ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ማከናወኗ ግብጽን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ ‘የመጨረሻ’ የተባለውን አራተኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ማካሄዷን ተከትሎ ግብጽ ብስጭቷን ገለጸች።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት ያከናወነችው የታችኛው ተፋሰስ አገራት ፍላጎትን ቸል በማለት ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትናንት ጵጉሜ 5/2015 ዓ.ም. በይፋዊ የኤክስ ገጻቸው ኢትዮጵያ “አራተኛውንን እና የመጨረሻውን ሙሌት በተሳካ ሁኔታ” ስለማካሄዷ ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን ለመገደብ በገንዘብ በዕውቀት፣ በጉልበት እና በጸሎት የተሳተፉትን አመስግነው፣ ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የውስጥ እና የውጭ ጫናዎች እንደነበሩባት ገልጸዋል።
“ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር። በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል።” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ይህ ግንባታው ከተጀመረ 12 ዓመታትን ያስቆጠረውን ግዙፍ ግድብን በውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ግብጽ እና ሱዳን ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከአባይ ውሃ ፍትሐዊ የሆነ የድርሻዬን መጠቀም አለብኝ በማለት አሳሪው ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ስታደርግ ቆይታለች።
ይህን ተከትሎ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት በፌስቡክ ገጹ ላይ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ ሙሌት ያከናወነችው ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ እ.አ.አ 2015 (መጋቢት 14፣ 2007 ዓ/ም) ላይ የተፈራረሙት የመርሆዎች ስምምነት በሚጥስ ሁኔታ ነው ብላለች።
ግብጽ በተፈራረምነው የመርህዎች ስምምነት መሠረት በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ የውሃ ሙሌት ማድረግ የተከለከለ ነው ብላለች።
“የኢትዮጵያ የአንድ ወገን እርምጃ በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች የተረጋገጡትን የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ጥቅምና መብት እንዲሁም የውሃ ደኅንነታቸውን ያላገናዘበ ነው” ብሏል የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።
ግብጽ ይህን ትበል እንጂ በሥልጣን ሹኩቻ በርስ በርስ ግጭት ውስጥ የገባችው ሌላኛው የታችኛው ተፋሰስ አገር ሱዳን የ4ኛው ዙር የውሃ ሙሌትን በተመለከተ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።
በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ የሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና ኦፕሬሽንን በተመለከተ በአዲስ አበባ፣ ካይሮ እና ካርቱም ተደጋጋሚ ድርድሮችን ሲያደርጉ ቢቆዩም ሦስቱ አገራት እስካሁን ከስምምነት መድረስ ሳይችሉ ቆይተዋል።
በቅርቡም በሦስቱ አገራት መካከል ሲደረግ የነበረው እና ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በካይሮ ተካሂዶ ያለውጤት ተበትኗል።
ይህ ውይይት በመስከረም 2016 በኢትዮጵያ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
የግድቡ ግንባታ 11ኛ ዓመት ላይ፣ ባለፈው ዓመት የካቲት 13፣ 2014 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ 90 በመቶው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጎረቤት አገራት ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ግድቡ የሚይዘውን 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ ሙሉ በሙሉ ሲይዝም ውሃው የሚተኛበት ስፍራ ርዝመት 246 ኪሎ ሜትር እንደሚደርስ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ግብፃውያን ግድቡ አገራቸው ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ መጠንን በመቀነስ ጉዳት ያስከትልብናል የሚል መከራከርያ ያቀርባሉ።
ኢትዮጵያ ግን የአባይ ውሃን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳለት በመግለጽ፣ ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን የውሃ አቅርቦት በማይጎዳ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማመንጨት እንደምታውለው ትገልጻለች።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ መጀመሯን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከግብፅ እና ከሱዳን በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን፣ የግድቡ ጉዳይም ከአፍሪካ ኅብረት ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሦስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ ኅብረት እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ንግግር ቢያደርጉም ሁሉንም ከሚያግባባ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ተጠናቆ ሥራውን ሲጀምር በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከራሷ በማውጣት እያከናወነች ነው።












