የዩናይትድ ሴት ደጋፊዎች ግሪንውድ ወደ ክለቡ ከተመለሰ ዩናይትድን መደገፍ እናቆማለን አሉ

ራቼል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እውቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ክለቡ ግሪንውድን መልሶ የሚቀበል ከሆነ ክለቡን መደፍ አቆማለሁ ብላለች።

የማንቸስተር ዩናይትድ ክለብ ሴት ደጋፊዎች ከቡድኑ ተገልሎ የቆየው ሜሰን ግሪንውድ ወደ ክለቡ እንዲመለስ የሚፈቅድ ከሆነ ድጋፍ እናቆማለን አሉ።

የግሪንውድን ወደ ክለቡ የመመለስ ውሳኔ የሚቃወሙ የዩናይትድ ሴት ደጋፊዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ ዩናይትድ ተጫዋቹን እመልሳለሁ የሚል ከሆነ “ሴት በመሆናችን ረብ ለሽ መሆናችንን” ይንገረን ብለዋል።

በእግር ኳስ ሕይወቱ ብዙ ተስፋ የነበረው የዩናይትዱ አጥቂ የአስገድዶ መድፈር እና የጾታዊ ጥቃት ክስ ከቀረበበት በኋላ ከክለቡ እና ከብሔራዊ ቡድኑ ተገልሎ እንዲቆይ ተደርጓል።

ይሁን እንጂ ግሪንውድ የቀረቡበት ክሶች በሙሉ ውድቅ መደረጋቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ተጫዋቹን ወደ ቡድኑ ለመመለስ ውሳኔ እሰጣለሁ ብሏል።

ክለቡ እስካሁን ተጫዋቹን በተመለከተ የመጨረሻ ውሳኔ አልሰጠሁም ይላል። ክለቡ ተጫዋቹን ለመመለስ ሂደት ላይ ያለ ቢመስልም በዩናትድ ቤት ውስጥ ያለው የከረረ ክርክር ውሳኔው እንዲዘገይ አድርጓል።

ምንም እንኳ የ21 ዓመቱ እግር ኳስ ተጫዋች የቀረቡበት ክሶች ውድቅ ቢደረጉም በሴት የፍቅር ጓደኛው ላይ ያደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ የተባሉ ፎቶግራፎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መሰራጨታቸው ብዙዎች በመልካም ስሙ አያስታውሱትም።

ከእነዚህ መካከል እውቋ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ እና የዩናይትድ ደጋፊ ራቼል ሪሌይ ክለቡ ግሪንውድን መልሶ የሚቀበል ከሆነ ክለቡን መደፍ አቆማለሁ ብላለች።

“ግሪንውድ በክለቡ የሚቆይ ከሆነ ቡድኑን መደገፍ አይቻለኝም” ብላለች ራቼል።

የዩናትድ ሴት ደጋፊዎች
የምስሉ መግለጫ, ዩናይትድ ከዎልቭስ ጋር ጨዋታውን ከማድረጉ በፊት ሴት የቡድኑ ደጋፊዎች ከስታዲየሙ ፊት ተጫዋቹ እንዳይመለስ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዩናይትድ ከዎልቭስ ጋር የመጀመሪያውን የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከማድረጉ በፊት ሴት የቡድኑ ደጋፊዎች ከስታዲየሙ ፊት ተጫዋቹ እንዳይመለስ ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ሴት ደጋፊዎቹ ክለቡ ሴቶች ላይ ለሚቃጡ ጾታዊ ጥቃቶች ክለቡ ምንም አይነት ትዕግስት እንዳይኖረው አሳስበዋል።

ቢቢሲ ስፖርት የተቃውሞ ሰልፉን በተመለከተ የግሪንውድ ጠበቆችን አስተያየት ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።

በዩናይትድ እስከ 2025 ድረስ ውል ያለው ግሪንውድ ክሱ ከቀረበበት ግዜ ወዲህ ከክለቡ ከመገለሉ በተጨማሪ በልምምድ ሜዳም ተሳታፊ ሳይሆን ቆይቷል።