የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር የእግር ኳስ ኃላፊው ተጫዋቿን ከንፈሯ ላይ መሳማቸው “ተቀባይነት” የለውም አሉ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ጄኒ ሄርሞሶ የተባለችውን ተጫዋች ከንፈሯ ላይ መሳማቸው “ተቀባይነት የለውም”፤ ይቅርታ ማለታቸውም “በቂ አይደለም” ብለዋል።
የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ ሉዊስ ሩቢያሌስ የስፔን ሴቶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ከሆነ በኋላ የቡድኑን አጥቂ ከንፈሯ ላይ መሳማቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በሴቶች የዓለም ዋንጫ ስፔን እንግሊዝን 1-0 አሸንፋ ዋንጫ ስታነሳ ነው የፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ተጫዋቿን የሳሙት።
ሩቢያሌስ ሰኞ ዕለት ይቅርታ ጠይቀው ያደረግኩት ነገር “ፍፁም ትክልል አይደለም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው “ያየነው ነገር ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ትናንት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የሩቢያሌስ ይቅርታ በቂ አይደለም። ያየነው ነገር ለምን እንዳደረገው ግልጥ እንዲሆን እርምጃዎች መውሰድ አለባቸው።”
የስፔን ተቀዳሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮላንዳ ዲያዝ የፌዴሬሽኑ ኃላፊ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ጠይቀዋል።
“ይቅርታ መጠየቁ ዋጋ የለውም” ያሉት ዮላንዳ “ብሔራዊ ቡድኑ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ስለ እኩልነት ብዙ ነገር አሳይተውናል” የሚል ሐሳብ አክለዋል።
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን “በአስቸኳይ ለመመልከት” ልዩ ጠቅላይ ስብስባ ጠርቷል።
በኢንስታግራም ሐሳቧን ያካፈለችው ሄርሞሶ የሩቢያሌስን ድርጊት “አልወደድኩትም” ብትልም ቆይታ በለቀቀችው መግለጫ የግለሰቡን ድርጊት ሳታወግዝ ቀርታለች።
ሰኞ ዕለት በቪድዮ መግለጫ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት “እኔ ክፉ አስቤ አይደለም። በወቅቱ በጣም ደስተኛ ስለነበርኩ ነው። ይቅርታ ጠይቅያለሁ። ከስህተቴ እማራለሁ። ፕሬዝደንት ስሆን በጣም መጠንቀቅ እንዳለብኝም ገብቶኛል” ብለዋል።
ሄርሞሶን ጎትተው ከንፈሯን የሳሙት ሩቢያሌስ ከበርካታ የስፔን መንግሥት ባለሥልጣናት ወቀሳ እየደረሰባቸው ነው።
የስፔን የእኩልነት ሚኒስትር አይሪን ሞንቴሮ ይህ “ሴቶች በየቀኑ የሚያሳልፉት ወሲባዊ ጥቃት መገለጫ ነው” ሲሉ የስፖርት ሚኒስትሩ ሚኬል አይሴታ ደግሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ድርጊት “ተቀባይነት የሌለው” ነው ብለዋል።
በይነ መረብ ላይ የተሠራጩ ምስሎች እንደሚያሳዩት የተከበሩ ሰዎች በሚቀመጡበት ሥፍራ ከፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ እና ከስፔኗ ንግሥት ሌቲዚያ አጠገብ የተቀመጡት ሩቢያሌስ ስፔን ዋንጫ መብላቷ ሲረጋገጥ መራቢያ አካላቸውን አካባቢ ሲይዙ ያሳያል።












