በካርቱም በፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና በአገሪቱ ጦር መካከል የሚደረገው ውጊያ ለሦስተኛ ቀን ተጠናክሮ ቀጠለ

ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የሱዳን ከተሞች በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ የሚሊሻ አባላት መካከል የሚደረገው ውጊያ ለሦስተኛ ቀን ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በውጊያው ከ100 ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ1ሺህ 100 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን የዶክተሮች ስብስብ የሆነ ኮሚቴ ተናግሯል።
የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ 83 ሰዎች መሞታቸውን አረጋገጫለሁ ብሏል። ከሟቾቹ መካከል ሦስቱ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሠራተኞች ናቸው።
ግድያውን ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሱዳን ያለኝን ስራ አቋርጫለሁ ብሏል።
ሁለቱም ተዋጊ ኃይሎች በካርቱም እንደ አየር ማረፊያ፣ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችን፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ቤተ-መንግሥትን ተቆጣጥረናል ሲሉ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መረጃ ሲያወጡ ነበር።
ተዋጊዎቹ ኃይሎች ትናንት እሁድ ረፋድ ላይ ለሰብዓዊነት ሲባል ለጥቂት ሰዓታት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት አድርገው ነበር።
በዚህ የተኩስ አቁም ጊዜ ውስጥ የቆሰሉ ወደ ሕክምና ተጓጉዘዋል።
ሀኪሞች በካርቱም ሆስፒታሎች ያለው ሁኔታ እጅግ ከባድ መሆኑን እና ውጊያው ባለሙያዎች እና የህክምና ግብዓቶች ወደ ጤና ተቋማት እንዳይደርሱ እክል መሆኑን እየተናገሩ ነው።
የግጭቱ ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?

በግጭቱ ውስጥ ሁለት ዋነኛ ተዋናዮች አሉ። ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ።
ላለፉት ሦስት ቀናት ውጊያ ገጥመው የሚገኙት በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መደበኛ ጦር ሠራዊት እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ የሚሊሻ አባላት ናቸው።
እነዚህ ሁለት ጀነራሎች እአአ 2021 ላይ የሲቪል መንግሥቱ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ ሱዳንን ሉዓላዊ ምክር ቤት በሚል ሲመሩ ቆይተዋል።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ዋነኛ ሰው ሲሆኑ የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ደግሞ ምክትል ናቸው።
እነዚህ ሁለት የጦር ጀነራሎች በሱዳን ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ተስማምተናል ብለው ነበር። እንዲሁም የልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አገሪቱ ጦር እንዲቀላቀሉ ተስማምተዋል።
ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጀነራል የሚመሩት 100ሺህ አባላት ያሉት ልዩ ኃይል፣ የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል በሚለው ላይ ሁለቱ ጀነራሎች መግባባት አልቻሉም።
ጀነራል አል-ቡርሃን የሚሊሻ አባላቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ወደ አገሪቱ ጦር መግባት አለባቸው ሲሉ ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ግን የሚመሩት ኃይል ጦሩን የሚቀላቀለው ከ10 ዓመት በኋላ ነው ይላሉ።
በዚህ ልዩነት ውጥረት ሰፍኖ ከቆየ በኋላ ግጭት በካርቱም እና በሌሎች ከተሞች ተቀስቅሷል።
እሁድ እና ሰኞ ንጋት ላይ ልዩ የሚሊሻ ኃይል አባላቱ በካርቱም ቁልፍ ቦታዎችን መቆጣጠራቸው ተዘግቧል። ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥት፣ የኦማድሩማን ከተማ፣ የዳርፉር ግዛት እና በሰሜናዊ አገሪቱ የምትገኘው ሜሮዌ አየር ማረፊያን መያዛቸው ተዘግቧል።
የአገሪቱ ጦር በበኩሉ የልዩ ኃይል አባላቱ ቁልፍ ቦታዎችን አልያዙም ይላል። ሮይተርስ የዜና ወኪል የዓይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው የአገሪቱ ጦር በጦር ጀቶች አማካይነት የልዩ ኃይል አባላቱ ጦር ሰፈሮችን በመደብደብ አንዳንድ ስፍራዎችን እየተቆጣጠር ነው።
“ለ24 ሰዓታት አልተኛንም”
በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙት የካርቱም ነዋሪዎች በፍርሃት እና ደንጋጤ ውስጥ ገብተዋል።
“በጣም ፈርተናል። ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ስላለ በዚያም የተነሳ ቤታችን እየተናወጠ ለ24 ሰዓታት አልተኛንም” ስትል ሁዳ የተባለች የካርቱም ነዋሪ ለሮይተርስ ተናግራለች።
ድንገት የተቀስቀሰው ግጭት ከቤታቸው ርቀው ያሉ ሰዎችን መንቀሳቀስ እንዳይችሉ አድርጓቸዋል።
ሁዳ “የስኳር ሕመምተኛ አባት አለኝ። ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት ያልቅብናል ብዬ እፈራለሁ” ብላለች።
ካሎሆድ ካሃኢር የተባሉ ነዋሪ ደግሞ “ሁሉም ሰላማዊ ሰዎች ከቤት እንዳይወጡ ተነግሯቸዋል። ግን ይሄ የማንንም ደኅንነት ማረጋገጥ አይችልም” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።












