የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሦስተኛ ወገን ባለበት ከመንግሥት ጋር ለመደራደር መስማማቱን አረጋገጠ

እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ከስምምነቱ መደረሱን አረጋገጠ።
ታጣቂ ቡድኑ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ያስቀመጥነውን ቅድመ ሁኔታ ተቀብሏል ብሏል።
ታጣቂ ቡድኑ ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን ባለበት በድርድሩ ወቅት በዘላቂነት ግልጸኝነት እንዲኖር ተስማምተናል ብሏል።
የታጣቂ ቡድኑ ማረጋገጫ የተሰማው ትናንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥታቸው ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር ነገ ማክሰኞ ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም. በታንዛኒያ ለመነጋገር ቀጠሮ ስለመያዛቸው መናገራቸውን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት 'ሸኔ' ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ድርድር ሊያደርግ እንደሆነ የተናገሩት ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሹን የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በተደረገ ጥረት ውስጥ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እና ግለሰቦች የእውቅና መስጠት ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ ወቅት ነው።
‘ሸኔ አትበሉኝ’
ታጣቂ ቡድኑ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ መንግሥት ድርጅቱን “ሸኔ” ብሎ ከመጥራት እንዲቆጠብ አሳስቧል።
የድርጅታችን መጠሪያ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ነው፤ ሌላ ስያሜ ስህተት ከመሆኑም በላይ ማንነታችንን እና ዓላማችንን የሚወክል አይሆንም” ካለ በኋላ መንግሥት ይህን አይነት የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨት ሊቆጠብ ይገባል ብሏል።
ሁለቱ አካላት ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት ቀጠሮ መያዛቸው፤ “ለፍትሕ፣ እኩልነት እና የራስን እድል በራስ ለመወሰን የለውጥ ምዕራፍ ጅማሮ ነው” ብሏል።
አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በምዕራባዊ እና በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ሲያካሂድ የነበረውን እንቅስቃሴ ለማቆም ለድርድር የመቀመጥ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል።
ከእነዚህም መካከል ንግግሩ ከኢትዮጵያ ውጪ በሦስተኛ ወገን አሸማጋይነት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጾ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሳወቁት ድርድሩ ታንዛኒያ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።
ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ ታጣቂ ቡድኑ ሁለቱን አካኣለት በታንዛኒያ የሚያደራድረው ሦስተኛ ወገን ማንነትን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከታጣቂው ቡድን ጋር መንግሥት ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል።

የፎቶው ባለመብት, @AbiyAhmedAli
የዕውቅና ሥነ ሥርዓት
የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲቋጭ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምሥጋና እና የዕውቅና ሥነ ሥርዓት እሁድ ሚያዝያ 15/2015 ዓ.ም. ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ የወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሐማት፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና የክልል ርዕሰነ መስተዳደሮች ተገኝተዋል።
“ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና” በሚል መሪ ሐሳብ በተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በመሆን የፌደራል መንግሥቱን እና ህወሓትን በዋናነት ያደራደሩት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ለተፈጠረው ሰላም በተለይ የሁለቱን ወገኖች አመራሮችን አመስግነዋል።
ኦባሳንጆ የማደራደር ሥራቸውን እአአ 2021 ከጀመሩ በኋላ “እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ወቅቶች ውስጥ እንኳን ሰላም እንደሚመጣ ተስፋ ነበረኝ” ብለዋል።
“ለስኬቱ መምጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሰላም የወሰዱት ጠንካራ እርምጃ ወሳኝ ነበር። . . . የህወሓት ተነሳሽነትንም ሳላነሳ አላልፍም” ብለዋል ኦባሳንጆ።
ሰላም በሁለት ወገኖች ተሳትፎ የሚመጣ ነው ያሉት ኦባሳንጆ፤ ሁለቱ አካላት የደረሱት የሰላም ስምምነትን ሙሉ በሙሉ ለማስፈጸም ቀሪ ትኩረት የስፈልጋል ብለዋል።
የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት የፖለቲካ ንግግር በፍጥነት በኢትዮጵያ መጀመር አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
“በጦርነቱ ለሞቱት አብረናችሁ እናዝናለን፤ ጦርነቱ ስላበቃ ደግሞ አብረናችሁ እንደሰታለን” ብለዋል።
ከአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተወካዮች መካከል አንዱ በመሆኑን ሁለቱን ተዋጊ ኃይሎች ሲያደራድሩ የነበሩት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር “አፍሪካ ለራሷ ችግር የራሷን መፍትሄ መስጠት ትችላለች” ብለዋል።
የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት የሰሜን ኢትዮጵያን የእርስ በርስ ጦርነት የተቋጨበት መንገድ አፍሪካ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል ማሳያ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት ደግሞ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ሚና ለተጫወቱ ግለሰቦች፣ ተቋማት እና መንግሥታት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ በአፍሪካ ኅብረት ስር በተደረገው ድርድር ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ ኡሁሩ ኬንያታ፣ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮንዚሌ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ)፣ የደቡብ አፍሪካ እና የአሜሪካ መንግሥታት ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል።
ሙሳ ፋኪ በንግግራቸው “ኢትዮጵያ የሰላም እና የጦርነት ዋጋን ትረዳለች” ካሉ በኋላ ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ መማር ይኖርባቸዋል፤ ጨምረውም “ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን መርዳት ይኖርባታል” ብለዋል።
“ይህን የምለው ወንድም አገር ሱዳናውያንን እያሰብኩ ነው። ሱዳናውያን ከእናንተ መማር ይኖርባቸዋል።”

