የሰሜን ኮሪያው አየር መንገድ ከኮቪድ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ በረረ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሰሜን ኮሪያው አየር መንገድ ከኮቪድ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ በረራ አደረገ።
በአገሪቱ መንግሥት የሚተዳደረው "ኤር ኮሪዮስ" የተባለው አየር መንገድ በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ በረራው ወደ ቻይና ቤይጂንግ አቅንቷል።
ከሰሜን ኮሪያ መዲና ፒዮንግያንግ ተነስቶ ቤይጂንግ በደረሰው የበረራ ቁጥር ጄኤስ151 አውሮፕላን የተሳፈሩት እንማን እንደሆኑ እና ምን ያህል መንገደኞችን እንደተሳፈሩ አልታቀም።
የበረራ መከታተያ ድረ-ገጹ ፍላይትራዳር24 እንዳሳየው 210 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው ሩሲያ ሰራሹ ቱፖልብ ቱ-204 አውሮፕላን ማክሰኞ ጠዋት ቤጂንግ አርፏል።
ሰሜን ኮሪያን በማስጎብኘት የሚታወቀውም ኮርዮ ቱርስ የተባለው የጉዞ ወኪል ከፒዮንግያንግ-ቤይጂንግ የበረራ መስመር ዳግም የተከፈተው ከአገር ውጪ ያሉ ሰሜን ኮሪያውያን ወደ አገራቸው መግባት እንዲችሉ ነው ብሏል።
በዚሁ የበረራ መስመር ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት ከቤይጂንግ ወደ ፒዮንግያንግ በተደረገው በረራም የሰሜን ኮሪያ ሰንደቅ አላማ ደረታቸው ላይ ያደረጉ እና ብዙ እቃ የሸከፉ በርካታ ሰዎች ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚበረውን አውሮፕላን ለመሳፈር ሲዘጋጁ ታይተው ነበር።
ትናንት ሰኞ የቻይና የውጭ ጉዳይ ቢሮ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ለሦስት ዓመት ተኩል ተቋርጦ የነበረው የኤር ኮርዮ የቤይጂንግ በረራ እንዲጀምር ፍቃድ መስጠቱን ይፋ አድርጓል።
የኮቪድ ወረርሽኝ መቀስቀስን ተከትሎ በሰሜን ኮሪያ ተቋርጠው የነበሩ ዓለም አቀፍ በረራዎች ገና መጀመራቸው ነው።
ባለፈው ሳምንት በካዛኪስታን በሚደረግ የቴክዋንዶ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ የሰሜን ኮሪያ አትሌቶች በጎረቤት አገር ቻይና በኩል አድርገው ወደ ካዛኪስታን አቅንተው ነበር።
ሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ደግሞ የኮሪያ ጦርነት የተኩስ አቁም ስምምነት 70ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለመገኘት የሩሲያ እና የቻይና ልዑካን ወደ ፒዮንግያንግ ተጉዘው ነበር።
ይህ የሩሲያ እና የቻይና ልዑካን ቡድን በአገሪቱ ከእአአ 2020 በኋላ በሰሜን ኮሪያ መንግሥት ይፋዊ ግብዣ ወደ አገሪቱ የገባ የመጀመሪያው የውጭ አገር ልዑክ ነው።












