የሱዳን መፃዒ ዕድል በእጃቸው ያለው የጦር አበጋዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካርቱም እና በሌሎች የሱዳን ከተሞች የሚደረገው ውጊያ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሦስት ቀናትን ባስቆጠረው በዚህ ለስልጣን ሽሚያ በሚደረግ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ከመሞታቸው በተጨማሪ የሱዳንን መጻዒ ተስፋ ጥያቄ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
በዚህ ግጭት ዋነኛ ተሳታፊዎቹ ሁለት ኃይሎች ናቸው።
የአገሪቱ መደበኛ ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላት።
100ሺህ አባላት ያሉትን ይህን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላት የሚመሩት ደግሞ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ናቸው።
እጅግ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ "ሄሜቲ" የልዩ ኃይሉ መሪ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሱዳንን የሚያስተዳድረው የሉዓላዊ ምክር ቤት ሁለተኛ ሰው ናቸው።
ሄምቲ ቀውስ ውስጥ የገባችውን ሱዳን የመጠገን አቅም አላቸው። ነገር ግን የጦር አበጋዙ ከፍ ያለ ስልጣንን ይሻሉ። ለዚህም ነው ከአገሪቱ ጦር አዛዥ ጋር ሳይስማሙ ቀርተው ግጭት የተቀሰቀሰው።
ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የአገሪቱ ጦር መሪ እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ናቸው። አል-ቡሩሃን እና ሄምቲ የአብደላ ሃምዶክን ሲቪል አስተዳደር ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ ሱዳንን በሉዓላዊ ምክር ቤት ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል።
ሁለቱ ጀነራሎች ታዲያ ወደፊት በሱዳን የሲቪል አስተዳደር እንዲመሰረት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል። ሄምቲ የሚመሩት ፈጥኖ ደራሽ የልዩ ኃይል አባላትም ወደ አገሪቱ ጦር እንዲቀላቀል በመርህ ደርጃ ተስማምተዋል።
የሁለቱ ጦር ጀነራሎች ልዩነት ግን 100ሺህ አባላት ያሉት ልዩ ኃይል፣ የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል የሚለው ነው።
ሄምቲ ዳርፉር ላይ በተከሰተው የአማጺዎች እና ሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ ይከሰሳሉ። ከእአአ 2019 ጀምሮ ካርቱም ውስጥ በተካሄዱት ግድያዎች እጃቸው አለበት የሚሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው።
ሄሜቲ የዳርፉሩን ጭፍጨፋ በተመለከተ "እርምጃው ንጹሃንን ለመጠበቅ ሲባል አስፈላጊ ነበር" ሲሉ የካርቱሙን ጉዳይ ደግሞ ገለልተኛ ወገን ገብቶ ያጠናዋል፤ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሄሜቲ የቀድሞው የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር የቅርብ ሰው ነበሩ። ነገር ግን በአል በሽር ላይ ተቃውሞዎች ሲበረቱ ከቀድሞ መሪው ጋር የነበራቸውን ወዳጅነት ቀንሰዋል።
በአል በሽር አስተዳደር ላይ የተቃውሞ ሰልፎች ሲጀመሩ ከከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች መካካል ለተቃዋሚዎች ቀድሞ ድጋፍ በመስጠት ሄሜቲ የመጀመሪያው ናቸው። መንግሥትንም "ለዜጎች ተገቢ አገልግሎት በመስጠት ኑሯቸውን ሊያሻሽል ይገባል" ሲሉ ተደምጡ።
ሄምቲ ከአገሪቱ ጦር ጋር አብረው ፕሬዝዳንት አል በሽር ሥልጣን እንዲለቁ ካስገደዱ ከ2 ቀናት በኋላ የሱዳን ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ብቅ አሉ።