የፎቶው ባለመብት, EBC
“ከትግራይ የመጣሁት ሰላም እና ፍቅር ብቻ ይዤ ነው”
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በንግግራቸው ጦርነትን ለማቆም ብቻ ሳይሆን፣ ሰላምን ለማጽናት እጅግ ወሳኝ የሆነው ሥነ ሥርዓት እንዲዘጋጅ በማድረጉ መንግሥትን አመስግነዋል።
አቶ ጌታቸው “ከትግራይ ይዤ የመጣሁት የሰላም እና የፍቅር መልዕክት ብቻ ነው” ካሉ በኋላ የትግራይ ሕዝብ ሰላም እንዲሰፋ እና ወደ ቀድሞ ሕይወቱ ለመመለስ እንጂ የጥይት ድምጽ የመስማት ፍጹም ፍቃደኝነት እንደሌለው ተናግረዋል።
“ደም አፋሳሽ ጦርነት አልፈናል። በርካታ 100 ሺዎችን አስከፍሎናል” ካሉ በኋላ የሰላም ስምምነቱ እንዲፈረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የወሰዷቸውን “ድፍረት የተሞሉባቸው ውሳኔዎችን ሳላደንቅ ባልፍ ንፉግነት ነው የሚሆንብኝ” ብለዋል።
“በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች አሉ። ወላጆቼን ጨምሮ። ተፈናቃዮች ወደ ቤት መመለስ አለባቸው። አራት ዓመት ከትምህር ቤት ርቀው የቆዩ ወደ ትምህር ቤት መመለስ ይፈልጋሉ። . . . ከጎረቤት አፋር እና አማራ ክልሎች ጋር ግጭት ሊኖር አይገባም” ብለዋል።
አቶ ጌታቸው በንግግራቸው፤ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በድፍረት እና በሆደ ሰፊነት እንደሚፈቱት ተስፋ አደርጋለሁ። እኛም ለዚህ ስኬት የተቻለንን ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, EBC
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የፌደራል መንግሥቱን ወክለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንም ንግግር አድርገዋል።
አቶ ደመቀ በንግግራቸው የጦርነቱን አስከፊነት ገልጸዋል። “ግጭቱ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል። ተስፋን ነጥቋል። ወጣቶች ሩቅ አላሚ ቅርብ አዳሪ ሆነዋል። ላልተበደሩት ዕዳ ከፋይ ሆነዋል” ብለዋል።
አክለውም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት “ያለ አንዳች ማመንታት መተግበር ይኖርበታል” ሲሉ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።












