የአሜሪካ ጦር ዲፕሎማቶችን እና ቤተሰቦቻቸውን ከካርቱም አስወጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ጦር አሜሪካውያን ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸውን ከሱዳን፣ ካርቱም እንዳስወጣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናገሩ።
“ዛሬ ባስተላለፍኩት ትዕዛዝ መሠረት የአሜሪካ ጦር ባካሄደው ኦፕሬሽን ከካርቱም የአሜሪካ ተወካዮች እንዲወጡ ተደርጓል” ብለዋል ባይደን።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል ስድስት አውሮፕላኖች ዜጎችን ለማስወጣት ጥቅም ላይ እንደዋሉና ከአሜሪካ ጋር እንደተባበረም ገልጿል።
የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ እና የቻይና ዲፕሎማቶች እና ዜጎች በወታደራዊ አውሮፕላኖች ከካርቱም እንዲወጡ ሊደረግ መሆኑን የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫው ማስታወቁ ይታወሳል።
ምን ያህል ሰዎች ከሱዳን እንደወጡ ገና ግልጽ አይደለም። ሆኖም ከዚህ ኦፕሬሽን በፊት የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ 70 የመንግሥት ሠራተኞችን ለማስወጣት ዕቅድ እንዳለ ዘግቧል።
ካርቱም ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ እንደተዘጋ ባይደን አረጋግጠዋል።
ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያንም አመስግነዋል።
የኤምባሲው ሠራኞችን “ብርቱ እና የሙያ ሥነ ምግባር የጠበቁ” ሲሉ ባይደን አሞግሰዋል።
በሱዳን ግጭቱ ከተነሳ ወዲህ የውጭ አገር ዜጎቹን ሲያስወጣ ይህ ሁለተኛው ነው።
ባለፈው በብዛት የባህረ ሰላጤው አገራት ዜጎች እንዲሁም የግብጽ፣ የፓኪስታን እና የካናዳ ዜጎች የሆኑ 150 ዜጎች፣ ዲፕሎማቶች እና ዓለም አቀፍ አመራሮች በባሕር ወጥተው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የወደብ ከተማ ጅዳ ተወስደዋል።
አል ሀዳት የተባለው አረብኛ ሚዲያ እንደዘገበው ስድስት የአሜሪካ አውሮፕላኖች በሱዳን አርፈዋል።
ነዋሪዎችም ትዊተር ላይ የአውሮፕላን ድምጽ እንደሰሙ ሲጽፉ ነበር። ቢቢሲ ግን ይህንን በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
የሱዳን አውሮፕላን ማረፊያ የአየር ድብደባ እንዲሁም የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደባቸው ቦታዎች አንዱ ስለሆነ ሰዎችን ለማስወጣት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ግጭቱ እንደማይቆም በመረዳት የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቡድን ለባይደን ጥቆማ ከሰጠ በኋላ ዜጎችን ለማስወጣት መወሰኑን አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ አመራር ለአሶሽየትድ ፕረስ ተናግረዋል።
“በሱዳን ያሉ አሜሪካውያንን ለማገዝ የሚያስችል መረጃ በየጊዜው እየደረሰኝ ነው። ከአገር አገሮች ጋርም በጋራ እየሠራን ነው። ይህ አሳዛኝ ግጭት ሊቆም ይገባል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
“ተዋጊዎቹ ቡድኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ ሊያቆሙ ይገባል። የሱዳንን ሕዝብ ፈቃድ ሊያከብሩና ለሰብአዊ እርዳታ መንገድ ሊከፍቱም ይገባል” ሲሉም አክለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም እንዴት ዜጎቿን እንደምታስወጣ እያቀደች እንደሆነ ተገልጿል። ዜጎች የት እንዳሉ ለኤምባሲው እንዲያሳውቁም መረጃ ተላልፏል።
ዲፕሎማቶች እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሚሠሩ ሠራተኞች እንደሚወጡ ይጠበቃል።
የዩኬ ዜጎች በአውሮፕላን ዜጎችን ለምን ማውጣት አልተቻለም ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል።
ኢማን አቡ ጋርጋ የተባለች ዜጋ እሷና ሁለት ልጆቿ ቢመዘገቡም እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳልተሰጠ ተናግራለች።
“መቼ እንደምንወጣ የምናውቀው ነገር የለም። በአውሮፕላን ነው የምንወጣው? ወይስ በየብስ? አንዳችም የሚያናግር ሰው አለመኖሩ ያበሳጫል” ብላለች።
ሌላ የዩኬ ዜጋም መንግሥት “እንደተዋት እንደሚሰማት” ለቢቢሲ ገልጻለች።
የካናዳ ኤምባሲ ዜጎቹ “ደኅንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲሆኑ” ማሳሰቢያ አውጥቷል።
ሁኔታው እጅግ አደገኛ መሆኑን ገልጾ፣ ዜጎች በሁሉም ሰዓት ስልካቸውን ቻርጅ እንዲያደርጉና ባሉበት ቦታ በርና መስኮታቸውን ዘግተው እንዲቆዩ አልያም ከአገር መውጣት አስተማማኝ መንገድ ካገኙ እንዲወጡ አሳስቧል።
ስፔን ስድስት አውሮፕላኖች ወደ ጂቡቲ መላኳን አስታውቃለች።
ግጭቱ ከተነሳ ወዲህ መብራት የተቋረጠ ሲሆን፣ ምግብ እና ውሃ ለማግኘትም አልተቻለም።
ለኢድ አል-ፍጥር ይካሄዳል የተባለውን የተኩስ አቁም ጨምሮ በተደጋጋሚ ሁለቱን ቡድኖች የተኩስ አቁም አድርገናል ቢሉም በተደጋጋሚ ተጥሷል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው ከ400 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከሆስፒታሎች መረጃ ለማግኘት አዳጋች ስለሆነ ነው እንጂ ቁጥሩ ከዚህም በላይ እንደሚሆን ይታመናል።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው በብዛት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ 20,000 ሰዎች ወደ ቻድ ተሰደዋል።












