ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግብጽን እና ሱዳንን ለምን ያሰጋቸዋል?

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ አራተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌትን አከናውኛለሁ ማለቷን ተከትሎ ግብጽ ከናይል ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት ላይ አደጋ የጋረጠ ነው ስትል ከሳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቀናት በፊት የታላቁ የህዳሴ ግድብ አራተኛ እና የመጨረሻ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ህጋዊ እና አስገዳጅ ሶስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብጽ ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።

ጥቂት ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የናይል ወንዝ 85 በመቶ የሚሆነውን የውሃ መጠን ድርሻ በሚገብረው አባይ ወንዝ ላይ የተገነባ ነው።

የአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ከሱዳን ጋር ከሚዋሰነው ድንበር በስተደቡብ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ከ1.6 ኪሎሜትር በላይ እርዝማኔ እና 145 ሜትር ከፍታ አለው።

ሙሉ በሙሉ ግንባታው ያልተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ 12 ዓመታትን ያህል ፈጅቷል።

4.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል የአገሪቷ እና የህዝቧ አንጡራ ሃብት የፈሰሰበት ግድብ የታላቋን ለንደን የሚያህል ስፋት አለው።

ግድቡ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው ጥቅም ምንድን ነው?

ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን እየገነባች ያለችው በጨለማ ውስጥ ያለው 60 በመቶ የሚሆነው ህዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እንዲያገኝ ነው።

ከዚያም አልፎ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅም በእጥፍ በማሳደግ ለተቋማት የማያቋርጥ የኃይል አቅርቦት ለማቅረብ እና ልማቱን በማሳደግ ተስፋ ተጥሎበታል።

ለጎረቤት አገራቱ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ጂቡቲ እና ኤርትራን የመሳሰሉ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙበት እንደሆነም ተነግሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግብጽ እና ሱዳንን ለምን ያስቆጣቸዋል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ 107 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ግብጽ ለውሃ እቅርቦትም ሆነ ለህልውናዋ መሰረት የናይል ወንዝ ነው ትላለች።

ብዙ ውሃ የሚያስፈልገውን ጥጥ ለማምረት ጨምሮ ለተለያዩ እርሻዎችም ሆነም ለመኖሪያ ቤቶች የሚጠጣ ውሃ የምታገኘው ከናይል ወንዝ ነው።

ይህ ብቻ አይደለም ግብጽ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት የገነባችውን አስዋን ግድብንም ሙሌት የሚካሄድበትን የናስር ሃይቅንም ለመሙላት የምትጠቀመው ናይልን ነው።

48 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ሱዳንም በናይል ወንዝ ላይ ጥገኛ ናት።

ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ ግብጽ እና ሱዳን እያነሱ ያሉት ስጋት አገራቱ የሚያገኙትን የውሃ መጠን አቅርቦት ኢትዮጵያ እንድትቆጣጠር ያስችላታል የሚል ነው።

ሌላኛው ግብጽ የምታነሳው ቅሬታ ዝናብ በሚቀንስበት ወቅት ወይም ድርቅ ቢያጋጥም ኢትዮጵያ ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በቂ ውሃ እንደሚፈስ ዋስትና ትስጥ የሚለውን ነው። በተጨማሪም በነዚህ ወቅቶች ኢትዮጵያ ግድቡን ኃይል ለማመመንጫነት ሙሉ አቅሙን ትጠቀማለች የሚለውም ላይ ያላትን ስጋት ታነሳለች።

“የኢትዮጵያ የተናጠል እርምጃዎች የታችኛውን ተፋሰሰስ አገራት ጥቅምና መብት እንዲሁም የውሃ ደህንነታቸውን ችላ ያለ ነው” ሲልም ነው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሙሌቱ በኋላ በመግለጫው ያስታወቀው።

ግብጽ ከናይል የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት 2 በመቶ ከቀነሰ በመስኖ የለማ 200 ሺህ ሄክታር መሬትን የሚያወድም ነው ስትልም ትከራከራለች። በወንዙም ላይ ዝቅተኛ የውሃ መጠንም በናይል ላይ ያለውን ትራንስፖርት ሊጎዳ ይችላል ትላለች።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ሙሌት በሶስት ዓመት አጠናቅቄ ጨርሻለሁ በማለት ያስታወቀች ሲሆን ግብጽ ከዚህ ቀደም የግድቡ ሙሌት ከ12 እስከ 21 ዓመታት መውሰድ እንዳለበት ስትከራከር ቆይታለች።

ሱዳን በናይል ወንዝ የውሃ መጠን ላይ የግብጽን ያህል የጎዳት ባይመስልም ለግድቡ የምትሰጠው ምላሽ ግን አገሪቱን እየናጣት ባለው ጦርነት ምክንያት ቀንሷል።

ግብጽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ላይ መደረስ ይቻል ይሆን?

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ በሶስቱ አገራት መካከል የውዝግብ መንስኤ ሆኗል።

ኢትዮጵያ ባልነበረችበት የተፈረሙትና በተደጋጋሚ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ብላ የምትጠራቸው የአውሮፓውያኑ 1929 እና የ1959 በናይል ላይ የተደረሱት ስምምነቶች ሱዳንና ግብጽን በወንዙ ድርሻ ላይ የበላይነት መብት የሰጠ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የላይኛው ተፋስስ አገራት በወንዙ ላይ ፕሮጀክቶችን ካሰቡም ከውሃ ድርሻቸው የመንፈግ መብትም የሰጠ ነው።

85 በመቶ በላይ የአባይን ውሃ የምትገብረውን ኢትዮጵያ ያለ ውሃ የሚያስቀር አግላይና ኢፍትሃዊ ነው በማለትም በነዚህ ስምምነቶች መተዳደር የለብኝም በማለትም ግድቡን መገንባት ጀመረች።

ወቅቱም ግብጽ በአረብ አብዮት በምትናወጥበት ወቅት ነው።

ሶስቱ አገራት በአውሮፓውያኑ 2015 የህዳሴ ግድብ የትብብር መግለጫ ስምምነት ቢፈራረሙም ከህዳሴ ግድብ ሙሌት እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ የሶስትዮሽ ድርድሮች ፍሬ ማፍራት አልቻሉም።

ግጭቶችን ለመከላከል የሚሰራው አለም አቀፉ የክራይሲስ ቡድን በአገራቱ መካከከል የትጥቅ ግጭት ሊኖር እንደሚችልም ነው ያስጠነቀቀው።

በአውሮፓውያኑ 2019 የህዳሴ ግድብን የማደራደር እና ግብጽ እና ኢትዮጵያንም የማሸማገል ሚናን አሜሪካ ብትወስድም ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።

ለሁለት ዓመት ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድርም ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላቷን ማጠናቀቋን ከማሳወቋ ከሶስት ሳምንታት በፊት ተጀምሯል።