በመላው ዓለም እስከ 100 ዓመት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር እንዴት ጨመረ?

ዕድሜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆሴፋ ማሪያ ዳ ኮንሲካዎ 120 ዓመታቸው እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ።

ዕድሜያቸውን ያሳለፉት በእርሻ ነው። ብራዚላዊቷ 120ኛ ልደታቸውን ካከበሩ በኋላ አቅማቸው እየተዳከመ እንደመጣ ቤተሰቦቻቸው አስተውለዋል።

በተለይ ‘ሲጋራ ስጡኝ’ ማለት ሲያቆሙ ቤተሰቡ ግራ ተጋብቷል።

ጆሴፋ በአብዛኛው የሕይወት ዘመናቸው ሲጋራ አጭሰዋል። ዕድሜያቸው ሲገፋ ሲጋራ እንዲያቆሙ ቤተሰቦቻቸው ቢወተውቱም በጄ አላሉም።

እንዲያውም “ሲጋራ ካልሰጣችሁኝ ራሴ እየወጣሁ እገዛለሁ” ብለው ማስፈራራት ጀመሩ። በሕይት ካሉ የጆሴፋ አራት ልጆች አንዷ ሲሴራ እንደምትለው እናታቸው ሲጋራ መጠየቅ ሲያቆሙ ተደናግጠዋል።

ጆሴፋ 22 ልጆች የወለዱ ሲሆን፣ አሁን አራት ልጆቻቸው ናቸው በሕይወት ያሉት።

ባለፉት ዓመታት ጆሴፋ አቅማቸው እየተዳከመ መጥቷል።

በመንደራቸው የሚገኝ መገናኛ ብዙኃን “በዓለም በዕድሜ ትልቋ ሴት” ብሏቸዋል። የተወለዱት እአአ በ1902 ነው።

በጊነስ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን ለማስመዝገብ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።

ጆሴፋ ማሪያ ዳ ኮንሲካዎ 120 ዓመታቸው እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ
የምስሉ መግለጫ, ጆሴፋ ማሪያ ዳ ኮንሲካዎ 120 ዓመታቸው እንደሆነ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ

አሁን በዕድሜ ትልቋ ሴት ተብለው የተመዘገቡት የ118 ዓመቷ ፈረንሳዊቷ መነኩሴ አንድሬ ሲሆኑ፣ በዕድሜ ትልቁ ወንድ ደግሞ የ113 ዓመቱ ቬንዝዌላዊ ሁዋን ቪንሰንቴ ሞራ ናቸው።

ዕድሜያቸው ወደ 100 የተጠጋ ወይም ያለፈ ሰዎች ቁጥር በመላው ዓለም እየጨመረ መጥቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ጉዳዮች ተቋም እንደሚለው በ2021 (እአአ) ከ621,000 በላይ ሰዎች ቢያንስ እስከ 100 ዓመት ኖረዋል።

በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ቁጥሩ ከአንድ ሚሊዮን እንደሚልቅ ይጠበቃል።

በ1990 እዚህ ዕድሜ ላይ የደረሱት 92,000 ሰዎች ብቻ ነበሩ።

መድኃኒቶች ከመፈጠራቸው እንዲሁም ከተሻለ አመጋገብ እና አኗኗር ጋር በተያያዘ ሰዎች በሕይወት የሚቆዩበት ዘመን እየጨመረ መጥቷል።

በ1960ዎቹ የተወለዱ ሰዎች ወደ 52 ዓመት ገደማ ነበር የሚኖሩት።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በ2021 እስከ 100 ዓመት የመኖር መጠን 0.008 በመቶ ነበር።

አሁንም ቢሆን አማካይ የመኖሪያ ዕድሜ 73 ነው። ቁጥሩ ከአገር አገር የተለያየ ነው።

በጃፓን አማካይ መኖሪያ ዕድሜ 73 ሲሆን፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐሊክ ቁጥሩ ወደ 54 ዝቅ ይላል።

የሕዋስ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጃኔት ሎርድ “ብዙ ዓመት መኖር ጥሩ ኑሮ መግፋት ማለት አይደለም” ይላሉ።

አብዛኞቹ ወንዶች የመጨረሻዎቹን 16 የዕድሜያቸውን ዓመታት እንደ ስኳር እና መዘንጋት (dementia) ካሉ ሕመሞች ጋር በመታገል ሲያሳልፉ፣ በሴቶች ዘንድ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 19 ዓመታት ከፍ ይላል።

ዕድሜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ብዙ ዓመት የመኖር ምስጢር ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰዎችን በሕይወት መቆት የሚያጠኑ ሰዎች 110 ዓመት ስለሞላቸው ሰዎች (Supercentenarians) በተለየ ይመራመራሉ።

“እነዚህ ሰዎች በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከሚያሳዩት የተለዩ ናቸው። ለምን የተለዩ እንደሆኑ ገና አልታወቀም” ይላሉ ፕሮፌሰሯ።

