በግማሽ ጨዋታ ጡት ማጥባት፡ የሴት ስፖርተኞች ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, FIBA
"የተወሰኑ የቡድናችን አባል ነበሩ፤ ግማሽ ጨዋታ ሲሆን ወይ ጡት ለማጥባት ወይም ጡታቸውን ለማለብ ይሄዳሉ። ከዚያም ወደሜዳ ይመለሳሉ" ትላለች አንጎላዊ-አሜሪካዊቷ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ኢታሊ ሉቃስ።
"ይህንን ቀርቦ ማየትም ሆነ በዚህ ማለፍ የሚያስደምም ነው፤ ለየት ያለ ጥንካሬ ያስፈልጋል" በማለት ታስረዳለች።
እናት መሆንና ታዋቂ ለሆነ የቅርጫት ኳስ ቡድን መጫወት እንዲሁም ለሁለቱም የሚሆን ጊዜ ማግኘት ቀላል አይደለም። እናትነትና ስፖርተኝነትን አመጣጥኖ መሄድም ፈታኝ ነው።
በተለይም ሴት ስፖርተኞች በሚያረግዙበት ወቅት እርግዝናው በአካላቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ፣ አሰሪዎች ነፍሰጡር መሆናቸውን በሚያውቁበት ወቅት ሊከተል የሚችለው ጫና እንዲሁም አዲስ ህይወትን ወደ ስፖርቱ ዓለም ማምጣት የራሱ የሆኑ ፈታኝ ችግሮች አሉት።
በዚህም ምክንያት ሴት ስፖርተኞች እናት መሆንን በከፍተኛ ሁኔታ ይፈሩታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 'አፍሮ ባስኬት' ተብሎ በሚጠራው የአፍሪካውያን የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ውድድር በሴኔጋል ሲካሄድ ከ144ቱ ቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች መካከል እናት የሆኑት 25ቱ ብቻ ናቸው። ይህ ቢሰላ አስራ ሁለት ቡድን ከሚይዝ ቡድን ውስጥ እናት የሆኑት ሁለት ብቻ ናቸው እንደማለት ነው።
ምናልባት በስፖርቱ ዓለም ውስጥ እርጉዝ ሆነው ስፖርቱን ከቀጠሉት መካከል የሜዳ ቴኒስ ተጫዋቿ ሴሪና ዊልያምስ ትገኝበታለች። ከሦስት ዓመት በፊትም የዓለም አቀፉን ሻምፒዮና ለ23ኛ ጊዜ ስታሸንፍ ልጇን አሌክሲስ ኦሎምፒያ ኦሃኒያን ነፍሰ ጡር ሆና ነው።
ካሜሮናዊቷ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች ባሌታ ሙኮኮ ነፍሰጡር መሆኗን አታውቅም ነበር፤ እርጉዝ መሆኗን የተረዳችው በጣም ዘግይታ ነው።
ለፈረንሳዩ ቡድን ትጫወት በነበረበት ወቅት አንድ ቀን ጀርባዋን በፀና ታመመችና ወደ ሆስፒታል ሄደች፤ ዶክተሩም የሰባት ወር ነፍሰጡር እንደሆነች ነገራት።
"ዓመቱን በሙሉ ቅርጫት ኳስ ተጫውቻለሁ። መጋፋት መውደቅ እንዲሁም መመታት ነበር። እርጉዝ መሆኔን አላወቅኩም። ልክ መጫወት ሳቆም ሆዴም እየገፋ መምጣት ጀመረ" ትላለች።
አክላም "ልጅ ለመውለድ እንዲሁም ለመታረስ ጊዜው ነበረኝ። የወለድኩት ሰኔ ወር ነበር እናም እስከ ነሐሴ ድረስ ምንም አይነት ጨዋታ አልነበረኝም እናም ለማረፍ ጊዜ አግኝቻለሁ" በማለት ታስረዳለች።
ምንም እንኳን እንደ ሴሪና ባሌታ ወደ ስፖርቱ ዓለም መመለስ ብትችልም፤ ነገር ግን እናት መሆንና ስፖርተኛ መሆን ከፍተኛ መስዋዕትነትን ይጠይቃል።
በባለፈው ዓመት በዓለም አቀፉ ሻምፒዮን ውድድር ላይ የዱላ ቅብብል የወርቅ ሜዳሊያዋን ያገኘችው ሼሊ አን ፍሬዘር ፕራይስ ደስታዋን የገለፀችው ልጇን ዛየንን በውድድሩ ቦታ ላይ በማምጣት ነበር።
በወቅቱም ምን ያህል መስዋዕትነት እንደከፈለች ስትናገር የልጇ ዛየን ትምህርት እንዲሁም ስፖርት ነክ ውድድሮች ላይ መገኘት አለመቻሏን ነው። ምክንያቱም መቋረጥ የማይችሉ ስልጠናዎች ስለነበሯት ነው፤ ይህም በወቅቱ ፈታኝ ነበር ብላለች።
