“ስለዓለም ዋንጫ ድላችን ሳይሆን ስለ ተጫዋቿ መሳም ብቻ መወራቱ አሳዛኝ ነው” የስፔኗ ግብ ጠባቂ

የስፔን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ካታሊና ኮል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቅርቡ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ አስተናጋጅነት በተደረገው የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ውድድር ስፔን ሻምፒዮና ሆኗለች።

የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ቀድሞውንም እንደ ወንዶች የዓለም ዋንጫ ትኩረት የማያገኝ ቢሆንም የዘንድሮው ደግሞ በአንድ ክስተት ተሸፍኗል።

የስፔን እግር ኳሰ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሉዊስ ሩቢያሌስ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋች የሆነችውን ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈሯን ያለፈቃዷ መሳማቸው ውዝግብ አስነስቷል።

ስፔን ዩናይትድ ኪንግደምን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በረታችበት የፍጻሜ ውድድር ዕለት ነው ፕሬዝዳንቱ እስካሁን መነጋገሪያ የሆነውን ድርጊት የፈጸሙት።

የፕሬዝዳንቱ ተግባር በአገሪቱ እንዲሁም በዓለም የስፖርት መድረክ መወዛገቢያ መሆኑ ቀጥሏል። የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ “ያየነው ነገር ተቀባይነት የለውም። የሩቢያሌስ ይቅርታ በቂ አይደለም። ያየነውን ነገር ለምን እንዳደረገው ግልጽ እንዲሆን እርምጃዎች መውሰድ አለባቸው” ሲሉም ወቅሰዋል።

የስፔንን ዋንጫውን የማንሳት ድልን ያጠለሸውን ይህንን ክስተትም የስፔን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ካታሊና ኮል “አሳዛኝ” ስትል ገልጻዋለች።

“ሁሉም ሰው ስለዓለም ዋንጫ አሸናፊነታችን ሳይሆን ስለ መሳም ብቻ ማውራቱ አሳዛኝ ነው። እኛ እግር ኳስ ተጫዋቾች ነን። እንድንከበር እንፈልጋለን” ብላለች።

ጄኒ ሄርሞሶ ፕሬዝዳንቱ ያለ ፈቃዷ እንደሳሟት አስታውቃለች። ይህንንም ተከትሎ ሉዊስ ሩቢያሌስ ከሥራ ታግደዋል፤ እንዲሁም ምርመራ ተከፍቶባቸዋል።

የፓቹካ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሆነችው ጄኒ ሄርሞሶ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ባወጣችው መግለጫ “ይህንን ክስተት ሪፖርት ማድረግ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ማንኛችንም ቢሆን በሥራ አጋጣሚ፣ በስፖርታዊ ዝግጅቶችም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ፈቃዳችንን ያልሰጠንበት ያልተገባ ባህርይ ሰለባ መሆን እንደሌለብን ስለማምን ነው። የተጋላጭነት ስሜት ተሰምቶኛል። በስሜት የተነዳ፣ ጾተኝነት የተሞላበት፣ ያልተገባ እንዲሁም የእኔ ፈቃድ የሌለበት ጥቃት ሰለባ ሆኛለሁ” በማለት “በቀላሉ ስገልጸውም አልተከበርኩም” ብላለች።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ተጫዋቿን በሳሙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከ17 ዓመት በታች እና ከ19 ዓመት በታች እግር ኳስ ውድድር ሻምፒዮና የነበረችው ግብ ጠባቂ ከጄኒ ሄርሞሶ ጎን እንደምትቆም እና እንደምትደግፋት ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

የስፔን የሴቶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን 23ቱም ተጫዋቾች ፕሬዝዳንቱ ከኃላፊነት ካልተነሱ በየትኛውም ጨዋታዎች እንደማይተሳተፉ ጽኑ አቋማቸውን ከሰሞኑ ግልጽ አድርገዋል።

ፕሬዝዳንቱ የፈጸሙት ተግባር በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ትችትን፣ ጠለቅ ያሉ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክርክሮች እንዲነሱ መንስዔ ሆኗል። በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ላይም ጾተኝነት፣ ስምምነትን በተመለከተ እንዲሁም ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም የሚሉ ጉዳዮችን በርካቶች እንደገና እንዲከልሷቸው ሆነዋል።