ምንም እንኳ የወታደራዊ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ቢሆኑም ከምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ጋር ሲደራደሩ የሚታዩት ግን ሄሜቲ ናቸው።
ከግብፅ፣ ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የሚሰጣቸው ድጋፍም ሌላኛው የሄሜቲ የኃይል ምንጭ ነው ይባላል። ሄምቲ ከዚህ ቀደም ወደ ሳዑዲ ዐረቢያ በመሄድ ከልዑል ሞሃመድ ቢን ሳልማንን አግኝተዋቸዋል።
ሄምቲ የሚመሩት ኃይል በሊቢያ እንዲሁም በየመን ከሳዑዲ መራሹ ኃይል ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል።
ከግመል ነጋዴነት ወደ ጦር አበጋዝነት
ሄሜቲ ከቻዳዊ የዐረብ ጎሣ ነው የተወለዱት።
ጦርነትን በመሸሽ በ1980ዎቹ በዳርፉር መኖር ጀመሩ። እ.አ.አ 2003 ላይ በዳርፉር ጦርነት ተቀሰቀሰ።
መብታችን ተረግጧል የሚሉ ጥቁር ነዋሪዎች አማፂ ቡድንን ፈጠሩ። የመንግሥት ወታደርም ጃንጃዊድ ከሚባለው ቡድን ጋር በመሆን ጥቃት ፈፀመ። በዚህም ግመል የሚያረቡ ሰዎች ተገደሉ፣ ሴቶች ተደፈሩ፣ ማንኛውንም ያገኙትንም ንብረት ዘረፉ።
ከ2005 ጀምሮም ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የዘር ፍጅት እና በንፁሃን ላይ በተከፈተ የጦር ወንጀል ጥናት አድርጓል። በዚህም በርካታ የሱዳን ባለሥልጣናት፣ የጃንጂዊድ እና የአማፂ ቡድኑ ጥፋተኛ ተብለዋል።
በሱዳንና ቻድ ድንበር ያለውን አካባቢ ከተቆጣጠሩት የዐረብ ጎሣዎች መካከል የሄሜቲ አጎት ጁማ ዶንጎሎ ዋናው ናቸው። ሄሜቲ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው የግመል ንግድ ይሠሩ የነበር ሲሆን በዳርፉር ጦርነት ወቅትም ለተዋጊዎች ግመል ያከራዩ ነበር። በዚህ ሥራቸው የንግድ ሰው እና ባለፀጋ መሆንም ችለዋል።
በ2003 የዳርፉር አማፂያን እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሄሜቲ አርብቶ አደሮችን በማደራጀት መንግሥትን እንዲያግዙ አድርገዋል። ከዓመት በኋላ ደግሞ ይህ ቡድን መደበኛ ወታደር መሆኑን መንግሥት ይፋ አደረገ። በዚህም ሄሜቲ በፕሬዝዳንት አል በሽር ድጋፍ አገኙ። ወዲያውም ዳርፉር አካባቢ ለሚገኘው የድንበር ጠባቂ ጦር መሪ ሆነው ተመረጡ።
በ2013 መደበኛ ሠራዊቱን ለማገዝ "ፈጥኖ ደራሽ ኃይል" ተቋቋመ። ከዓመት በኋላ ደግሞ ቡድኑ መደበኛ ሠራዊት እንዲሆን በመንግሥት እውቅና ተሰጠው። ተንታኞች እንደሚሉት ግን ጃንጂዊድን እንደገና ማቋቋም ነው።
የሰብዓዊ መብት ጥሰት
የመብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ሄምቲ ላይ የሚያቀርቡት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብዛት ተመዝዞ አያልቀም።
ዳርፉር ላይ በተፈጠረው የዘር ፍጅት፣ የጦር ወንጀለኝነትና በሰብዓዊ ቀውስ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽር በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ። በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ስማቸው ባይጠቀስም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን በግርፋት እና ሴቶች በብዛት እንዲደፈሩ በማድረግ ሄሜቲን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት እአአ በ2014/15 በተካሄደ አመፀኞችን የማፅዳት ዘመቻ መድፈር፣ ቤቶችን ማቃጠል፣ ነዋሪዎችን በጅምላ መግደል በሱዳን ወታደርና በጃንጃዊድ ሚሊሻዎች ተፈፅሟል። ሄምቲ ግን እርምጃው የተወሰደው የዳርፉር ንፁሃንን ለመጠበቅ ነው ይላሉ።