ፅናትና ቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን ታዋቂ አትሌት ለመሆን መስዋዕትነት እንደሚያስፈልግ ባሌታ የተማረችው ነገር ነው።
"የመጀመሪያ ልጄ የሚኖረው ከእናቴ ጋር ነው ምክንያቱም ስፖርቱ አብዛኛውን ጊዜዬን ስለሚወስድብኝ ብዙም አላየውም" የምትለው ባሌታ፤
"የማገኘው በበዓላት ወቅት እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜና እሁድ ብቻ ነው። የሚቀጥለውን ልጄን በምወልድበት ጊዜ ግን ለአንድ ዓመት ቢሆን ስፖርቱን ቀጥ አደርገዋለሁ" በማለት እቅዷን አስረድታለች።
ለሴት ስፖርተኞች በሚወልዱበት ወቅት ሥራ ማቋረጥ ግዴታ ይሆን? ሥራ ማቋረጡስ ለስፖርተኞች ምን አይነት ሁኔታን ያስከትል ይሆን? ቀድሞ ይከፈላቸው የነበረውን የገንዘብ መጠን ከወለዱ በኋላ ያገኙት ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, @AF85
ስድስት ጊዜ በመቶና ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ የኦሊምፒክ ሻምፒዮና መሆን የቻለችው አሊሰን ፌሊክስ፤ እናት መሆኗን ተከትሎ ስፖንሰር የሚያደርጋት ናይክ ይከፍላት ከነበረው 70 በመቶ ቀንሶ ልክፈልሽ እንዳላት ገልፃለች።
ምንም እንኳን ፌሊክስ ናይክ ያደረገውን ኢፍትሃዊነት በማጋለጥና በመሞገት ማሸነፍ ብትችልም ብዙ ሴት ስፖርተኞች ይህ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸው ቢቢሲ ያናገራቸው አትሌቶች ገልፀዋል።
ይህ ብቻ አይደለም ልጅ ከወለዱ በኋላ ከአካላዊ ሁኔታ መቀያየር ጋር ተያይዞ መጫወትም ሆነ መወዳደር ቢከብዳቸውስ? የአይቮሪኮስቷ ቅርጫት ኳስ አምበል ማሪያማ ካዩቴ ይህ ነው ያጋጠማት።
"በውድድር ላይ ተጎድቼ ሁለቱም ጉልበቴ ላይ ቀዶ ጥገና አደረግኩኝ። እናም የመጀመሪያ ጉልበቴን ቀዶ ጥገና ሳደርግ ለምን ልጅ አልወልድም እና ወደ ቅርጫት ኳሱ አልመለስም አልኩኝ። እና አሁን ማለት የምችለው ልጅ በመውለዴ እኮራለሁ" በማለት ጉዞዋን አስረድታለች።
በሴቶች የስፖርት ዓለም ውስጥ እናትነት እንደ አንድ ችግር መታየቱ መቆም አለበት የምትለው የባሌታ አሰልጣኝ ናቶሻ ከሚንግስ፤ ይህም ጥያቄ ሊሆን አይገባም በማለት ትከራከራለች።
"ኮሌጅ ውስጥ ስፖርተኞች የነበሩ ወልደው እንደገና ተመልሰው የሚወዳደሩ ስፖርተኞችን አውቃለሁ" በማለት የቅርጫት ኳስ አሰልጣኟ ናቶሻ አፅንኦት ሰጥታ ትናገራለች።
"ሴት አትሌቶች በእናትነትና በስፖርት ህይወታቸው መካከል እንዲመርጡ መገደድ የለባቸውም። ዋናው ነገር በደንብ ጠንክረው መስራትና ቁርጠኝነትን ማሳየት አለባቸው። ምክንያቱም ለብዙ ሴቶች ከባድ የሚሆነው በእርግዝና ወቅት የሚፈጠረውን አካላዊ ሁኔታ ወደነበረበት መመለስ ነው። ለመጫወት ወደሚያበቃቸው አካላዊ ቅርፅም ሆነ ብቃት መመለስ አለባቸው።"
የምትለው አሰልጣኟ "ቤተሰብ መመስረት ለሚፈልጉትም ምርጫቸው ነው። እኛም እናበረታታቸዋለን ቤተሰብ መመስረት የሚፈልጉትን የአትሌትነት ህይወታቸውን እንዳያቋርጡ የምንጎተጉታቸው ጉዳይ ነው።"
አትሌቶች ልጅ ከወለዱ በኋላ ወደ ስፖርቱ መመለስ ለሚፈልጉትም ሆነ ቤተሰብ መመስረት ለሚሹ ዋናው ጉዳይ ከአሰልጣኞች ዘንድ የሚያገኙት ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አሰልጣኟ ታስረዳለች።
"ከአሰልጣኞች እንዲሁም ከአስተዳደሩ ዘንድ የሚያገኙት ድጋፍ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታል። ድጋፍ እስካለ ድረስ ቅርጫት ኳስ መጫወት የሚፈልጉ ስፖርተኛ እናቶች የትም መድረስ ይችላሉ" በማለት ሃሳቧን ታጠቃልላለች።















