሉት ሴሪና ለክብደቷ መቀነስ መድኃኒት ብቻ ሳይሆን "አመጋገቧ እና አካላዊ እንቅሰቃሴ" አስፈላጊ መሆኑን መናገሯ ጥሩ ነው ይላሉ።

አክለውም "ልጅ ከወለደች በኋላ ክብደት መቀነስ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መናገሯ በጣም ጠቃሚ እንደሆነም" ያስረዳሉ።

ሆኖም የሴሪና መልዕክት አንዳንድ ሴቶችን ከማበረታት ይልቅ ተቃራኒው ሊሆን ይችል እንደሆነ ይጠይቃሉ።

"መድኃኒቶቹ በጣም ውድ ናቸው፤ በተጨማሪም አንድ ተራ ሰው ይህች የላቀች አትሌት ጂም እየሠራች፣ በሥነ ምግብ ባለሙያ ታግዛ፣ ጊዜ ኖሯት እነዚህን መድኃኒቶች ተጠቀመች ብሎ ሊያስብ ይችላል" ይላሉ።

ዶክተር ማዲጋን ሌላኛው የሚጠቅሱት ከመድኃኒቶቹ ጋር ተያይዘው ያሉ የጎንዮሽ ጉዳቶች የጨጓራ እና የአንጀት ችግሮችን ሊያስከትሉ የሚችሉ እንደ ማስታወክ፣ ተቅማጥ እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የሐሞት ከረጢት እና የኩላሊት ችግሮች አትሌቷ መድኃኒቱን ከመጠቀሟ ጋር ተያይዞ አለመነሳታቸው ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

ሴሪና ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላጋጠማት ለአንድ የሴቶች የጤና መጽሔት ተናግራ በጂም ውስጥ እያደረገችው ያለውን ልፋቷ ውጤት አፍርቷል ብላለች።

"መገጣጠሚያዎቼ የተሻለ ሁኔታ ላይ ናቸው። አሁን ሁሉንም ምርመራ አድርጌ ዶክተሬ የደም ስኳር መጠንን ጨምሮ ሁሉ ነገር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ነግሮኛል" ስትል አስረድታለች።

በሜዳ ቴኒስ ላይ ክብረ ወሰኖችን ባትሰብርም በመድኃኒት እገዛ ክብደት በመቀነሷ በግል ሕይወቷ ክብረ ወሰኖችን መስበሯን አስረድታለች።

በአሁኑ ወቅት ለግማሽ ማራቶን ሩጫ በመሠልጠን ላይም ትገኛለች።

"ከመቼውም ጊዜ በላይ ያልሸፈንኩትን ርቀት እየሮጥኩ ነው" ብላለች አትሌቷ በኩራት።