“እዛ ቤት ገብቼ የተሰማኝ ደስታ በሕይወቴ የመጀመሪያም የመጨረሻም ነው”

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮጀክት መኖሪያ ቤት ከሰጣቸው አቅመ ደካሞች አንዱ አቶ ታደሰ ፋንቴ ገብሬ ናቸው።
ቀድሞ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ነበር የሚኖሩት።
“ጣሪያው ግድግዳው ቆርቆሮ የሆነ ቤት በማዳበሪያ ሸፍነን ነበር የምንኖረው። ለ18 ዓመት ተሰቃይተናል። ወንዝ ዳር ነው። በጋ ላይ ይሸታል። ክረምት ላይ ተባይ አለው” ሲሉ የቀድሞ ቤታቸውን ይገልጻሉ።
አስም እንዳለባቸው፣ እግራቸውን እንደሚያማቸውና ዐይነ ስውር እንደሆኑም ይናገራሉ።
“እግዚአብሔር ይመስገን የልደታ ክፍለ ከተማ የቤቶች ኤጀንሲ ከላይ እስከ ታች ተባብረውኛል። ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መጥተው አይተውን ቃል ገብተውልን ነበር። አሁን የቤቱን ቁልፍ ተረክበናል” ሲሉም ተናግረዋል።
አዲስ ቤት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 እንደተሰጣቸውና ከሳቸው በተጨማሪ ጎረቤታቸውም ቤት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በጂቡቲ የከባድ መኪና ሹፌር ነበሩ። ሱዳንም ለ18 ዓመት ያህል ከባድ መኪና እንደነዱ ይናገራሉ።
“ኢትዮጵያ ሰላም ሲሆን ገባሁ። ጂቡቲ እየሠራሁ ሳለ ድንገት በ1996 ዓ. ም. ዐይኔን ታመምኩ። 19 ዓመት ይሆናል ዐይኔ ከጠፋ። ጭንቅላቴ ላይም እጢ ነበረብኝ እሱን አስወጥቻለሁ። አሁን እገሬን ያስነክሰኛል።”
የ62 ዓመቱ አዛውንት አቶ ታደሰ የሚረዳቸው እንደሌለና በችግር ውስጥ እንደነበሩ ይናገራሉ።
“ምግብ ከጎረቤት ነበር የምበላው። ዳቦም ከተገኘ፣ እንጀራም ከተገኘ፣ ሽሮም ከተገኘ ከጎረቤት እየተለመነ ነበር የምበላው። ደኅና እያለሁ ቤተክርስቲያንም፣ ሃይገር ውስጥም እለምን ነበር። ከታመምኩ በኋላ ጎረቤቴን መለመን ጀመርኩ።”
አዲስ ቤት ሲሰጣቸው የተሰማቸውን ሲገልጹም “ወደር የሌለው ደስታ ነው የተሰማኝ። በሕይወት ዘመኔ ደስታን አላውቅም ነበር። በመንከራተት ነው ያሳለፍኩት። እዛ ቤት ገብቼ የተማኝ ደስታ በሕይወቴ የመጀመሪያም የመጨረሻም ደስታ ነው” በማለት ነው።
“ገብተን ለመኖር ውሃና ሌሎችም ነገሮች እስከሚሟሉልን እየጠበቅን ነው። ሶፋ አለው፣ አልጋ አለው። እግዚአብሔር ይመስገን” ሲሉም አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ላለፉት ሦስት ዓመታት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በዋናነት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የሕዝብ ግንኙነት እንደያዘ እናትዓለም መለሰ ይናገራሉ።
አቅመ ደካማ ሰዎችን መደገፍ አንዱ መንገድ እንደሆነ ይገልጻሉ። በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀምሮ ወደ በጋም መቀጠሉን አክለዋል።
እናትዓለም በእነዚህ የክረምት እና የበጋ ፕሮጀክቶች ብዙ ሺህ ቤቶች ይሠራሉ። ይጠገናሉ። ሙሉ በሙሉ እንደ አዲስ የሚሰሩ ቤቶች አሉ ያሉ ሲሆን፤ ቤቶቹ "ለአረጋውያን፣ አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ይሰጣቸዋል” ብለዋል።
ቀድሞ ይኖሩባቸው የነበሩ ቤቶች “ቤት” የሚል ስም ቢሰጣቸውም የቤትነትን ደረጃ የማያሟሉ እንደሆኑ ይናገራሉ።
እነዚህ ቤቶች ከተለዩ በኋላ እድሳት ይደረግላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency
“በክረምት ፕሮጀክት ከተጀመሩት ቤቶች ተሠርተው የተጠናቀቁ 860 ቤቶችን በዚህ ጷግሜ እስረክበናል” ብለዋል።
ለቤቶቹ ከ947 ሚሊዮን ብር በላይ ከባለሃብቶች፣ ግለሰቦች፣ የሃይማኖት ተቋማትም መሰብሰቡን አክለዋል።
ከክረምት ፕሮጀክት በተጨማሪ በበጋ ፕሮጀክት “ወደ 6200 ቤቶች በ11ዱም ክፍለ ከተማ ተሠርተው ተሰጥተዋል” ሲሉም አስረድተዋል።
“የበጎ ፈቃድ ሐሳቡ መንግሥት ራሱ እንዲሠራው ሳይሆን በጎ ፈቃደኞችን ለማበረታታት ነው” በማለትም አክለዋል።
ቤት የሚሰጣቸው ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ የቀደመ ቤታቸው ፈርሶ በበጎ ፈቃደኞች ድጋፍ እንደተሠራ ገልጸዋል። ይህም ቤቶቹን አፍርሶ መኖሪያ ሕንጻ ገንብቶ ለአቅመ ደካሞች መስጠትን ያካትታል።
“የሚኖሩበት ቤት ሲታይ ያሳዝናል። እኔ ብሆን ብሎ ማሰብ ነው። የበለጠ እንድንሠራ የሚገፋፋን ነው” ሲሉም ስሜታቸውን ገልጸዋል።
“እያንዳዱ ተቋም ባለሃብቶችን አስተባብሮ ለመሥራት የወሰደው አለ። ግለሰቦች ተባብረው የሚሠሩትም አለ” ሲሉም ስለ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ይገልጻሉ።
የዛሬ ሦስት ዓመት ፕሮጀክቱ ሲጀመር በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ይሠሩ እንደነበርና አሁን ግን ቁጥሩ መጨመሩንም ጠቅሰዋል።
በክረምት በጎ ፈቃድ ተማሪዎችን የማገዝ፣ ሕሙማንን የማከም ሥራዎች እንደተሠሩም ይናገራሉ።
“ሰዎች ሲሳካላቸው ሌላውንም እንዲያስቡ የማድረግ ባህልን ለማዳበር ነው” በማለትም አስረድተዋል።
20ኛው የምገባ ማዕከል በአዲስ አበባ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሰሞኑ እንደሚመረቅም ተናግረዋል። እስካሁን ያሉት ማዕከሎች ወደ 40ሺህ ተጠቃሚዎች ነበሩት።
በጷግሜን ቀናት የበጎነት ቀንን ጨምሮ በተለያዩ ስያሜዎች የተለያዩ በጎ አገልግሎቶች እየተሰጡ ሲሆን፣ ይህም የነጻ መጓጓዣ አገልግሎት መስጠትን እና ለ424 ሺ 689 አቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራትን ይጨምራል።












