ኪም ጆንግ ኡን ‘ኒውክሌር መሣሪያ የሚሸከም ሰርጓጅ መርከብ’ አስመረቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አዲስ ሰርጓጅ መርከብ አስመርቀዋል።
ፒዮንግያንግ እንደምትለው አዲሱ ሰርጓጅ መከርብ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመሸከም አቅም ያለው ነው።
የሃገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው አዲሱ ሰርጓጅ መርከብ የሃገሪቱን የኒውክሌር አቅም “በፍጥነት” ከፍ ያደርገዋል።
ሰሜን ኮሪያ ለረዥም ጊዜ ኒውክሌር ጦር መሣሪያ ተሸክሞ መንቀሳቀስ የሚችል ሰርጓጅ መርከብ የመገንባት ዕቅድ ነበራት።
ብሔራዊው ጣቢያ በለቀቃቸው ፎቶዎች ላይ ኪም በባሕር ኃይል መኮንኖች ተከበው፤ ከአንድ ግዙፍ ሰርጓጅ መርከብ አጠገብ ተቀምጠው ይታያሉ።
ይህ ጥቁርና ግዙፍ ሰርጓጅ መርከብ ነው ኒውክሌር ተሸክሞ መንቀሳቀስ እንደሚችል የተነገረለት።
ኪም፤ ለበርካታ ዓመታት ይህን ሰርጓጅ መርከብ የመሥራት ሕልም ነበራቸው። የኒውከሌር ጦር መሣሪያ ፕሮግራማቸው ትልቅ አካል አድርገውም ይቆጥሩታል።
ሰርጓጅ መርከቦች ከሰጠሙ በኋላ ያሉበትን ሥፍራ መለየት ከባድ ነው። ይህ ማለት ፒዮንግያንግ ያሏት የየብስ ጦር መሣሪያዎች ቢወድሙ ከባሕር ጥቃት መሰንዘር ትችላለች ማለት ነው።
ነገር ግን ይህ ሰርጓጅ መርከብ ሥር ይጀምር አይጀምር የሚታወቅ ነገር የለም።
ሰሜን ኮሪያ ይህ መርከብ የኒውክሌር ጦራ መሣሪያ መተኮስ ይችላል ወይ የሚለውን ሙከራ ይፋ አላደረገችም።
የሰሜን ኮሪያው መሪ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ወር የሩሲያውን ፕሬዝደንት ፑቲን ሊያገኙ አቅደዋል።
የዩናትይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሁለቱ መሪዎች የሚገናኙት ኪም ለፑቲን በዩክሬን ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውል የጦር መሣሪያ ለማቅረብ ነው።
በምትኩ ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት አለ።
ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት በርካታ የሚሳዔል ሙከራዎች ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ ዘንድሮም በተመሳሳይ ሙከራ ማድረጓን ተያይዛዋለች።
ኪም ጆንግ ኡን በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የባለስቲክ እና ክሩዝ ሚሳዔል ሙከራዎችን በአካል ተገኝተው ታድመዋል።












