ቤላሩስ ጸረ-ሩሲያ የሆኑ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግጥሞችን “ጽንፈኛ” ስትል አወገዘች

ሉካሼንኮ እና ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቤላሩስ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ እና ጸረ-ሩሲያ የሆኑ ሁለት ግጥሞችን ጽንፈኛ ናቸው ስትል አወጀች።

በፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ አስተዳደር የተወገዙት ቪንሰት ዱኒን-ማርትሲንኬቪች የተባለው ገጣሚ ግጥሞች በወቅቱ የነበረውን የሩሲያ ግዞት የሚቃወሙ ነበሩ።

ግጥሞቹን ጽንፈኛ ብሎ የማገዱ ትዕዛዝ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ተቀናቃኞቻቸውን ለማፈን ከሚወስዷቸው እርምጃዎች መካከል ተደርጎ ተወስዷል።

ሉካሼንኮ እአአ 2020 ተካሂዶ ተጨበርብሯል ተብሎ የሚታመነውን ምርጫ አሸንፊያለሁ ካሉ በኋላ ተቃዋሚዎችን በማሳደድ ተጠምደዋል።

ፕሬዝዳንቱን የሚተቹ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች ቤላሩስ ከሩሲያ ጋር ያላትን የቀረበ ወዳጀነት አይወዱትም። የሉካሼንኮ አብዛኛዎቹ ተቃዋሚዎች አሁን ላይ አገር ጥለው ሸሽተዋል አልያም በእስር ቤት እየማቀቁ ነው።

ፕሬዝዳንቱ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለፈጸመችው ወረራ ድጋፋቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

በቤላሩስ መዲና የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ትናንት ይፋ እንዳደረገው ‘ዘ ዊንድስ አር ፍሎቲንግ’ እና ‘ኮንቨርዜሽን ኦፍ አን ኤልደርሊ ማን’ የተባሉት ሁለቱ ግጥሞች “ጽንፈኛ ጽሁፎች ናቸው” ተብለው ተወግዘዋል።

ግጥሞቹ የተጻፉት እአአ 1863 የቤላሩስ እና ፖላንድ ዜጎች በሩሲያ አስተዳደር ላይ ካስቱስ ካሊኖውስኪ የተባለውን አመጽ ባካሄዱበት ወቅት ነበር።

ገጣሚ ቪንሰት ዱኒን-ማርትሲንኬቪች በወቅቱ በግጥም ስራዎቹ “ለባለስልጣናት መጥፎ የሆነ” መልዕክቶችን በማሰራጨት ተከሶ ነበር። ገጣሚ ዱኒን-ማርትሲንኬቪች በቁጥጥር ሥር ውሎ በእስር ማቅቆ ነበር።

ዛሬ ላይ የገጣሚው ስራዎች በትምህርት ሰርዓት ውስጥ ተካተው መማሪ ሆነዋል እንዲሁም የተውኔት ስራዎቹ በመደበናነት ለተመልካቾች ይቀርባሉ።

በቤላሩስ ዝነኛ የሆነው ዱኒን-ማርትሲንኬቪች በስሙ በርካታ ጎዳናዎች ተሰይመውለታል።

ሌክስታ የተባለው መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ከገጣሚው ስራዎች በተጨማሪ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተጻፉ በርካታ መጽሐፎችም በቤላሩስ የተወገዙ ናቸው ተብሎ ስለመታወጁ ጨምሮ ዘግቧል።