በሰሜን ሸዋ በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ባለፉት ቀናት በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በአገር መከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኤፍራታና ግድም ወረዳ የምትገኘው የማጀቴ ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያው ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሰው በተለይ ባሳለፍነው እሑድ ነሐሴ 28/2015 ዓ.ም. ከንጋት 12 ሰዓት ገደማ እስከ ከሰዓት 10፡00 ሰዓት ድረስ በቆየ ግጭት ከ30 የማያንሱ ነዋሪዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
'እናት' የተባለው አገራዊ ፓርቲ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ፣ ጵጉሜ 1/2015 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ ላይ በማጀቴ ሕጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ 29 ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ወታደሮች ተገድለዋል ብሏል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ሰዎች የተገደሉት በተባራሪ ጥይት፣ በከባድ መሣሪያ እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት ፍተሻ ወቅት ነው ብለዋል።
“ብዙ ሰው የተጎዳው ከተማ ውስጥ ነው። ሁለቱ ይተኩሳሉ ሕዝቡ በመሃል ነው ያለው። 34 ሰው ሞቷል። እየዞርን አስክሬን አንስተን ቀብረናል። እኔ ባለሁበት ቤተ-ክርስቲያን 7 ሰዎች የተቀበሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሕጻናት እና ሴቶች አሉበት” ብለዋል።
እኚህ ነዋሪ አብዛኛዎቹ በተባራሪ ጥይት ከተመቱ በኋላ ሕይወታቸው ያለፈ መሆኑን ጠቅስው፣ ሌሎች ደግሞ ቤት ለቤት በሚደረግ ፍተሻ ወቅት በመንግሥት ኃይሎች የተገደሉ ናቸው ብለዋል።
ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪም፣ ሕጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረው፤ አብዛኛው ግድያው የተፈፀመው የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በቤት ለቤት ፍተሻ ወቅት በወሰዱት እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
“ቤት ለቤት እየገቡ (የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች) ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችን፣ ሕመምተኛ ሁሉ አልጋ ላይ የመቱት። የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ናቸው። 85 ዓመት ሽማግሌ ሁሉ ተገድለዋል።” ብለዋል።
እኚህ ነዋሪ የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ወደ አርሳቸው ቤትም መምጣታቸውን እና የጦር መሳሪያ እንዲያስረክቧቸው እንደጠየቋቸው ተናግረዋል።
“ቤቴን አንኳኩ። ግቡ ብዬ ካስገባኋቸው በኋላ መሣሪያ አምጣ ሲሉኝ እኔ መሣሪያ የለኝም፤ እንደምታዩኝ ከብት እያረባሁ ነው የምኖረው አልኳቸው። መሣሪያ ደቅነውብኝ ነበር። ሌሎች ቤት ውስጥ የነበሩትን በዱላ ደበደቧቸው። መርምረዋቸው መሣሪያ የለውም ሲሏቸው ትተውን ሄዱ” በማለት ያጋጠማቸውን ለቢቢሲ አጋርተዋል።
ነዋሪዎች እና እናት ፓርቲ በማጀቴ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ በተመለከተ ቢቢሲ የመንግሥት ኃላፊዎችን ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።
እናት ፓርቲ በመግለጫው በዚያኑ ዕለት ነሐሴ 28/ 2015 ዓ.ም. በክልሉ በሚገኙት ምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ፣ ሞሰባ ሽሜ አቦ ቀበሌ እና ምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደጋ ዳሞት ወረዳ በተፈፀመ የድሮን ጥቃትም ቢያንስ 20 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግሥቱ የክልል ልዩ ኃይሎች ፈርሰው ወደ ተለያዩ የፀጥታ እና የመከላከያ መዋቅሮች እንዲገቡ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ እየተጠናከረ ሄዶ፣ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭቶች እና የተኩስ ልውውጦች አሁንም ቀጥለዋል።
ባለፈው ሳምንት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛ ኃይሎች ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ያሉ ቢሆንም በዚህ ሳምንት በበርካታ አነስተኛ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ግጭቶች መቀጠላቸው እየተነገረ ነው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ፣ሐሙስ፣ ጳጉሜ 2/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “ክልሉ አሁን ላይ በጣም በተሻለ የጸጥታ ሁኔታና ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መኾኑን” ገልጸዋል።
አብዛኛው የክልሉ አካባቢ ሰላም መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የቀሩት ጥቂት ወረዳዎችም ሕዝብን በማስተባበር ወደ ሰላም እንዲመለሱ እንሠራለን ብለዋል።
በአማራ ክልል ከተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ ፖለቲከኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ከእነዚህ መካከል የምክር ቤት አባላት የሆኑ የገዢው እና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይገኙበታል።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያለመከሰስ መብት ያላቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለን፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ ከ50 በላይ ግለሰቦች አዋሽ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ ታስረው እንደሚገኙ ገልጿል።
ኢሰመኮ በዚህ ሪፖርቱ ብዙዎቹ ታሳሪዎች የአማራ ብሔር ተወላጅና የኦርቶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች መሆናቸው፣ ለእስር የበቁትም በማንነታቸው መሆኑን እንደሚያምኑ እንደገለጹለት በሪፖርቱ ጠቅሶ ነበር።
ኮሚሽኑ ወደ አዋሽ አርባ ከመወሰዳቸው በፊትና በቁጥጥር ሥር በሚውሉበት ወቅት ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻ እንደደረሰባቸው፤ ሆኖም በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን ገልጸውልኛል ማለቱ ይታወሳል።












