ሕንድ፡ ለሴቶች የተከለከለ ተራራን የወጣችው የመጀመሪያ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Dhanya Sanal
ዳንያ ሳናል የተባለች ሕንዳዊት ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ተራራ በመውጣት ግንባር ቀደም ሆናለች።
ተራራው አግስታይኮዳም ይባላል። ተራራው 6,128 ጫማ (1,868 ሜትር) ርዝመት አለው። ይህን ተራራውን መውጣት እንደ ሀይማኖታዊ ጉዞ ይቆጠራል።
የሕንድ ፍርድ ቤት በቅርቡ ሴቶች ተራራውን እንዲወጡ ከመፍቀዱ በፊት፤ ተራራው ጫፍ መድረስ የተፈቀደው ለወንዶች ብቻ ነበር።
ዳንያ ተራራውን በመውጣት ታሪክ ብትሰራም፤ የሂንዱ እምነት ተከታይ የቀዬው ነዋሪዎች ሴቶች ተራራውን እንዲወጡ በመፈቀዱ ደስተኛ አይደሉም።
የ38 ዓመቷ ዳንያ ለቢቢሲ እንደተናረችው፤ ተራራውን ስትወጣ ሊያስቆማት የሞከረ ሰው አልነበረም። የመብት ተሟጋቾች የዳንያ ጉዞ ለሴቶች መብት መከበር የሚያደርጉት ትግል መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ሴቶች ተራራውን መውጣት እንዲፈቀድላቸው የድጋፍ ፊርማ አሰባስበው ወደ ሕንድ ፍርድ ቤት ያቀኑ ሴቶች ደስታቸውን ገልጸዋል።
ከሴቶቹ አንዷ ዲቫያ ዲቫክራን "የሴቶችን ጭቆና ለማስቆም አንድ ርቀት ወደፊት ተራምደናል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሕንዷ ካርላ የሚገኘው አግስታይኮዳም ተራራ ከአካባቢው ተራሮች በርዝመት ሁለተኛው ነው። የአካባቢው ተወላጆች ሴቶች ተራራውን እንዲወጡ መፈቀዱ 'እምነታችንን ይጻረራል' ቢሉም ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ውድቅ አድርጎታል።
ዳንያ ተራራውን እየወጡ ከነበሩ 100 ወንዶች ብቸኛዋ ሴት ነበረች። በቀጣይ ሳምንታት የእሷን ፈለግ በመከተል ወደ 100 ሴቶች ተራራውን ለመውጣት ተመዝግበዋል።












