የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊዎች ተጫዋቿን የሳሙት ፕሬዝደንት ሥልጣን እንዲለቁ ጠየቁ

ሉዊስ ሩቢያሌስ የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክልላዊ መሪዎች ጄኒ ሆርሞሶን የሳሙት ፕሬዝደንት ሉዊስ ሩቢያሌስ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ጠይቀዋል።

የ46 ዓመቱ ሩቢያሌስ የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ካነሳ በኋላ በፈፀሙት ድርጊት እየተወቀሱ ይገኛሉ።

የ33 ዓመቷ ሄርሞሶ ፕሬዝደንቱ ከንፈሯ ላይ የሳሟት ያለፈቃዷ መሆኑን ገልጣለች።

የስፔን አቃቤ ሕግ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት የፈፀሙት ድርጊት ወሲባዊ ትንኮሳ ነው ወይ የሚለውን መመርመር መጀመራቸውን አሳውቀዋል።

በተያያዘ ዜና የሩቢያሌስ እናት አንጀለስ ቤሃር ልጃቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ወቀሳ ለመቃወም ቤተ-እምነት ገብተው የረሃብ አድማ መምታቸው ተሰምቷል።

በርካታ ሰዎች በሴቶች ንቅናቄ ቡድኖች የተዘጋጀውን ሰልፍ ተቀላቅለው በማድሪድ ጎዳናቸው ከሄርሞሶ ጎን መሆናቸውን እና የሩቢያሌስን ድርጊት ደግሞ እንደሚያወግዙት ሲገልጡ ታይተዋል።

ባለፈው ሳምንት አርብ ሰውዬው ከሥልጣኔ አልወርድም፤ ተጫዋቿን የሳምኩት “በፈቃደኝነት ነው” ብለው ነበር።

በማግስቱ ቅዳሜ የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ ባለፈው ሩቢያሌስን ለተወሰነ ጊዜ ያክል አግዷቸዋል።

የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰኞ ዕለት የሃገሪቱን ክልላዊ የፌዴሬሽን ኃላፊዎች ሰብስቦ ካወያየ በኋላ ሩቢያሌስ ከመንበራቸው እንዲሱ ጠይቋል።

“የሰውዬው ድርጊት ተቀባይነት የሌለው እና የስፔን እግር ኳስ ምስልን የሚያጠለሽ ነው። ሩቢያሌስ ከፌዴሬሽኑ ኃላፊነት በፍጥነት እንዲነሱ እንጠይቃለን” ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አክለው ለጊዜያዊ አስተዳዳሪው ፔድሮ ሮካ ያላቸውን “የተቀናጀ ድጋፍ” ከገለጡ በኋላ ፌዴሬሽኑ ራሱን መፈተሽ አለበት የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ፊፋ ሩቢያሌስን ባገደ ወቅት ፕሬዝደንቱም ሆነ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ተጫዋቿን እንዳያገኙት ያዘዘ ሲሆን ፌዴሬሽኑ ደግሞ ሄርሞሶን እከሳለሁ ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የስፔን የስፖርት ግልግል ችሎት ሰኞ ስብሰባ አድርጎ ሰውዬው ከሥልጣን እንዲነሱ ሐሳብ ቢያቀርብም ውሳኔውን እስካሁን ይፋ አላደረገም።

የስፔን ከፍተኛ የወንጀል ችሎት እንዳለው ሄርሞሶ የሰጠችውን “ግልጥ” አስተያየት ተከትሎ ምርመራ መክፈት አስፈላጊ ሆኗል።

“ጄኒፈር ሄርሞሶ በሰጠችው ይፋ አስተያየት መሠረት የሉዊስ ሩቢያሌስ ድርጊት በሷ ፈቃድ መሠረት የሆነ አይደለም” ይላል መግለጫው።

የሕግ አዋቂዎች ተጫዋቿን ቀርበው “ያሉትን ሕጋዊ እርምጃዎች እንድትመርጥ የሚያማክሯት ሲሆን፤ የተጠረጠረ ወሲባዊ ትንኮሳ ሰለባ እንደመሆኗ ክስ መመሥረት የምትሻ ከሆነ በ15 ቀናት ውስጥ ብሔራዊ ችሎቱን ማናገር እንደምትችል” ይገልጡላታል።

የስፔን ተቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮላንዳ ዲያዝ ሰኞ ዕለት የወንዶች የበላይነት በሃገሪቱ “የሰረፀ” እና መጥፎ ጎኑን በሩቢያሌስ ድርጊት የገለጠ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

የቀኝ ዘመሙ ሱማር ጥምረት ፓርቲ መሪ የሆኑት ዲያዝ በጠቅላላው በሃገሪቱ ያለው ማሕበራዊ አመለካከት መቀየር እንዳለበት ተናግረዋል።

የሄርሞሶ ወኪል የሆነው ፉትፕሮ ከተሰኘው የሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ማሕበር ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ምክክር የወሲባዊ ትንኮሳ እና ጥቃት ሰለባዎች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

“በስፖርት ሕግ መሠረት ሊጠብቋት የሚገባትን ሴት አዋርደው መሳለቂያ ማድረጋቸው ሳያንስ ተጨማሪ ስቃይና ኪሳራ አድርሰዋል” ብለዋል።