የረሃብ አድማ ላይ የነበሩት የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ እናት ከሆስፒታል ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሉዊስ ሩቢያሌስ እናት ከሆስፒታል ወጥተዋል።
እናት አንግሌዝ ቤሃር ባለፈው ሰኞ የረሃብ አድማ መትተው አንድ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ራሳቸው ላይ በር ቆልፈው ነበር።
“ልጄ ላይ እየደረሰ ያለው በድል ይቁም” ብለው አድማ የመቱት እናት፣ ረቡዕ ዕለት ሆስፒታል መግባታቸው ተሰምቷል።
ሩቢያሌስ የስፔን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ሲያነሳ ጄኒ ሆርሞሶን ከንፈሯ ላይ በመሳማቸው ታላቅ ነቀፌታ ገጥሟቸዋል።
“ሄርሞሶ፤ ሰውዬው ያለፈቃዴ ነው የሳመኝ” ስትል በወቅቱ የነበረው ክስተት እንደጎረበጣት ተናግራለች።
ይህን ተከትሎ ሩቢያሌስ ላይ የደረሰው ትችት እና ወቀሳ ያሳሰባቸው እናት ልጃቸውን ደግፈው የረሃብ አድማ መትተዋል።
ቤሃር በድቡባዊ ስፔን በምትገኘው የጠረፏ ከተማ ሞትሪል ካለ አንደ ቤተ-እምነት ገብተው ቆይተዋል።
ኢአፍኢ ለተሰኘው የዜና ወኪል የተናገሩት እናት “ልጄን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ ደም የጠማቸው ሰዎች እያሳደዱብኝ ነው፤ ይህ አይገባውም” ብለዋል።
ነገር ግን አንድ አባት አንቶኒዮ የተባሉ ቄስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የሩቢያሌስ እናት ረቡዕ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
እናትየው “በሙቀቱ እና በሌሎች ተፅዕኖዎች ምክንያት ጥሩ ስሜት ላይ አልነበሩም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአገሪቱ መገናኝ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ ቤሃር ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ በልጃቸው ታጅበው ከሆስፒታል ወጥተዋል።
የዓለም እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ፊፋ ባለፈው ቅዳሜ ሩቢያሌስን ከማንኛውም የእግር ኳስ ክንውን አግዷቸዋል።
ሩቢያሌስ በፊፋ ከመታገዳቸው በፊት በፌዴሬሽኑ ስብሰባ ላይ ተገኝተው “ሥልጣኔን አልለቅም” ሲሉ ፈርጠም ያለ ንግግር አሰምተዋል።
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክልላዊ መሪዎች ጄኒ ሆርሞሶን የሳሙት ፕሬዝዳንት ሉዊስ ሩቢያሌስ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ጠይቀዋል።
ሰኞ ዕለት በርካታ ሰዎች በሴቶች ንቅናቄ ቡድኖች የተዘጋጀውን ሰልፍ ተቀላቅለው በማድሪድ ጎዳናቸው ላይ በመውጣት ከሄርሞሶ ጎን መሆናቸውን እና የሩቢያሌስን ድርጊት ደግሞ እንደሚያወግዙት ሲገልጡ ታይተዋል።
ፊፋ ሩቢያሌስን ባገደ ወቅት ፕሬዝዳንቱም ሆነ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ተጫዋቿን እንዳያገኙት ያዘዘ ሲሆን፣ ፌዴሬሽኑ ደግሞ ሄርሞሶን እከሳለሁ ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የስፔን የስፖርት ግልግል ችሎት ሰኞ ስብሰባ አድርጎ ሰውዬው ከሥልጣን እንዲነሱ ሐሳብ ቢያቀርብም ውሳኔውን እስካሁን ይፋ አላደረገም።
የስፔን ከፍተኛ የወንጀል ችሎት ድግሞ ሄርሞሶ የሰጠችውን “ግልጽ” አስተያየት ተከትሎ ምርመራ መክፈት አስፈላጊ ሆኗል ብሏል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ኃላፊ አሌክሳንደር ቼፌሪን የሩቢያሌስ ድርጊት “ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
በሌላ በኩል አዲስ የተለቀቀ አንድ ቪድዮ እንደሚያሳየው ሄርሞሶ እና የቡድን አጋሮቿ ከጨዋታው በኋላ ባስ ውስጥ ሳሉ ስለሰውየው ድርጊት እያወሱ ሲሳሳቁ ታይተዋል።