እነዚህ ሰዎች ዕድሜያቸው ቢገፋም በአንጻራዊነት ጤነኛ ናቸው።

ብራዚላዊቷ የዕድሜ ባለጸጋ አዘውትረው የሕክምና ክትትል አያደርጉም። ሥጋ እና ጣፋጭም ይበላሉ።

“ትንሽ የማስታወስ ችሎታዋን እያጣች ነው። የምናንቀሳቅሳት እና የምናጸዳዳትም እኛ ነን። ነገር ግን ሲጋራ እያጨሰች እና የጉልበት ሥራ እየሠራች ይህን ሁሉ ዓመት መኖሯ ይገርመናል” ይላሉ የ76 ዓመት ልጃቸው።

ተመራማሪዎችን የሚያስገርመው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ያን ያህልም ‘ጤናማ’ የሚባል አኗኗር የገፉ አለመሆናቸው ነው።

በ2011 በአሜሪካ የሳይንስ መጽሔት የወጣ ጥናት እንደሚለው፣ 95 እና ከዚያ በላይ ዓመት የኖሩ አሜሪካውያን አይሁዳውያን ጤናን የሚጎዱ ልማዶች ያሉባቸው ናቸው።

60 በመቶ ሲጋራ ያጨሳሉ፣ ገሚሱ የሰውነታቸው ክብደት በሕክምና ከሚመከረው በላይ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማያደርጉ እና አትክልት መመገብ የማያዘወትሩ ናቸው።

በብሪግቶን ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፋርጋር “እነዚህ ሰዎች ልዩ ናቸው። ሰዎች ረዥም ዕድሜ ለመኖር እንዲያደርጉ ከምንመክረው በተቃራኒው ነው የሚኖሩት” ይላሉ።

እነዚህ ሰዎች ዕድሜያቸው የረዘመው በዘረ መላቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መላ ምቶች አሉ።

ምክንያቱም ዕድሜ የሚያሳጥሩ ጎጂ ልማዶች ሲጎዷቸው አይታይም።

በ2020 የታተመ ጥናት እንደሚጠቁመው ዕድሜ ሲገፋ የሚገጥሙ ሕመሞች ከዘረ መል ጋር የተያያዙ ናቸው።

100 ዓመት የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር መጨመር የሰው ልጆች ምናልባትም ከ100 ዓመት በላይም ሊኖሩ ይችላሉ ብለው ሳይንቲስቶች እንዲያስቡ አድርጓል።

100 ዓመት ዕድሜ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዕድሜ ባለጸጋዎች

በዓለም ትልቅ ሰው የተባሉት የፈረንሳዩዋ ጃኔ ካልሜት ከ120 ዓመት በላይ ኖረው በ1997 ነው ያረፉት።

በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በዚህ ምዕተ ዓመት የሰዎች በሕይወት መቆያ ዕድሜ ይጨምራል።

ሰዎች እስከ 125 እና 130ም ሊኖሩ ይችላሉ።

“በ2100 በሕይወት መቆያ ዕድሜ አሁን ካለው እንደሚበልጥ አያጠራጥርም። ሰዎች እስከ 126፣ 128 እና 130 ዓመት ይኖራሉ” ይላሉ የስታትስቲክስ ባመሉያው ማይክል ፔራስ።

በሰበሰቡት መረጃ መሠረት የጃኔ ካልሜት ዕድሜ አማካይ መሆኑ ወደ 68 በመቶ ይወርድና 127ኛ ልደታቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ይበዛሉ።

በዕድሜ የመቆየት ምስጢርን ለመፍታት ሳይንስ ገና ብዙ ይቀረዋል።

በኪንግስ ኮሌጅ ስለ እርጅና የሚያጠኑት ዶ/ር ሪቻርድ ሲዎ እንደሚሉት ሰዎች ብዙ ዓመት እንዲኖሩ ምን ዓይነት ሕይወት መግፋት እንዳለባቸው መታወቅ አለበት።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለምን የሞሉት 65 ዓመት የሆኑ እና ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሰዎች ናቸው ይላል።

“ብዙ ዓመት መኖር እንዴት እንችላለን? ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን እንዴት ጤነኛ ሆነን ረዥም ዓመት መኖር እንችላለን? የሚለውም ይነሳል። ይህ ጥያቄ ከተመለሰ ረዥም ዕድሜን ጤነኛ ሆነን እንገፋለን” ይላሉ ተመራማሪው።

ኸልፕኤጅ የተባለው ድርጅት በመላው ዓለም አረጋውያንን ይረዳል።

የተቋሙ ቃል አቀባይ ኤድዋርዶ ኪለን “ጤነኛ የሆኑ አረጋውያን ለማኅበረሰብ ይጠቅማሉ” ይላሉ።