ሚጥሚጣ፣ እርድ እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞችን መመገብ የጤና ጥቅም አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሚጥሚጣ፣ እርድ እና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች የጤና በረከቶች እንዳሏቸው በተደጋጋሚ ይነገራል።
አልፎ ተርፎም ቅመማ ቅመሞች “የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ሥርዓትን” የማጎልበት አቅም አላቸው ይባላል።
በምግባችን ላይ የምንጨምራቸው ቅመማ ቅመሞች በሽታዎችን እንድንከላከል ሊያግዙን ይችላሉ?
ቅመማ ቅመሞች ለበርካታ ሺህ ዓመታት የምግባችን አካል ሆነው ቆይተዋል።
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት እንደ ኮረሪማ፣ ከሙን፣ ቁንዶ በርበሬ፣ በሶ ብላ፣ ጥቁር አዝሙድ፣ እርድ የየቀኑ የሕዝቡ ምግብ አካል ናቸው። ሽሮው፣ በርበሬ ከበርካታ ቅመማ ቅመሞች ተመጥነው የሚዘጋጁ ሲሆን፣ በርካታ ምግቦችን ያለ ቅመማ ቅመም መብላት የሚታሰብ አይደለም።
ለዘመናት የምሥራቁ ዓለም ቅመማ ቅመሞችን እንደ አንድ የምግብ አካል እና መድኃኒቶች ቢያያቸውም በምዕራቡ ዓለም በቅርቡ ነው መታወቅ የጀመሩት። ቅመማ ቅመሞች ያላቸው የፈዋሽነት ኃይል እንዲሁም ፋይዳቸው መሰማት ተጀምሯል።
ሂላሪ ክሊንተን በአውሮፖውያኑ 2016 የምርጫ ዘመቻ ቅስቀሳቸው ወቅት በሽታን ለመከላከል አንድ የሚጥሚጣ ቃሪያ ይመገቡ እንደነበር ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በእስያ አልጫ ምግቦችን ለመሥራት የሚውለው እርድ በዓለም ዙሪያ ባሉ ካፌዎች በላቴነት መጠጣት ጀምሯል።
በተለይም በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት እርድ በሽታን የመከላከል አቅምን ይጨምራል እንዲሁም በኮሮና ቫይረስ ከመያዝ ይከላከል የሚሉ መልዕክቶች በሰፊው ተጋርተው ነበር።
በርበሬ ወይም ቅመም ያልተጨመረበት (ኬይን ፔፐር)፣ ከሎሚ እና ውሃ ጋር አቀላቅሎ መጠጣት ክብደት ይቀንሳል የሚለውን ቢዮንሴ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የሰጠችው ያልተገባ ምክር እስካሁን ድረስ አንዳንዶች ይከተሉታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሚጥሚጣ የጤና ጥቅሞች
በበርካታ ዓለማችን ክፍሎች በብዛት ጥቅም ላይ ከሚውሉት ቅመሞች አንዱ ሚጥሚጣ ነው።
በርካታ ጥናቶች በጤናችን ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ተጽእኖዎች መርምረው ጠቃሚ እና አሉታዊ ውጤቶችን አግኝተዋል።
በሚጥሚጣ ቃሪያ ውስጥ የሚገኘው ንጥረ ነገር ካፕሳይሲን ይሰኛል። አንዳንድ ጥናቶች ካፕሳይሲን የተሰኘው ንጥረ ነገር ረዥም ዕድሜ ለመኖር ሊረዳ እንደሚችል ያመለክታሉ።
በአውሮፓውያኑ 2019 የወጣ አንድ የጣሊያን ጥናት እንዳመለከተው በሚጥሚጣ የተቀመመ ምግብ በሳምንት አራት ጊዜ የሚመገቡ ሰዎች የሚጥሚጣ ቃሪያ ከማይበሉት ጋር ሲነጻጸሩ የመሞት ዕድላቸው ዝቅተኛ እንደሆነ ነው።
ተመራማሪዎቹ ሲጋራ ማጨስን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ የተመጣጠነ ምግብ አመጋገብን በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤንም በመቆጣጠር ነው ጥናቱን ያካሄዱት።
በአውሮፓውያኑ 2015፣ በቻይና ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎችን የሚጥሚጣ አመጋገብ እና ጤናን የመረመሩ ቻይናውያን ተመራማሪዎች ሚጥሚጣ መመገብ ሞትን እንደሚያዘገይ ይፋ አደርገዋል።
በየቀኑ ቅመማ ቅመም ያላቸውን ምግቦች የሚመገቡ ነዋሪዎች በሳምንት አንድ ጊዜ ወይም ከሚመገቡት ጋር ሲነጻጸር በ14 በመቶ የሞት ዕድላቸውን ዝቅ አድርጎታል ብለዋል።
