በኡጋንዳ ለገበያ የሚቀርቡ እንስሳትን ለማደለብ የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒት ጥቅም ላይ ውሏል ተባለ

አሳማ

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES

በኡጋንዳ ከእአአ 2014 ጀምሮ ለገበያ የሚቀርቡ እንስሳትን ለማደለብ የጸረ ኤችአይቪ መድሃኒት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል ተብሏል።

የኡጋንዳ ብሔራዊ መድኃኒት ባለሥልጣን የጸረ ኤችአይቪ መድኃኒቱ እንስሳት ለማፋፋት ጥቅም ላይ መዋሉን እያውቀ ለሕዝብ ማስጠንቀቂያ አልሰጠም የሚል ክስ ቀርቦበታል።

የተቋሙ ከፍተኛ መድኃኒት መርማሪ አሞስ አቱማንያ በፓርላማ እንደተናገሩት፣ ለኤችአይቪ ሕሙማን የሚሰጠው መድኃኒት አሳማ እና ዶሮ ለማደለብ እና ለማከም ውሏል።

የእንስሳቱን ሥጋ የሚመገቡ ሰዎች ከሥጋው ጋር መድኃኒቱን ሰውነታቸው ውስጥ ሲገባ መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም አደገኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ከተናገሩ በኋላ የኡጋንዳ ብሔራዊ መድኃኒት ባለሥልጣን የመርማሪውን ንግግር ለማጣጣል ሞክሯል።

ባለስልጣኑ ጤና ላይ ጉዳት ቢያስከትል ኖሮ ለሕዝብ ያሳውቅ እንደነበር ገልጿል። መድኃኒት ላይ ቁጥጥር ማድረግ ኃላፊነቱ ቢሆንም እንስሳት ምን ተመገቡ የሚለው የመቆጣጠር ኃላፊነት እንደሌለው ገልጿል።

በማኬሬሬ ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ከሦስት እጥፍ በላይ በዶሮ ውስጥና 50 በመቶ አሳማ ውስጥ የኤችአይቪ መድኃኒት ተገኝቷል።

ሥጋው ለናሙና የተወሰደው ከመዲናዋ ካምፓላ እና ሊራ ከተባለች ከተማ ገበያዎች ነው።

መርማሪው በምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ ብሔራዊ ተቋሙ በ2014 በእንስሳት ማደለቢያ ስለ ኤችአይቪ መድኃኒት ጥቅም ላይ መዋል ምርመራ አድርጓል።

ሆኖም የአገሪቱን የምግብ የውጭ ገበያ ላለመጉዳትና “ነገሩን ላለማጋነን” ሲል ለሕዝብ ሳያሳውቅ ቀርቷል።

“ሁኔታውን መቆጣጠር የምንችልበት ሌላ መንገድ ለማግኘት እየሞከርን ነበር” ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው ጥናት እንደሚያሳየው መድኃኒቱ የተሰጣቸው አሳማዎች “በፍጥነት ያድጋሉ፣ ይፋፋሉ፣ ቶሎም ይሸጣሉ”።

ሥጋውን ለሚበሉና በኤችአይቪ ለሚያዙ ሰዎች ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር መርማሪው ገልጸዋል።

“ሥጋውን መብላት ሰውነት እነዚህን መድኃኒቶች እንዲላመድ እና እንዲቋቋም ያደርጋል። ለወደፊት መድኃኒቱን መውሰድ ሲያስፈልግ መድኃኒቱ አልሠራም ይላል” ሲሉ አብራርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በኡጋንዳ ወደ 1.4 ሚሊዮን ሰዎች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ይገኛል።

የኡጋንዳው ብሔራዊ ተቋም ምርመራ ሲያደርግ የደረሰበት መድኃኒቱ የዶሮዎችን ‘ኒውካስል’ ሕመም፣ ‘ስዋይን ፊቨር’ እና በአሳማ ‘ፒግ ኢቦላ’ የተባሉ ሕመሞችን ለማከም እንደሚውል ነው።

“መድኃኒቶቹ አደጋ ቢያስከትሉ ለሕዝብ እናሳውቅ ነበር” ሲሉ ለምን መረጃውን ለሕዝብ እንዳላሳወቁ የተቋሙ ቃል አቀባይ አስረድተዋል።

“የኡጋንዳውያንን ጤና ከመጠበቅ ወደኋላ አንልም” ሲሉም አክለዋል።

ከዚህ ቀደም መድኃኒት ያላግባብ ጥቅም ላይ ያዋሉ መታሰራቸውንም ተናግረዋል።