በሞሮኮ በርዕደ መሬት ሳብያ ከ2000 በላይ ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሞሮኮ በርዕደ መሬት ሳብያ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ2ሺህ በላይ ማሻቀቡ ተገለፀ።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በርዕደ መሬቱ የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ከ1ሺህ 400 እንደሚሆን ገለፀዋል።
በሞሮኮ በርዕደ መሬት ክፉኛ የተጎዳው የአገሪቱ ክፍል የማራካሽ ደቡባዊ ክፍል መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ የሦስት ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ያወጁ ሲሆን በአደጋው ቤት ንብረታቸውን ላጡ ሰዎች መጠለያ እና የምግብ ድጋፍ እንዲደግላቸው ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ዳግም መሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል ሲሉ የሰጉ በርካታ ሰዎች ለሁለተኛ ቀን ከቤታቸው ውጪ አውላላ ሜዳ ላይ ለማሳለፍ ተገድደዋል።
በዋነኛነት የመሬት መንቀጥቀጡ የተሰማው በአትላስ ተራራ አካባቢ ነው።
ይህም ከማራኬሽ በደቡብ ምዕራብ 71 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል። ጥልቀቱም 18.5 ኪሎ ሜትር ነው።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው በ6.8 የተለካው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
በማራኬሽና በሌሎችም ደቡባዊ አካባቢዎች ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።
አል-ሀውዝ፣ ማራኬሽ፣ ኦራዛቴ፣ አዚል፣ ክሪቾዋ እና ታራውዳንት በተባሉት አካባቢዎች ነው ሰዎች የሞቱት።
በመሬት መንቀጥቀጡ ሕንጻዎችና ጎዳናዎች ሲጎዱ የሚያሳዩ ቪድዮዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ወጥተዋል።
አንድ የዐይን እማኝ ለሮይተርስ እንደነገሩት በማራኬሽ ጥንታዊ ሰፈር ሕንጻዎች ወድመዋል።
በታሪካዊቷ ከተማ የሚኖሩ ሌላ ሰው “ሕንጻዎች ሲንቀሳቀሱ” ማየታቸውንና አስጊ እንደሆነም ገልጸዋል።
አብደላክ ኤል አምሪኒ የተባሉ ሰው ለኤኤፍፒ “ሰዎች ደንግጠውና ፈርተው ነበር።
ወላጆች ግራ ተጋብተው ልጆችም እያለቀሱ ነበር” ብለዋል።
ለአሥር ደቂቃ የኤሌክትሪክና ስልክ መስመሮች መቋረጣቸውንም ገልጸዋል።
አንድ ቤተሰብ የቤት ፍርስራሽ ውስጥ ታፍኖ እንደነበርና በርካቶችም ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ዘገባው ይጠቁማል።
ከአትላስ ተራራ በተጨማሪ በመዲናዋ ራባት፣ በካሳብላንካ እና ኢስዎሪያ የመሬት መንቀጥቀጡ ተሰምቷቸዋል።
በተራራማው መንደር የተሠሩ ሕንጻዎች ከመሬት መንቀጥቀጡ የሚተርፉ አይመስልም።
በዛ አካባቢ ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ለማወቅም ጊዜ ይወስዳል።
የቢቢሲ ሪፖርተር የመሬት መንቀጥቀጡ በደረሰበት አንድ መንደር ሲደርስ፣ በእድሜ የገፉ ሴት ከአንድ ስፍራ የወጡ 18 አስክሬኖችን እያዩ ሲያለቅሱ ተመልክቷል።
ዳግም የመሬት መንቀጥቀጥ ሊኖር ይችላል ብለው የሰጉ በርካታ የአካበቢው ነዋሪዎች ለሁለተኛ ቀን ከቤታቸው ውጪ ማደር መርጠዋል።
ከፍተኛ የሆነ የምግብ እና የመጠጥ ውሃ እጥረት አለ።
የአስቸኳይ ጊዜ የአደጋ ሠራተኞች በተራራማው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ጋር ለመድረስ፣ በመሬት መንቀጥቀጡ የፈራረሱ ቤቶች እና ድንጋዮች መንገዱን በመዝጋታቸው አስቸጋሪ አድርጎታል።
ከንጉሡ ቤተመንግሥት የወጣ መግለጫ እንደሚያስረዳው ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በሁሉም የሕዝብ መገልገያዎች የአገሪቱ ባንዲራ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል።
ንጉሡ አክለውም የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የነፍስ አድን ስራውን እንዲያግዝ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ሞሮኮያውያን የተጎዱ ሠዎችን ለመደገፍ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ደም እየሰጡ ነው።
ይህ ርዕደ መሬት በ1960 ከተከሰተው እና የ12 ሺህ ሰዎችን ከገደለው በመቀጠል ከባድ ሆኖ ተመዝግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የሞሮኮ ነፍስ አድን ስራን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን የገለፀ ሲሆን ስፔን፣ እስራኤል እና ፈረንሳይም በተመሳሳይ ቃል ገብተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሞሮኮ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ የገባችው ጎረቤት አገር አልጄርያም፣ ለሰብዓዊ እርዳታ መተላለፍያነት የአየር ክልሏን ክፍት አድርጋለች።