“የጥናቶቹ ግኝቶች ቅመም ያላቸውን ምግቦች በየዕለቱ መመገብ በካንሰር፣ በልብ ህመም እና በመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ምክንያት የሚያጋጥሙ ሞቶችን እንደሚቀንስ ነው” ሲሉ በሃርቫርድ የሕብረተሰብ ጤና ክፍል የሥነ ምግብ ፕሮፌሰር የሆኑት ተመራማሪው ሉ ኪው ያስረዳሉ።
ይህ ማለት ግን ሚጥሚጣ አብዝቶ መብላት መጀመር ጤናዎን ይጠብቃል ወይም ከመተንፈሻ አካላት ህመም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከላከላል ማለት አይደለም።
በቻይናው ጥናት ምርምር ያደረጉባቸውን እያንዳንዳቸውን ሰዎች ለሰባት ዓመታት ያህል መከታተላቸውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው።
በእነዚህም ዓመታት ሚጥሚጣን የተመገቡ ሰዎች ጤናቸው ላይ በጎ ነገር ተስተውሏል።
ተመራማሪው ኪው ሚጥሚጣን የመመገብ ተጽዕኖን አልኮል መጠጣትን፣ ማጨስን እና የአካል ብቃት የመሳሰሉ የአኗኗር ዘይቤን በመቆጣጠር ነው ምርምሩን ያካሄዱት።
የሚጥሚጣ ቃሪያን መመገብ በበሽታ የመያዝ አጋጣሚን የሚከላከለው በካፕካይሲን በተሰኘው ንጥረ ነገር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪው ያስረዳሉ።
“እንደ ካፕሳይሲን ያሉ በሚያቃጥሉ ምግቦች ውስጥ ያሉ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች በደም ውስጥ ያለውን ኮሌስትሮል እና የጨጓራ ብግነትን (ኢንፍላሜሽን) በመቀነስ ምግብ በሰውነት የመዋሃድ ሁኔታን እንደሚጨምሩ አሳይተዋል” ይላሉ ተመራማሪው።
በርካታ ጥናቶችም ካፕሳይሲን የምናቃጥለውን የኃይል መጠን እንዲጨምር እና የምግብ ፍላጎታችን እንዲቀንስ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
የሚጥሚጣ ቃሪያ መመገብ ለከፍተኛ ውፍረት እንዳንጋለጥ እና ከፍተኛ የደም ግፊት ላለባቸው ጠቃሚ እንደሆነ በምርምራቸው እንደደረሱበት በኳታር ዩኒቨርስቲ የሥነ ምግብ ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዙሚን ሺ ገልጸዋል።
ነገር ግን የሚጥሚጣ ቃሪያ አብዝተው የሚመገቡ ቻይናውያን ግንዛቤያቸውን (ኮግኒቲቭ ስኪል) እንደሚቀንሰው ፕሮፌሰር ዙሚን ያስረዳሉ።
ይህ በተለይም ከማስታወስ ችሎታ ጋር የተያያዘ ሲሆን በቀን ከ50 ግራም በላይ ሚጥሚጣን መመገብ የማስታወስ ሁኔታን በእጥፍ እንደጨመረባቸው ምርምር የተደረገባቸው ቻይናውያን ተናግረዋል ተብሏል።
የሚጥሚጣ ቃሪያን ስንበላ የሚያቃጥለን ስሜት ከግንዛቤ ማሽቆልቆል ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ተጠቁሟል። የማቃጠል ስሜቱ ዕጽዋት ራሳቸውን ከበሽታዎች እና ከተባዮች ለመከላከል የሚያመነጩት ነው።
ዕጽዋት ከተባዮች ራሳቸውን ለመከላከል መራራ፣ የሚያቃጥሉ ነገሮች የሚያመነጩት ንጥረ ነገር በሰው ልጅ ላይ ተጽዕኖው አናሳ እንደሆነ በዩናይትድ ኪንግደም ኒውካስል ዩኒቨርስቲ የሥነ ምግብ ተመራማሪ የሆኑት ክርስቴን ብራንድት ያስረዳሉ።
“መርዛማ ንጥረ ነገር ጥሩ ሊሆን ይችላል ለምሳሌ በቡና ላይ የምናገኘው ካፌይን የበለጠ የንቃት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ከበዛ ግን መጥፎ ነው” ይላሉ ክርስቴን።
በዩኬ የአስቶን ሕክምና ትምህርት ቤት የምግብ ተመራማሪ የሆኑት ዱአን ሜሎር በበኩላቸው በቅመሞች ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች ለሰው ልጆች ጎጂ አይደሉም ሲሉ ይከራከራሉ።
በምግብ ውስጥ የሚጨመሩ ቅመሞች ውስጥ ያሉ የሚያቃጥሉ እና መራራ ንጥረ ነገሮችን ጣዕም ለምደናል የሚሉት ምሁሩ የሰው ልጅ እነዚህን መቋቋም ይችላል ይላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ቅመም ውስጥ ያለው ንጥረ ነገር ጥቅም ቢኖረውም የምንመገበው መጠን በበቂ ስላልሆነ በረከቱን አናየውም የሚሉ ተመራማሪዎች አሉ።
አንዳንድ ጥናቶች አበረታች ግኝቶችን ይፋ ቢያደርጉም በአውሮፓውያኑ 2022፣ በ11 ጥናቶች ላይ ያደረገ ትንታኔ ካፕሳይሲን እና ቅመማ ቅመሞችን መመመገብ ለጤና የሚሰጠው ጥቅም ግልጽ አይደለም። እንዲሁም ማስረጃዎቹ “እጅግ ከፍተኛ ጥራት” ያላቸው እንዳልሆኑ ደምድሟል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእርድ ጥቅሞች