ሉዊስ ሩቢያሌስ ከኃላፊነታቸው እንደማይለቁ እና ተጫዋቿን የሳሟትም “ፈቃደኝነት” በነበረው ሁኔታ ነው ባሉ ማግስት በፊፋ ታግደዋል። ተጫዋቿ ፕሬዝዳንቱ ፈቃደኝነት ነበረው ያሉትን ጉዳይ “ሙሉ በሙሉ ፍጹም ሐሰት ነው። ሰዎችን የሚያታልልበት እና የሚያጭበረብርበት ልምዱም አካል ነው” በማለት ተናግራ ነበር።

የ22 ዓመቷ ግብ ጠባቂ ከ“ቢቢሲ ሙንዶ” ጋር በነበራት ቆይታ በዓለም ዋንጫ አሸናፊነታቸው ስፔናውያን በሙሉ ሊደሰቱ ሲገባ የፕሬዝዳንቱ ተግባር ያገኙትን ስኬት በማጠልሸቱ የተሰማትን ብስጭት አልደበቀችም።

የስፔን የሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ፡ የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሉዊስ ሩቢያሌስ የብሔራዊ ቡድን አባል የሆነችውን ጄኒ ሄርሞሶን በመሳማቸው በስፔን ከፍተኛ ውዝግብ እንዳስነሳ እናውቃለን። በዚህም ድላችሁ እንዲሁም ሕዝቡ አሸናፊነታችሁን የሚያጣጥምበትን መንገድም አጠልሽቶታል። መጀመሪያ በድሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ያ ታሪካዊ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ እንዴት ነበር?

በጣም ከፍተኛ ደስታ የተሰማን ዕለት ነበር። በፍጻሜ ጨዋታው ዩናይትድ ኪንግደምን እንደምናሸንፍ እናውቅ ነበር። በጨዋታው ወቅት ያሰብነው ሁሉም ነገር በጥሩ ሁኔታ እንደሚሄድ እና እንደሚጠናቀቅ እርግጠኛ ነበርን። እውነት ነው ለባከነ ሰዓት የተሰጠው 13 ደቂቃ ማለቂያ የለሽ ስሜት ፈጥሮብን ነበር። ነገር ግን 1 ለ 0 አሸንፈን ሻምፒዮና መሆናችን እስካሁንም በቃላት የማልገልጸው ስሜት ነው።

ቢቢሲ፡ የዓለም ዋንጫ ካሸነፋችሁ በኋላ የቀጠሉት ሳምንታትን እንዴት አገኘሻቸው?

በምኖርባት ከተማ ማሎርካ ውስጥ ድሉን በከፍተኛ ሁኔታ አክብረናል። ሞቅ ያለ አቀባበል ነው የተደረገልኝ። የትም ብሄድ ሰዎች ያውቁኛል። ገበያ ስሄድ፣ ጎዳናዎች ላይ መንገደኞች ፎቶ እንነሳ ብለው ያስቆሙኛል። በጣም ከፍተኛ ደስታ የሚፈጥር ስሜት ነው። ሁሉም ነገር በጣም አዲስ ነው። በዓለም ላይ ያከናወንነው ከፍተኛ ስፍራ እንደሚሰጠው ግልጽ መሆኑን አሳይቶኛል። ትልቅ ስኬትን ተጎናጽፈናል ለወደፊቱም እንቀጥላለን።

ቢቢሲ፡ በአሁኑ ወቅት መወዛገቢያ ወደሆነው ጉዳይ እንሂድ፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንቱ ጄኒ ሄርሞሶን የሳሙበት ጉዳይ። ፕሬዝዳንቱ እሷን መሳሟን ተከትሎ ስለተፈጠረው መወዛገብ እና ቀውስ እስቲ ንገሪን።

23ቱ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን እግር ኳስ ቡድን አባላት ዋነኛ ትኩረት የሚሰጠን ባለመሆናችን ያሳዝናል። ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነኝ ግን መንገድ ላይ የሚያስቆሙን በመሉ ከእንኳን ደስ አላችሁ በፊት አጽንዖት የሚሰጡት የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት ተጫዋቿን የመሳም ጉዳይ ነው። ሁላችንም በዚህ እናዝናለን። ነገር ግን በጊዜው ሁሉም ነገር ተፈትቶ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጠር አምናለሁ።

ቢቢሲ፡ በአሁኑ ወቅት የሚመላለስብሽ ስሜት ምንድን ነው?

