የስፔን የእግር ኳስ ኃላፊ ተጫዋቿን ‘ያለ ፈቃዷ’ መሳማቸውን ተከትሎ የቡድኑ አባላት እንደማይጫወቱ አሳወቁ

የፎቶው ባለመብት, Eurasia Sport Images
የስፔን የሴቶች እግር ኳስ ተጫዋች ጄኒ ሄርሞሶ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ያለ ፈቃዴ ነው የሳሙኝ ማለቷን ተከትሎ በርካታ ሴት ተጫዋቾች እንደማይጫወቱ አሳወቁ።
81 ተጫዋቾች የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሉዊስ ሩቢያሌስ ከኃላፊነታቸው እስኪነሱ ድረስም ባለመጫወት አቋማቸው እንደሚጸኑ አረጋግጠዋል።
በሴቶች የዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን በሲድኒ ስታሸንፍ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አጥቂዋን ጄኒን ከንፈሯን ስመዋል።
ከዚያም በኋላም በርካታ ተቃውሞዎች ቢቀርባቸው ከሥራ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆኑም።
የስፔን መንግሥት የ46 ዓመቱን ግለሰብ ለማገድ ሕጋዊ ሂደቶችን የጀመረ ሲሆን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ተቋም ፊፋም የዲሲፒሊን ምርመራ ከፍቷል።
የስፔን የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በጠራው ያልተለመደ ጠቅላላ ጉባዔ ሩቢያሌስ ሥልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጠበቅም እሳቸው ግን በምላሹ “ይሄ መታደን አይገባኝም” ሲሉም ተደምጠዋል።
አክለውም “ጄኒ ብድግ አደረገችኝ። ሜሪ ኧርፕስ ስላዳነችው ፍጹም ቅጣት እርሽው አልኳት። ልሳምሽ አልኳት እና’ እሺ አለች” ብለዋል።
“ብዙ ያልታሰበበት መሳሳም ነው። የጋራ፣ የደስታ ስሜት የተሞላበት እንዲሁም ስምምነት የተገኘበት መሳሳም ነው። ቁልፉ ስምምነት የነበረው መሆኑ ነው። አንዴ በመሳሜ ከፌደሬሽኑ ውጣ ለመባል በቂ ነው ?” ሲሉም ጠይቀዋል።
የፓቹካ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች የሆነችው ጄኒ ሄርሞሶ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ላይ ረዘም ያለ መግለጫ አውጥታለች።
“ሉዊስ ሩቢያሌስ ተነጋግረን ነበር ብሎ በመግለጫው የሰጠው ጉዳይ ፍጹም አልነበረም። ከሁሉም በላይ የሳመኝ ያለ ፈቃዴ እንደነበር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ” ብላለች።
አክላም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ያሉት ነገር “ሙሉ በሙሉ ፍጹም ሐሰት ነው። ሰዎችን የሚያታልልበት እና የሚያጭበረብርበት ልምዱም አካል ነው” በማለት አስፍራለች።
“ይህንን ክስተት ሪፖርት ማድረግ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ማንኛችንም ቢሆን በሥራ አጋጣሚ፣ በስፖርታዊ ዝግጅቶችም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ፈቃዳችንን ያልሰጠንበት ያልተገባ ባህርይ ሰለባ መሆን እንደሌለብን ስለማምን ነው። የተጋላጭነት ስሜት ተሰምቶኛል። በስሜት የተነዳ፣ ጾተኝነት የተሞላበት፣ ያልተገባ እና እንዲሁም የኔ ፈቃድ የሌለበት ጥቃት ሰለባ ሆኛለሁ”
“በቀላሉ ስገልጸውም አልተከበርኩም” ብላለች።