በሰዎች ጤና ላይ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉ በሰፊው የሚነገርለት እርድ ነው። በእርድ ውስጥ የሚገኘው ኩርከሚን የተሰኘው ንጥረ ነገር ብግነትን፣ ጭንቀትን እና ሌሎችን ሕመሞች ለማከም በአማራጭ ሕክምናዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ይውላል።
ሆኖም እርድ ስላለው ጠቀሜታ ጠንካራ ማስረጃዎች የሉም።
በርካታ ጥናቶች ኩርከሚን በካንሰር ላይ ተጽእኖዎች እንዳላቸው በላብራቶሪ የተደረጉ ሙከራዎች አሳይተዋል። ሆኖም ላብራቶሪ እና የሰው ልጅ አካል የተለያየ ነው።
በሰው ልጅ አካል ውስጥ የሚገኙበት መጠን በጣም ዝቅተኛ ስለሚሆን ለጤና ጥቅም ላይኖራቸው ይችላል ይላሉ ተመራማሪዎቹ።
በሰውነት ውስጥ በዝቅተኛ መጠን መገኘት ለጤና የሚሰጡት ፋይዳ የሌሎችም ቅመሞች ሁኔታ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳንድ ተመራማሪዎች አንዳንድ ቅመሞች በሰውነት ውስጥ በከፍተኛ መጠን ሲገኙ ሊኖራቸው የሚችለውን ጠቀሜታ ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን አግኝተዋል።
በባለፈው ዓመት የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በየቀኑ ዝንጅብል መመገብ ሉፐስ እና የሪህ በሽታን (rheumatoid arthritis) ጨምሮ አውቶ ኢሚዩን የተሰኙትን በሽታዎች መከላከል እንደሚችሉ ነው።
በሚኒሶታ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፐሮፌሰር የሆኑት ካትርይን ኔልሰን በኩርከሚን ላይ ጥናት ያደረጉ ሲሆን ሰውነታችን ውስጥ ከገባ በኋላ ልንጠቀምበት እንደማንችል ነው።ንጥረ ነገሩ በትንሹ እና በትልቁ አንጀት ውስጥ ካሉ ፕሮቲኖች ጋር ሲገናኝ አወቃቀሩ እንደሚቀየር ደርሼበታለሁ ይላሉ።
እርድ ጠቃሚ የሆነ ነገር ሊኖረው ቢችልም ኩርከሚን የተሰኘው ንጥረ ነገር አይደለም ይላሉ። ምንም እንኳን እርድ ላይ ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግ ቢገልጹም ከሌሎች ምግቦች ጋር ስለሚበስል ኬሚካላዊ አወቃቀሩን እንደሚቀይር ማስታወስ ይገባል ይላሉ።
እርድን መመገብ ምንም ጉዳት እንደሌለው ቢናገሩም ነገር ግን እንደ መድኃኒት መጠቀም አይመክሩም።
በሚጥሚጣ እና እርድ ላይ በሰፊው ጥናት የተደረገ ሲሆን ሙከራዎቹ በአጠቃቀም እና በጤና ተጽዕኖዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን መንስዔውን እና ውጤቱን አለዩም።
ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2019 የተደረገው ጥናት ሚጥሚጣን መመገብ ሞትን ዝቅ እንደሚያደርግ ያሳያል። ሆኖም ሰዎቹ ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው ያደረገው ሚጥሚጣ መመገባቸው፣ ቀድሞውኑ ጤናማ የሆኑ ሰዎች ሚጥሚጣ መመገባቸው ወይም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች እንዳሉ ማወቅ አልተቻለም።
በርካታ ተመራማሪዎች የቅመማ ቅመም የጤና ጠቀሜታ ከምንበላው ምግብ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናሉ።
ለምሳሌ ጨውን በቅመማ ቅመም የመተካት ሁኔታዎች አሉ የሚሉት በኒውዮርክ ዩኒቨርስቲ የካንጎን ጤና ማዕከል የክሊኒካል ረዳት ፕሮፌሰር ሊፒ ሮይ ያስረዳሉ።
“ቅመሞች ምግብን ጣፋጭ ያደርጋሉ። ከጨው በበለጠ ጤናማ አማራጭ ሊሆኑ ይችላሉ” ይላሉ።
እንዲያውም ባለፈው ዓመት ተመራማሪዎች ጨውና ስባማ ምግቦችን በቅመማ ቅመም በመተካት ምግቦችን የበለጠ ጣፋጭ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል።
ሚጥሚጣን ከአትክልት ጋር መመገብ ለጤና ጠቃሚ ቢሆንም ቅመማ ቅመሞችን በሽታን ለመከላከል ወይም ከሕመም ለመዳን ጥገኛ መሆን የለብንም።















