የስፔን የሴቶች ሊግ ተጫዋቾች በደሞዝ ክፍያ ምክንያት አድማ ሊመቱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ከፍተኛው የሴቶች ሊግ ተጫዋቾች በክፍያ ምክንያት አድማ ሊመቱ እንደሆነ ገልጠዋል።
ሊጋ ኤፍ የተሰኘ ስም ያለው የሴቶች ሊግ አርብ ይጀምራል። ነገር ግን ተጫዋቾች የመጀመሪያዎቹን ሁለት ጨዋታዎች በመጋጠም ፈንታ ወደ መልበሻ ክፍል በመግባት አመፃቸውን ይገልጣሉ።
የስፔን እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር አድማው የተጠራው “ፍትሐዊ” የሆነ ስምምነት ላይ ልንደርስ ስላልቻልን ነው ብሏል።
ባለፈው ዓመት ሊጋ ኤፍ ፕሮፌሽናል ሲሆን ነው ድርድር የተጀመረው። ነገር ግን ሊግ የተጫዋቾቹ “ጥያቄ” ሃገሪቱን ወደ “ምጣኔ ሃብት ቀውስ ይወስዳታል” ሲል ተቃውሞ ነበር።
ባለፈው ዓመት ዝቅተኛው ዓመታዊ ደመወዝ 16 ሺህ ዩሮ ነበር። ተጫዋቾቹ ደግሞ ዝቅተኛው ክፍያ 25 ሺህ ዩሮ እንዲሆን ነው ጥያቄያቸው።
በሚቀጥለው ዓመት ይህ ዝቅተኛው ክፍያ ወደ 30 ሺህ ዩሮ እንዲያድግ ይፈልጋሉ።
ቢሆንም ሊጋ ኤፍ ለተጫዋቾቹ 18 ሺህ ዩሮ ዝቅተኛ ክፍያ አቅርቦ በሚቀጥሉት ሶስት የውድድር ዘመናት ወደ 25 ሺህ ያድጋል የሚል ሐሳብ አቅርብያለሁ ይላል።
አልፎም የሕፃናት እንክብካቤ እና የትምህርት ወጭ መሸፈን የሚል ሐሳብ ሊጋ ኤፍ አቅርቢያለሁ ቢልም ተጫዋቾቹ በዚህ አልተስማሙም።
ሊጉ በለቀቀው መግለጫ ምንም እንኳ ማሕበሩ “በጭፍን” የቀረበውን ሐሳብ አልቀበልም ቢልም ደመወዛቸው በ25 በመቶ እንዲያድግ ያለውም ተቀባይነት ማጣቱን አሳውቋል።
የሊጋ ኤፍ የመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታዎች ከአርብ እስከ እሑድ ይካሄዳሉ። የሁለተኛው ሳምንት መርሐ ግብር ደግሞ በሳምንቱ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
ባለፈው የውድድር ዘመን እንዲሁ የመጀመሪያዎቹ የሊግ ኤፍ ጨዋታዎች ዳኞች የተሻለ ክፍያ ካልተከፈለን በማለታቸው ምክንያት መጓተቱ ይታወሳል።
የስፔን የሴቶች እግር ኳስ ባለፉት ሳምንታት በመላው ዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
ይህ የሆነው የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ባነሳበት ወቅት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሉዊስ ሩቢያሌስ የተጫዋቿ ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈር በመሳማቸው ነው።
ሄርሞሶ ሰውዬው ያለፍላጎቴ ነው የሳሙኝ ብላለች፤ ፕሬዝደንቱም ከሥልጣናቸው ታግደዋል፤ የብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ሆርጌ ቪልዳ ደግሞ ተነስተዋል።












