የቀድሞ ፍቅረኛው ላይ ጥቃት በመፈፀም የተጠረጠረው የዩናይትዱ አንቶኒ ከብራዚል ቡድን ተቀነሰ

አንተኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቀድሞ ፍቅረኛው ላይ ጥቃት አድርሷል ተብሎ የተጠረጠረው የማንቸስተር ዩናይትድ የመስመር ተጫዋች አንቶኒ ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ለጊዜው ታግዷል።

የብራዚል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደገለጠው የ23 ዓመቱ ተጫዋች ከቡድኑ እንዲቀነስ የተደረገው “አንዳንድ እውነታዎች ለሕዝቡ ይፋ በመሆናቸው” እና “ምርመራ ሊደረግባቸው ስለሚገባ ነው።”

የብራዚሉ ዜና አውታር ዩኦኤል የአንተኒ የቀድሞ ፍቅረኛው ፈፅሞብኛል ያለችውን ጥቃት ሰኞ ዕለት ለሕትመት አብቅቷል።

የሳዎ ፓውሎ እና የግሬተር ማንቸስተር ፖሊስ ምርመራ መክፈታቸውን ገልጠዋል።

ተጫዋቹ ግን የቀረበበኝ ክስ የሐሰት ነው ብሎ ማስተባበያ ለቋል።

“በእርጋታ መናገር የምችለው የቀረበበኝ ክስ ሐሰት መሆኑንና ይፋ የሆኑ ማስረጃዎች አልፎም ሌሎች ማስረገጫዎች እኔ ንፁሕ እንደሆንኩ እንደሚያሳዩ ነው” ሲል በማሕበራዊ ሚድያ ገፁ ፅፏል።

“ፖሊስ እያካሄደ ያለው ምርመራ የኔን ንፁሕ መሆን እንደሚያረጋግጥ እምነት አለኝ።”

አንቶኒ የቀረበበት ክስ በአውሮፓዎያኑ ጥር 15 የቀድሞው ፍቅረኛው ጋብርዬላ ካቫይንን ማንቸስተር ከሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ “በቴስታ መትቷል”፤ በዚህ ምክንያት ግንባሯ በመጎዳቱ ሕክምና አድርጋለች የሚል ነው።

ጋብርዬላ አክላ ተጫዋቹ ደረቷን በቡጢ ሲመታት ጡቷን ቀዶ ጥገና ስትሰራ የገባው ሲሊከን በመጎዳቱ ማስተካከያ ቀዶ ጥገና ለማድረግ እንደተገደደች ትናገራለች።

ሰኞ መግለጫ የለቀቀው አንቶኒ ከቀድሞው ፍቅረኛው ጋር የነበረው ግንኙነት “ጤናማ ያልሆነ ነው” ቢልም “ምንም ዓይነት አካላዊ ጉዳት የለውም” ሲል ያስተባብላል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ ተጫዋች ባለፈው ሰኔ በቀድሞ ፍቅረኛው በሐሰት የቤት ውስጥ ጥቃት ክስ እየቀረበበት እንደሆነ የሚጠቁም መግለጫ ለቆ ነበር።

የግሬተር ማንቸስተር ፖሊስ “ተጫዋቹ ላይ ስለቀረበው ወቀሳ መረጃ እንዳለው” ገልጦ “ይህን ሪፖርት ለማጠናከር ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያሻ” አስታውቋል።

ፖሊስ አክሎ “በአሁን ወቅት ከዚህ የዘለለ አስተያየት መስጠት አንችልም” ብሏል።

ቢቢሲ ስፖርት ያናገራቸው የማንቸስተር ዩናይትድ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የማንቸስተር ዩናይትድ የክንፍ መስመር ተጫዋች የሆነው እንግሊዛዊው ሜሰን ግሪንውድ በተመሳሳይ የቀድሞው ፍቅረኛው ላይ ጥቃት ፈፅሟል ተብሎ ክለቡ ለስድስት ወራት ምርመራ ካደረገ በኋላ ከተጫዋቹ ጋር ለመለያየት መስማማቱ የተሰማው ባለፈው ወር ነው።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ያለባት ብራዚል በማንቸስተር ዩናይትዱ ተጫዋች ፈንታ የአርሰናሉ ጋብርኤል ሄሱስን ጠርታለች።