የዓለም ዋንጫን አግኝተን በተጎናጸፍነው ድል እና ባሳካነው ነገር ደስተኛ ነኝ። ነገር ግን እየሆነ ባለው ነገር ደግሞ በተወሰነ መልኩ ሐዘን ይሰማኛል። በአሁኑ ወቅት ጎልተን እየታየን ያለነው ተጫዋቾቹ ሳንሆን ተመሳሳይ ሰዎች የዜናው ትኩረት መሆናቸው ያበሳጫል።

ቢቢሲ፡ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን ለተደረገው ጥሪ ላለመለስ ወስነሻል። እስቲ ስለዚያ ሂደት ትንሽ ንገሪን።

የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ተገናኘን። ሁላችንም ቢሆን የተፈጠረው ክስተት ተዳፍኖ በዚያው እንዲቀጥል አልፈለግንም። በዚህም መግባባት ላይ ደርሰናል። በጣም የምንሳሳላት የቡድን አባላችን ላይ በተከሰተው ሁኔታ ምንም ብትወስን ከጎኗ ልንቆም ወሰንን። ያደረግነውም እሱን ነው። ምንም ይሁን ምን ከጎኗ ቆመናል። ውሳኔያችን ይህ ነው። የመጨረሻውም ውሳኔያችን መሆኑን አሳውቀናል።

ቢቢሲ፡ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንደትመለሱም ይሁን በጨዋታዎች እንድትሳተፉ ምን መደረግ አለበት?

ሁሉም ነገር ሊስተካከል ይገባል። ሁላችንም ቢሆን የምንጠብቀው ይህንኑ ይመስለኛል። የተከሰተውን ነገር ሁላችንም አይተናል፤ ታዝበናል። ሁሉ ነገር አክትሞ መብታችን እንዲከበር እንፈልጋለን። ይህም ብቻ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ነገር የማይፈጠርበትን ሁኔታ ማየት እንፈልጋለን።

ቢቢሲ፡ የቡድን ጓደኛሽ ጄኒ ሄርሞሶ ጋር ለመነጋገር ዕድል አግኘተሽ ነበር? በአሁኑ ወቅት ያለችበት ሁኔታ እንዴት ነው?

ስልኳ እየደረሷት ባሉ መልዕክቶች ሁሉ የሞላ ይመስለኛል። ሁላችንም የቡድኑ አባላት ለእሷ ያለንን አጋርነት እና ድጋፍ አሳይተናል። ምንም ቢሆን ከጎኗ ለመቆም መወሰናችንን አሳይተናል። መገመት እንደምችለው ፈታኝ ሁኔታ ላይ ነች እችላለሁ። ነገር ግን እንዳልኩት ምንም ብትወስን ከጎኗ ነን።

ቢቢሲ፡ በፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ሩቢያሌስ ባህርይ ተገርመሻል?

ምንም አላስገረመኝም። ግልጽ ነው የሚያስደስት ተግባር አይደለም። በአሁኑ ወቅት ሁሉም ሰው ማውራት ስለማንፈልገው ነገር ማውራት ይፈልጋል። እኛ መናገር የምንፈልገው በዓለም ዋንጫው ስላገኘነው ድል እና ስኬት ነው እንጂ ስለዚህ ጉዳይ አይደለም።

ቢቢሲ፡ የፕሬዝዳንቱን ተግባር ተከትሎ በርካታ ሰዎች እና ተቋሟት ደግፈዋችኋል። በድጋፍ በኩል እንደጎደለ የሚሰማሽ ጉዳይ ይኖር ይሆን?

አይመስለኝም። ሊያግዘን የሚፈል አካል ሁሉ ሊያግዘን ይችላል። መደገፍ የማይፈልግ ደግሞ እንደዚያው ግዴታ አይደለም። ዋናው ነገር የተፈጸመውን እውነታ እናውቃለን። እንዳልኩት በድጋፍም ሆነ በሌላ እኛን መተባበር የሚፈልጉ ይችላሉ፤ የማይፈልጉት ደግሞ ማድረግ አይጠበቅባቸውም።

ቢቢሲ፡ ፌዴሬሽኑ የወሰደውን እርምጃስ እንዴት ታይዋለሽ? ይህስ ውዝግብ እንዴት እንዲጠናቀቅ ትፈልጊያለሽ?

በመልካም ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ነው የምንፈልገው። ሁሉም ተጫዋቾችም ሆኑ ሌሎችም የሚመኙት ይህንን ነው። እግር ኳስ ተጫዋቾች ነን። እግር ኳስ መጫወት እንፈልጋለን። መጫወት ብቻ ሳይሆን መከበር እንዲሁም ሌሎችን ባከበረ መልኩ መንቀሳቀስ እንፈልጋለን። ይኸው ነው። የምናፈቅረውን፣ የምንወደውን ኳስ መጫወት እንፈልጋለን። ውዝግቡ ያክትም እና ቶሎ እንመለስ እንዲሁም ዋንጫዎችን ማግኘት፣ ማሸነፋችንን እንቀጥል።

የስፔን የሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images