ሴቶችና ወንዶች በምጣኔ ኃብቱ እኩል መብት ያላቸው የት ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለማችን ስድስት ሃገራት ብቻ ናቸው ለሴቶችና ለወንዶች እኩል ህጋዊ የምጣኔ ኃብት መብት የሰጡት። እነማን ናቸው?
የአለም ባንክ አዲስ ባወጣው "ሴቶች፣ ቢዝነስ እና ህግ" በተባለ መግለጫው ላይ የሴቶችና የወንዶችን የኢኮኖሚ እኩልነት ሙሉ ለሙሉ መፍጠር የቻሉት ከ187 ሃገራት ስድስት ብቻ ናቸው ብሏል።
በዋሽንግተን መቀመጫውን ያደረገው ተቋም የ10 ዓመታት ገንዘብ ነክና ህጋዊ የሆኑ በሴቶችና ወንዶች መካከል እኩልነት እንዳይሰፍን የሚያደርጉ እንደ በነጻነት የመንቀሳቀስ፣ እናትነት፣ የቤት ውስጥ ጥቃትና ንብረት አስተዳደርን የመሳሰሉ መረጃዎችን ተመልክቷል።
በአለም ባንክ መስፈርት መሰረት በእነዚህ መስኮች ላይ የሁለቱን ፆታዎች እኩልነት ሙሉ በሙሉ ማስፈን የቻሉት ስድስት ሃገራት ቤልጂየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ላቲቪያ፣ ሉክዘምበርግና ስዊድን ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በአማካይ 75 በመቶ የሚሆነውን ለወንዶች የተሰጠ ተመሳሳይ መብት እንደሚጠቀሙ መረጃው ያሳያል።
ከቦታ ቦታ ያለው ያለ ልዩነት
አማካይ ውጤቱ እንደየቦታው ይለያያል። ለምሳሌ በአውሮፓና መካከለኛው እስያ 84 በመቶ ሲሆን በመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ደግሞ ወደ 47̄ በመቶ ዝቅ ይላል።
አሜሪካ 83.75 በመቶ የሚሆን ውጤት ቢኖራትም ከመጀመሪያዎቹ 50 ሀገራት ውስጥ መካተት አልቻለችም።
ህጎቿ የሴቶችን መብት በጣም የሚገታው ሳዑዲ አረቢያ ደግሞ 25.6 በመቶ በሆነ ውጤት የዝርዝሩ መጨረሻ ደረጃን ይዛለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመጀመሪያ ስራዋን ከጀመረች አንዲት የ25 ዓመት ወጣት ወይም ስራዋን እየሰራች ልጆቿን ለማሳደግ ጥረት ከምታደርገው እናት እስከ ጡረታ መውጫዋ የደረሰባትን ሴትን ውሳኔ ታሳቢነት አድርጎ የተሰራው ጥናት ሴቶች የሚወስዷቸው ውሳኔዎች እንዴት በህግ ተፅዕኖ ስር እንደሆኑ ተመልክቷል። " በማለት ክሪሰታሊና ጂኦርጂቫ የአለም ባንክ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ተናግራለች።
"ብዙ ህግና ደንቦች ሴቶች የስራ መስኩን እንዳይቀላቀሉ ወይም የራሳቸውን ቢዝነስ እንዳይጀምሩ ይከለክሏቸዋል። ይህ ሴቶችን በኢኮኖሚ የማግለል ሂደት በኢኮኖሚው ውስጥ የመሳተፍ እና የስራ ሃይሉን መቀላቀል ላይ ዘላቂ የሆነ ጠባሳ ያስከትላል።"
መግለጫው በአንዳንድ ሃገራት የተወሰደውንም አበረታች ውሳኔ አካቷል።
የአለም ባንክ ባለፉት 10 ዓመታት 131 ሃገራት 274 የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍኑ ህግና ደንቦችን ማፅደቃቸውን ገልጿል።
ሴቶችን በስራ ቦታ መጠበቅ
እነዚህ ለውጦች በ35 ሀገራት የሚገኙ ሴቶችን በስራ ቦታ ከሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች መከላከል ያስቻሉ ሲሆን የዛሬ አስር ዓመት ከነበረው 2 ቢሊዮን ተጨማሪ ሴቶችን መከላከል ተችሏል።
ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት ባለፉት 10 ዓመታት ብዙ የፆታ እኩልነትን የሚያሰፍኑ የህግ ለውጦችን ያደረጉ ሃገራት ናቸው።
የወርልድ ባንክ ዘገባ የሴቶችን ሙሉ የስራ ህይወት ያጠና ሲሆን ስራ ከመፈለግ ጀምሮ፤ ቢዝነስ ማቋቋምን እና ጡረታ የማግኘት እድላቸውን አካቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአለም አቀፍ ደረጃ 33 ሃገራት አባቶች ልጅ ሲወልዱ የስራ ፈቃድ እንዲወስዱ የሚፈቅድ ህግ እና 47 የሚሆኑት ደግሞ በቤት ውስጥ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ላይ ጠበቅ ያለ ህግ አፅድቀዋል።
"የፆታ እኩልነትን ለማስፈን ህግ እና ደንቦችን ብቻ ማፅደቅ እና መቀየር በቂ እንዳልሆነ እናውቃለን። ህጎቹ መተግበር አለባቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የመሪዎች ድጋፍ፣ የሁለቱም ፆታዎች ንቁ ተሳትፎ እና ለረጅም ጊዜ ተይዘው የቆዩ ባህላዊ አመለካከቶችን መቀየር ያስፈልጋል።" ብላለች ክርስታሊና ጂኦርጂቫ።
በመጨረሻም ''መረጃው እንደሚያሳየው ህጎች ሴቶችን የሚያጠናክሩ እንጂ ማሳካት ከምንችላቸው ነገሮች ወደ ኋላ የሚጎትቱን መሆን እንደሌለባቸው ነው።" ብላለች።












