ግብጽ የሱዳን ኃይሎችን ለማደራደር ጥያቄ አቀረበች

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ

ግብጽ እና ደቡብ ሱዳን በሱዳን እየተዋጉ ያሉትን ኃይሎች ለማደራደር ጥያቄ አቀረቡ።

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ከሱዳን ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር በመሆን የአገሪቱን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላቱን ለማደራደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የሱዳን ጎረቤት የሆኑት የግብጽ እና የደቡብ ሱዳን መሪዎች ትናንት እሁድ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ሁለቱን ኃይሎች ለማደራደር ይፋዊ ጥያቄ አቅርበዋል።

አል-ሲሲ እና የደቡብ ሱዳኑ አቻቸው ሳልቫኪር ከስልክ ንግግራቸው በኋላ፤ ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ንግግር ማድረግ አለባቸው” ስለማለታቸው በመግለጫቸው ተመልክቷል።

ሁለቱ አገራት የማደራደር ጥያቄን ያቅርቡ እንጂ ከተዋጊ ኃይሎች የተሰጣቸው ምላሽ ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።

በተያያዘ ዜና የመስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት ኢጋድ ሁለቱን ኃይሎች ለማደራድር ሦስት የአገራት መሪዎችን እንደሚልክ አስታውቋል።

የኢጋድ አባል አገራት የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የጂቡቲ ፕሬዝዳንቶች በተቻለ ፍጥነት ወደ ካርቱም እንዲላኩ ከስምምነት ደርሰዋል።

ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ዝግ በሆኑባት ሱዳን፤ ዊሊያም ሩቶ፣ ሳልቫ ኪር እና ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ካርቱም መቼ ሊደርሱ እንደሚችሉ ማወቅ አልተቻለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን በተያዙት የግብጽ ወታደሮች ጉዳይ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ከካይሮ ጋር ትብብር አድርጋለሁ ብሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላቱ ሜሮዌ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ የግብጽ ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል ብለው በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ ማስረጃ አውጥተው ነበር።

ይህን ተከትሎ የግብጽ መከላከያ ኃይል የጦር አባላቱ ሱዳን የተገኙት ከሱዳን ወታደሮች ጋር የጋራ ልምምድ ለማድረግ መሆኑን ገልጾ የጦር አባላቱ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከሱዳን ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገርኩ ነው ብሎ ነበር።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ፈጥኖ ደራሽ የልዩ ኃይል አባላቱ እጃቸውን የሰጡት የግብጽ ወታደሮችን አሳልፎ ለመስጠት ትብብር አደርጋለሁ ስለማለቱ ዘግቧል።

በግብጽ ያሉ የደኅንነት ባለስልጣናት በሱዳን ተይዘው የሚገኙ ወታደሮቻቸው ደኅንነትን ከወታደሮቹ ኃላፊ ማረጋገጫ ማግኘታቸውን ሮይተርስ ጨምሮ ዘግቧል።

ግጭት የማቆም ጥሪ

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የተለያዩ አካላት ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሁለቱ አካላት ከግጭት አባባሽ ድርጊቶች ተቆጥበው ወደ ሰላም ንግግር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ከአውሮፓ ኅብረት እና የአረብ ሊግ አገራት ግጭት በአስቸኳይ ቆሞ ተዋጊዎች ለንግግር እንዲቀመጡ ጠይቀዋል።

የአረብ ሊግ እና አሜሪካ ስልጣንን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ ንግግር መጀመር አለበት ብለዋል። የአፍሪካ ኅብረት ደግሞ ግጭት ለማስቆም የኮሚሽኑን ሊቀ መንበር ወደ ካርቱም እንደሚልክ አስታውቋል።

ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ሕብረት ግጭቱ በአስቸኳይ መቆም አለበት ያሉ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ደግሞ ጀነራል አል-ቡርሃን እና ጀነራል ዳጋሎን በስልክ ማነጋገራቸው ተገልጿል።