የፑቲን ቃል አቀባይ ልጅ በዩክሬን ዋግነር ቡድን ተቀላቅሎ መዋጋቱ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, RT
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ ልጅ በዩክሬን ዋግነርን ተቀላቅሎ ለስድስት ወራት መዋጋቱን ተናገረ።
የ33 ዓመቱ ኒኮላይ ፔስኮቭ፤ “ይህ ግዴታዬ ነው . . . ጓደኞቼ እና ሌሎች ወደዛ እየሄዱ እኔ ዝም ብዬ ተቀምጬ ማየት አልችልም” ብሏል።
ዋግነር እራሱን “የግል ወታደራዊ ኩባንያ” ብሎ ይጥራ እንጂ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያለው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ሲሆን በተሰማራባቸው አገራትም በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ ይደረጋል።
ቡድኑ በዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተዋጊዎቹን ካጣ በኋላ ከሩሲያ እስር ቤት ተዋጊዎችን መልምሏል።
በሩሲያ የባለስልጣናት ወይም የባለ ጸጋ ልጆች ዋግነርን መቀላቀል የተለመደ አይደለም። በሩሲያ ሕይወት የተደላደለላቸው ከአገር በመውጣት የጦር አገልግሎትን ይሸሻሉ።
ረዥም የወጣትን ዕድሜውን በለንደን ያሳለፈው ኒኮላይ ፔስኮቭ ለሩሲያው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ አርቲ ዘጋቢ ሆኖ ሰርቷል።
ኒኮላይም ሆነ ወላጅ አባቱ በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ በአሜሪካ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።
ኒኮላይ የሩሲያ መንግሥት ደጋፊ ከሆነ ኮመሶሞለስካያ ፕራቭዳ ከተሰኘ ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ዋግነርን የመቀላቀሉ ውሳኔ የራሱ መሆኑን ተናግሯል።
ኒኮላይ ተዋጊ ቡድኑን የመቀላቀል ውሳኔው የራሱ ይሁን እንጂ ቡድኑን እንዲቀላቀል አባቱ እንደረዱት ጨምሮ ተናግሯል። “ምን ማድረግ እንደነበረብኝ አላወቅኩም ነበር። ስለዚህን አባቴን ጠይቅኩ . . . ከዛ እሱ ረዳኝ” ብሏል።
ኒኮላይ የከፍተኛ ባለስልጣን ልጅ መሆኑ እንዳይታወቅ የሐሰት መታወቂያ ይዞ ዋግነርን መቀላቀሉን ጨምሮ ተናግሯል።
ቢቢሲ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ልጅ በትክክል ዋግነርን ተቀላቅሎ በዩክሬን ስለማገልገሉ ማረጋገጥ አልቻለም።
ይሁን እንጂ ኒኮላይ ይህን ቃለ መጠይቅ የሰጠው የሩሲያ መንግሥት የወታደሮች ምልመላ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ ላይ ባለበት ወቅት ነው።
ዋግነር በዩክሬን ባክሙት ከፍተኛ ውጊያ ያደረገ ሲሆን በዛ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ተዋጊዎች ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኒኮላይ ፔስኮቭ ዋግነርን በዩክሬን ተቀላቅያለሁ ይበል እንጂ በየትኛው ውጊያ እንደተሳተፈ ያለው ነገር የለም።
የዋግነር ዋና አዛዥ ዬቨጌንይ ፕሪጎዝሂን ግን የኒኮላይን ቆይታ በተመለከተ ለሩሲያ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ኒኮላይ በሐሰተኛ መታወቂያ ተዋጊ ቡድኑን ከተቀላቀለ በኋላ ለሦስት ሳምንታት ስልጣን መውሰዱን የቡድኑ አዛዥ ተናግረዋል።
እንደ አዛዡ ከሆነ ኒኮላይ ወደ ሉሃንስክ ተጉዟል። ሮኬት ተኳሽ ቡድን አባላትንም ተቀላቅሏል። “ልክ እንደተቀሩት ጀግንነት እና ተነሳሽነት አሳይቷል” ብለዋል።
ኒኮላይ በፍላጎቴ ዋግነር ተቀላቅዬ ተዋግቻለሁ ይበል እንጂ ከ8 ወራት በፊት የሩሲያን ጦር ተቀላቅሎ የመዋጋት ፍላጎት እንዴላለው ማወቅ ተችሎ ነበር።
የፑቲን ተቃዋሚ የሆነው አሌክሲ ናቫሊን አጋር የሆነው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ኒዞቫትሴቭ፤ የሩሲያ ጦር መኮንን በመመስል ወደ ኒኮላይ ስልክ ደውሎ በቁጣ ድምጽ ለምን ወታደር ምልመላ ማዕከል እንዳልመጣ ጠይቆታል።
በሁኔታው የተደናገጠ የሚመስለው ኒኮላይ የባለስልጣን ልጅ መሆኑን በመናገር፤ “ጉዳዩን ከፍ ወዳለ ቦታ እወድሰዋለሁ” በማለት ለማስፈራራት ሞክሯል።












