ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ግብፅ የናይል የውሃ ድርሻዋ እንዲነካ አትፈቅድም አሉ

የፎቶው ባለመብት, Yoweri K Museveni x
የግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ አገራቸው በናይል (አባይ) ያላትን የውሃ ድርሻ እንዲነካ እንደማትፈቅድ አስጠነቀቁ።
ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ይህንን ያሉት ከላይኛው የናይል ተፋሰስ አገራት አንዷ ከሆነችው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በካይሮ አል ኢትሃድያ ቤተ መንግሥት ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም. በጣምራ በሰጡት መግለጫ ነው።
"በድጋሚ ለግብፃውያን ማረጋገጥ የምፈልገው 105 ሚሊዮን ዜጎቻችን እና 10 ሚሊዮን የሚሆኑ በአገራችን ያሉ እንግዶቻችን በሕይወት የሚያቆየው ውሃ እንዲነካ ፈጽሞ እንደማንፈቅድ ነው" ሲሉ ፕሬዚዳንት አልሲሲ መናገራቸው በጽህፈት ቤታቸው በወጣ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጅመሩ እንዲሁም የተካሄዱ አምስት ውሃ ሙሌቶችን በጽኑ የሚያወግዙት አልሲሲ፤ በትናንትናው የጋራ መግለጫም በናይል ላይ የሚደረግ የተናጠል እርምጃን አገራቸው ውድቅ እንደምታደርግ አቋማቸውን አስታውቀዋል።
"ግብፅ በውሃ ደኅንነቷ ላይ የተደቀነን የኅልውና ስጋት ችላ ትለዋለች ብሎ የሚያስብ ማንኛውም አካል ተሳስቷል። ሁኔታውን መከታተላችንን እንቀጥላለን፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የሕዝቦቻችንን የኅልውና ሃብቶች ለማስጠበቅ ማንኛውንም እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ አልሲሲ አስጠንቅቀዋል።
አል ሲሲ ይህንን ያሉት 14 ዓመታትን የፈጀው እንዲሁም አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ የተበጀተለት ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አምስተኛ ዙር ሙሌት ተጠናቆ ምረቃው በመጪው መስከረም እንደሚካሄድ ኢትዮጵያ ካሳወቀች በኋላ ነው።
የነጭ ናይል መነሻ እና 15 በመቶ የሚሆነውን ውሃ ድርሻ የምታበረክተው የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በበኩላቸው የናይል የወደፊቱ ዕጣ ፈንታን አስመልክቶ ከግብፅ አቻቸው ጋር የተደረገውን ውይይት ጠቅሰው አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
"የናይል ሁኔታ ሰፋ ባለ መልኩ ልናየው ይገባል። አንዳንዴ ችግሮች የሚመነጩት ከአቀራረባችን ነው። በታሪካዊ መብቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ፤ የናይል ተፋሰስ አገራት ዓለም አቀፍ ፍላጎትን ልናጤን ይገባል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በዚህ ጽሁፋቸው ላይ ስላነሱት "በታሪካዊ መብቶች ላይ ማተኮር" በሚለው ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ አላሰፈሩም።
ሆኖም ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመውና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት ሙጥኝ ብላ ታሪካዊ ተጠቃሚነት በሚል መርኅ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ትቃወማለች።
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ያላካተተ ከመሆኑ በተጨማሪ ግብፅ 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃን እንዲሁም ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ እንድታገኝ እና 86 በመቶ የናይልን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይ እና ኢፍትሃዊ እንደሆነም ይጠቀሳል።
በየዓመቱ ከሚፈሰው 84 ቢሊዮን ኩየቢክ ውሃ 12 በመቶው በትነት የሚያልቅ ሲሆን፣ ይህ ስምምነት በዋነኝነት ግብፅን ትገዛ የነበረችውን ብሪታንያን ለጥጥ ምርቷ በዋነኝነት ተጠቃሚ አድርጓታል።
ሙሴቪኒ አክለውም "ዓላማችን ለሁሉም ብልጽግና፣ የመብራት አገልግሎተ ተደራሸነት፣ መስኖ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ለሁሉም በሚደርስበት መሆን አለበት" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው "እነዚህን ዓላማዎች በሙሉ በማዕቀፋችን በማካተት ሳይንሳዊ እና ፍትሃዊ መንገዶችን በመጠቀም ማሳካት ይቻላል" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ መስከረም ወር ላይ ይመረቃል ብለዋል።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ሕጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ስትወተውት የቆየችው ግብፅ ይህንኑ በመድገም አስጠንቅቃለች።
የግብፅ የውሃ ሃብት ሚኒስትር ሃኒ ሰዊላም አገራቸው በናይል ወንዝ ላይ የሚደረግ "የተናጠል እርምጃን" ትቃወማለች ሲሉ ባለፈው ወር ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል።
ፕሬዚዳንት አልሲሲ በዚሁ መግለጫቸው ላይ ሙሴቪኒን ጠቅሰው "በኡጋንዳ ግብፅ ማለት የአትክልት ስፍራ" ማለት እንደሆነ እንደነገሯቸው አስታውሰዋል።
"ይህ የአትክልት ስፍራ ከናይል ሌላ የውሃ ምንጭ የለውም። ዝናብ የለንም። ግብፅ ይህንን ትተዋለች ብሎ ማሰብ ሕይወታችንን አሳልፈን መስጠት ነው፤ ይህ ደግሞ በጭራሽ የማይሆን ነው" ሲሉ ናይል የግብፅ የኅልውና መሠረት ነው የሚለውን የቀደመ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
"ዝናብ የሚዘንብላቸው ሰዎች ዝናብ የሌላቸው የሚያልፉበትን ሁኔታ በፍጹም አይሰማቸውም" ብለዋል።
"ግብፃውያን የውሃ ጉዳይ በጣም እንደሚያሳስባቸው" የገለጹት አልሲሲ፤ እንደ ሙሴቪኒ ካሉ "ብልህ መሪዎች ጋር በመሆን የግብፃውያንን ሕይወት ፈጽሞ የማይጎዳ መፍትሄ የመፈለግ ኃላፊነት አለብኝ" ሲሉም አስምረዋል።
ግድቡን በሚመለከት በተከታታይ ሲካሄዱ የነበሩ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሦስትዮሽ ድርድሮች አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተናቸው ይታወሳል።
ውሃ ሌሎች ዓላማዎችን ለማሳካት የሚደረግ የዘመቻ አካል ሊሆን የሚችል እንደሆነ የጠቀሱት አል ሲሲ "ይህንን በሚገባ እናውቃለን" ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
አክለውም "በሌሎች ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት፣ ማሴር እና ጥፋትን ስንቃወመው የቆየ ጉዳይ ነው። የአፍሪካ አገራት ለዓመታት በበቂ ጦርነቶች እና ግጭቶች ስቃይ ውስጥ ስላለፉ እኛ ለግንባታ፣ ለትብብር እና ለልማት ነው የምንቆመው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጋርጥ ስታስታውቅ ቆይታለች።















