የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን መሪ አፍሪካን በበለጠ ነጻ እያደረግኩ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Telegram/Grey Zone
የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) መሪ ዮቭጌኒ ፕሪጎዢን በአገሩ ላይ ያስነሳው ነውጥ ከከሸፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መልዕክቱን በቪዲዮ አስተላልፏል።
ቪዲዮው ፕሪጎዢን አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኝ የሚጠቁም ቢሆንም የት እንደተቀረጸ ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።
ወታደራዊ መለዮ ለብሶ የሚታየው መሪ ቡድናቸው ቫግነር አፍሪካን በበለጠ ነጻ እያደረገ ነው ሲልም ተናግሯል።
ይህንን መልዕክት የያዘው ቪዲዮም ከቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) ጋር ግንኙነት ባላቸው የቴሌግራም ገጾችም ላይ ተለጥፏል።
የሩሲያ ቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) በአፍሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች እንዳሉት የሚታመን ሲሆን በሰፈረባቸውም አገራት በትርፋማ ንግዶች እየተሳተፈ ስለመሆኑ ይነገራል።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ በተለያዩ የመብት ተሟጋቾች የጦር ወንጀሎችን በመፈጸም የሚከሰሰው የዚህ ቡድን ተዋጊዎች በዋናነት በማሊ እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ይገኛሉ።
ባለፈው ወር ዩናይትድ ኪንግደም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙ ሁለት የቫግነር ኦፕሬሽን ኃላፊዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
ለዚህም ምክንያቱ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ማሰቃየት እና ግድያ ፈጽመዋል በሚል ነው።
የቫግነር ተዋጊዎች በአፍሪካ ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ ሕገ ወጥ የወርቅ ስምምነቶችን በማድረግ ራሳቸውን እያበለጸጉም ይገኛሉ ስትል አሜሪካ ትከሳቸዋለች።
ይቭጌኒ ፕሪጎዢን በዚህ ቪዲዮ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት በአህጉሪቱ ውስጥ በማዕድን ፍለጋ እንዲሁም እስላማዊ ታጣቂዎችን እና ሌሎች ወንጀለኞችን በመዋጋት ላይ እንደሆነም ተናግሯል።
“በአሁኑ ወቅት በስራ ተጠምደናል። የሙቀት መጠኑ ከፍተኛ ነው። ሁሉንም ነገር ወደነዋል። ቫግነር ወታደራዊ ክትትሎችን እንዲሁም ፍለጋዎችን ያካሂዳል። በዚህም ሩሲያን በሁሉም አህጉራት ታላቅ ያደርጋታል እንዲሁም አፍሪካን በበለጠ ነጻ ያደርጋታል” ሲልም ተናግሯል።
“ፍትህ እና ደስታ ለአፍሪካ ሕዝቦች፤ ለእስላማዊው መንግስት፣ ለአልቃይዳ እና ሌሎች አመጸኞች ሕይወታቸውን በቅዠት እየሞላነው ነው” ብሏል።
ቫግነር በአሁኑ ወቅት ምልመላ እያካሄደ እንደሆነ የተናገረው መሪው ቡድናቸው አሳካዋለሁ ያለውንና ቃል የገባውን ተግባርም እንደሚፈጽም አስረድቷል።
ይቭጌኒ ፕሪጎዢን ባለፈው ወር ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በነበረው የአፍሪካ- ሩሲያ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት አማካሪ አምባሳደር ፍሬዲ ማፑካ ጋር እጅ ሲጨባበጥ የሚያሳይ ፎቶግራፍም ወጥቷል።












