በሱዳን እየሆነ ስላለው ቀላል መግለጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታፍኖ የቆየው የስልጣን ሽሚያ ውጥረት ድንገት ፈንድቶ በሱዳን መዲና እና በበርካታ ከተሞች ግጭት ቀስቅሷል።
ግጭት እየተካሄደ ያለው በመደበኛ የአገሪቱ ጦር አባላት እና ራፒድ ሰፖርት ፎርስ ተብሎ በሚጠራ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላት መካከል ነው።
በሱዳን እየሆነ ስላለው ማወቅ የሚገባዎ እነሆ።
የግጭቱ ዳራ ምንድነው?
እአአ 2021 ላይ የሲቪል መንግሥቱ ከስልጣን ተወገደ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሱዳን በሉዓላዊ ምክር ቤት በሁለት የጦር ጀነራሎች ስትመራ ቆይታለች።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ዋነኛ ሰው ሲሆኑ የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ደግሞ ምክትል ናቸው።
የግጭቱ ማዕከልም እነዚህ ሁለት የጦር ጀነራሎች ነው። ጀነራሎቹ በሱዳን ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ተስማምተናል ብለዋል። እንዲሁም የልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አገሪቱ ጦር እንዲቀላቀሉ ተስማምተዋል።
ልዩነታቸው ግን መቼ እና ማን በሚለው ነው።
ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጀነራል የሚመሩት 100ሺህ አባላት ያሉት ልዩ ኃይል የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል በሚለው ሁለቱ ጀነራሎች መግባባት አልቻሉም።
ግጭቱ እንዴት ጀመረ?
ምንም እንኳ ከግጭቱ መቀስቀስ በፊት ውጥረት ነግሶ የነበረ ቢሆንም ግጭት ይቀሰቀሳል ተብሎ አልተጠበቀም። ሱዳናውያን የጦር ጀነራሎቹ ልዩነቶቻቸውን በንግግር ይፈታሉ ብለው ጠብቀው ነበር። ያ ግን ሳይሆን ቀረ።
የመጀመሪያዋን ጥይት የትኛው ወገን እንደተኮሰ ግልጽ አይደለም። ግጭት ይከሰታል ብለው ያለጠበቁት ሱዳናውያን እራሳቸውን ከተባራሪ ጥይት ለመጠበቅ ከለላ ፍለጋ ሲሯሯጡ ታይተዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላቱ እነማን ናቸው?
አርኤስኤፍ የሚባለው ኃይል የተመሰረተው እአአ 2013 ነው ይባል እንጂ መሠረቱ አማጺያንን በዳርፉር ሲዋጋ የነበረው ጃንጃዊድ ሚሊሻ ነው።
ሄምቲ ከሱዳን ተሻጋሮ በሊቢያ እና በየመን ጦርነት የተሳተፈ ጠንካራ ኃይል ገንብተዋል። ቡድኑ በሱዳን የሚገኙ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራዎችን ይቆጣጠራል።
ይህ ቡድን በተሳተፈባቸው ውጊያዎች በከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከሰሳል። እአአ 2019 ላይ 120 ተቃዋሚዎችን በመግደልም የሄምቲ ኃይል ተጠያቂ ይደረጋል።
ከአገሪቱ ጦር ቁጥጥር ውጭ ያለው ይህ ኃይል አገሪቱ እንዳትረጋጋ ምክንያት ነው ሲባል ቆይቷል።
በቀጣይ ምን ሊፈጠር ይችላል?
ትናንት የጀመረው ግጭት ቀጥሎ የሚካሄደ ከሆነ አገሪቱን ወደለየት ቀውስ ሊከት ይችላል።
ሁለቱ የጦር ጀነራሎች እየሰጧቸው ያሉት አስተያየቶች ነገሮችን የሚያባብስ ይመስላል።
ጀነራል አል-ቡርሃን የሄምቲ ጦር ስልጣን ለመያዝ እየጣረ ነው ሲሉ ሄምቲ ደግሞ ‘ወንጀለኛ’ የሆኑት አል-በሩሃን ‘ይገደላሉ’ አልያም ‘ሕግ ፊት ይቀርባሉ’ ሲሉ ለአል ጀዚራ በስልክ ተናግረዋል።
ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ሁለቱ የጦር ጀነራሎች ወደ ንግግር በአስቸኳይ እንዲመለሱ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ።
እስከዚያው ግን ሱዳናውያን የአገራቸው እጣ ምን ሊሆን ማውቅ በሚያዳግት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ዳግም ሕይወትን ለማስቀጠል ይገደዳሉ።












