ፊፋ፤ የስፔኑ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተጫዋቿን ከንፈር መሳማቸውን ተከትሎ ምርምራ ከፈተ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ በሴቶች ዓለም ዋንጫ ወቅት የፈፀሙትን ድርጊት ተከትሎ ምርምራ ከፍቷል።
ስፔን እንግሊዝን አሸንፋ ዋንጫ ስታነሳ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሉዊስ ሩቢያሌስ የአጥቂዋ ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈር ስመዋል።
ከዚህ ድርጊታቸው ቀድሞ ጨዋታው መጠናቀቁ በፊሽካ ሲታወጅ ብልታቸው አካባቢ እጃቸውን አድርገው ደስታቸውን ሲገልጡ ነበር።
በስፔን እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት አርብ ዕለት ከሥራ መልቀቃቸውን ይፋ ሊያደርጉ እንደሆነ ለሥራ አጋሮቻቸው ነግረዋቸዋል።
“ሩቢያሌስ ነገ ሥራ ይለቃሉ። ከተጫዋቾች የነበራቸውን ድጋፍ አጥተዋል። መንግሥት እና ፊፋ እንዲሁም በፌዴሬሽኑ በጀት የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ፊት ነስተዋቸዋል” ሲል የስፔን እግር ኳስ ተንታኙ ጉሌም ባላጉዌ ኤክስ ላይ ፅፏል።
“ቀጣዩ እርምጃ ስፔን ውስጥ ያሉ ሁሉ ይህ ለምን ሆነ ብለው የሚመረመሩበት ነው” ሲል አክሏል።
ፊፋ ባወጣው መግለጫ “በስፖርቱ የሚሳተፉ ሁሉ ክብራቸው ሊጠበቅ ይገባል፤ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ ባሕሪ የሚፈፅሙትን ግን እናወግዛለን” ብሏል።
የፊፋ ዲሲፕሊን ኮድ እንደሚለው ባለሥልጣናት “የፍትሐዊ ጨዋታ፣ ታማኝነት እና የፀና አቋምን” የማክበር ግዴታ አለባቸው።
“መሠረታዊ ጨዋነት የተሞላበት ምግባርን መጣስ፤ ማንኛውንም ተፈጥሯዊ አሊያም ሕጋዊ ሰው በየትኛውም መልኩ መሳደብ፣ በተለይ ደግሞ አስፀያፊ ምልክት ማሳየት፣ ድርጊት ወይም ቋንቋ መጠቀም፤ ወይም ደግሞ የእግር ኳስ ስፖርትን እና/ወይም ፊፋን የሚያጎድፍ ባሕሪ ማሳየት” የሚሉት የዲሲፕሊን ቅጣት ሊያስከትሉ ይችላሉ።
ሩቢያሌስ የጨዋታው መገባደጃ ፊሽካ ሲነፋ የተከበሩ ሰዎች በሚቀጡበት ሥፍራ ከስፔኗ ንግሥት ሌቲዚያ እና የ16 ዓመት ልጇ አጠገብ ተቀምጠው ነበር።
ከዚያ ቀጥሎ መድረክ ላይ የሜዳሊያ አሠጣጥ ሥነ-ሥርዓት ሲደረግ ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈሯን ስመዋታል።
ግለሰቡ ሰኞ ዕለት ለድርጊታቸው ይቅርታ ቢጠይቁም የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ይህ በቂ አይደለም ብለዋል።
ተቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ዮላንዳ ዲያዝ በበኩላቸው ፕሬዝደንት ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ጥሪ አቅርበዋል።
የሄርሞሶ ወኪል የሆነው ፉትፕሮ የተሰኘ ማሕበር ድርጊቱ ቅጣት ሊያስከትል ይገባል ሲል የ33 ዓመቷ ተጫዋች “ማሕበሩ የኔን ፍላጎት” ይወክላል ብላለች።
ፓቹካ ለተሰኘው የሜክሲኮ ክለብ የምትጫወት ሄርሞሶ ለስፔን ብሔራዊ ቡድን 101 ጊዜ ተሰልፋለች።
ሄርሞሶ መጀመሪያ በኢንስታግራም ገጿ የግለሰቡን ድርጊት “አልወደድኩትም” ስትል ቀጥሎ ባወጣችው መግለጫ ግን ሰውዬውን ተከላክላለች።
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አርብ ዕለት የሚካሄድ ልዩ ጠቅላላ ስብሰባ ጠርቷል።












