የኢድን በዓል በጦርነት ያሳለፉት ሱዳናውያን

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሱዳን መደበኛ ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ የሚደረገው ፍልሚያ ተፋፍሞ እንደቀጠለ ነው።
በመዲናዋ ካርቱም የሚደረገው የጎዳና ላይ ውጊያዎችም ቀጥሏል።
ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የረመዳን ጾም ማብቂያ፣ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረሰውን የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ አላደረጉም።
የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ለሶስት ቀናት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተፈጻሚ እናደርጋለን ካለ ከሰዓታት በኋላም ጦሩ በተመሳሳይ ስምምነቱን እቀበላለሁ ብሎ ነበር።
ነገር ግን ጦርነቱ ተፋፍሞ በመቀጠል ከባድ የመሳሪያ ድብደባ፣ የቦምብ ጥቃትና እና የጥይት እሩምታም በሱዳን እየተሰማ ነው።
ከሳምንት በፊት በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት ቢያንስ 400 ሰዎች ተገድለዋል።
የተመድ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ሰራተኛ የሆነ ሱዳናዊም ህይወቱን አጥቷል።
ግለሰቡ ከካርቱም በስተደቡብ ምዕራብ 430 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኦል ኦቤይድ መገደሉን ተቋሙ አስታውቋል።
በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው ያሉትና በስልጣን እየተሻኮቱ ያሉት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አዛዥ ጄነራል መሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሱዳን እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ይገኛሉ።
የሱዳን ጦር የካርቱምን ጎዳናዎች ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል “ለማጽዳት” ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችንና በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ማሰማራቱን አስታውቋል።
በእስልምና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ቅዱስ ወር ተደርጋ የምትታየውን የረመዳንን ወር ጾም የምታበቃበትን ዒድ አልፈጥር በዓል በሱዳን ከዚህ ቀደም ሞቅ ደመቅ ብሎ ነበር የሚከበረው። ዘመድ አዝማድ የሚጠያየቅበት፣ ጎረቤቶች ተሰባስበው አብረው የሚበሉበት፣ ልጆች የሚቦርቁበትና በርካታ የጣፋጭ አይነቶች የምትቀርብበት ዕለት ነበር።
በትናንትናው ዒድ በዓል ግን ካርቱም የሙት ከተማ መስላ ነበር። ያ ሁሉ ፈንጠዝያና ደስታም ደብዝዞ ስጋትና ፍርሃት በነዋሪዎች ላይ ነግሷል። በካርቱም እንዲሁም በሌላኛዋ መንታ ከተማ ኦምዱርማን የሚገኙ ነዋሪዎች በቁጣ እና በድንጋጤ ውስጥ እንዳሉ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎች በመስጂድ በመሰባሰብም በጸሎትና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች እለቷን ያስቧት የነበረ ቢሆን አርብ ዕለት በካርቱም እና በአምዱርማን የሚገኙ መስጊዶች ወና ሆነው ነበር።
በመስጂድ ደጃፍ እያለቀሱ የነበሩ ሁለት ሴቶች ሁለት ልጆችን ጨምሮ በርካታ የቤተሰብ አባላትን ማጣታቸውን አስረድተዋል።
የካርቱም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሁንም እንደተዘጋ ቢሆንም የአውሮፓ ህብረት በመዲናዋ ካርቱም የሚገኙ 1 ሺህ 500 የሚሆኑ የአውሮፓ ህብረት ዜጎችን ለማስወጣ አቅጃለሁ ብሏል።
አሜሪካ፣ እንግሊዝ እና ጃፓንን ጨምሮ በርካታ የውጭ አገራት ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን ከካርቱም አላስወጡም።
አርብ እለት የአሜሪካ የጦር ሰራዊት ጀነራል ማርክ ሚሌይ ከጦር አዛዡ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር በሱዳን ስላሉት አሜሪካውያን ደህንነት ተወያይተዋል። አሜሪካ በሱዳን የሚገኘውን ኤምባሲ ሰራተኞቿንም ለማስወጣት አቅዳለች።
በርካታ ሱዳናውያን ጦርነቱን ፈርተው ቤታቸው ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። ሌሎች ደግሞ ከመዲናዋ ካርቱም እየሸሹ ወደ ሌሎች ግዛቶች ሄደዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ነገር ግን ለማሃሲን ዳሃብ እና ለቤተሰቦቿ ከከተማዋ መውጣት የሚታሰብ አይደለም።
የምትንከባከበው የአካል ጉዳተኛ የሆነ ቤተሰቧ ጋር አብሮ መጓዝ “እጅግ የማይመች” በመሆኑም ባለችበት ስፍራ ለመወሰን መገደዷንም ለቢቢሲ የኒውደይ ፕሮግራም ገልጻለች።
ያላቸው ውሃ እየተመናመነ፣በስራ ባልደረቦቿ እና የጎረቤቶቿ ሞት ሃዘን ልቧ በተሰበረበት ሁኔታም ነው ያለችው።
በስልጣን ሽኩቻው መካከል ለረጅም ጊዜ ሱዳንን የገዟትን ኦማር አልበሽርን በአውሮፓውያኑ 2019 ከስልጣን ያወረደው መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ አገሪቱን ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመመለስ ባለው ፍኖተ ካርታ ላይ ሁለቱ ጄነራሎች መስማማት አልቻሉም።
በዚህ የፍኖተ ካርታ መሰረትም ጄነራል አል ቡርሃን በበላይነትና ጄነራል ሄምቲ በምክትልነት በሚመሩት ወታደራዊ መንግሥት
ውስጥ የሚመሯቸውን መደበኛ ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ያዋህዳሉም ተብሎ ነበር።
ነገር ግን በጄነራል ሄምቲ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህንን ለውጥ በመቃወም ወታደሮቹን ማሰባሰቡን ተከትሎም ከፍተኛ ጦርነት የተቀሰቀሰው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነው።
ግጭቱንም ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢቆስሉም የህክምና ማዕከላት ከአቅማቸው በላይ ተጨናንቀው እየጎረፈ የሚመጣውን የታካሚዎች ቁጥር ማስተናገድ አልቻሉም። በግጭት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ 70 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች አገልግሎት መስጠት ማቋማቸውን የሱዳን የዶክተሮች ሰራተኛ ማህበር አስታውቋል።
ከካርቱም በተጨማሪም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የወጣባት የዳርፉር ምዕራባዊ ክልልም በጦርነቱ ክፉኛ ተጎድቷል።
“ሁኔታው አስከፊ ነው። አብዛኞቹ የቆሰሉት በጥይት የተመቱ ህጻናትና ንጹሃን ዜጎች ናቸው” በማለት በሰሜን ዳርፉር ግዛት ፋሸር ከተማ አሁንም እየሰራ ባለው ብቸኛው ሆስፒታል ውስጥ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሰራተኛ የሆኑ ግለሰብ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአብዛኛው ሴቶች እና ህጻናትን የተካተቱበት እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ሱዳናውያን ህይወታቸውን ለማትረፍ የዳርፉርን ድንበር አቋርጠው ቻድ ደርሰዋል።
ጦርነቱን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ።
በርካታ አገራት እና አለም አቀፍ ተቋማት አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስና ሁለቱን ባላንጣ ጄነራሎች ለማደራደርም ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ቀደም ሲል የተደረሱ ሁለት የተኩስ አቅም ስምምነቶች ተግባራዊ ሊሆኑ አልቻሉም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሐሙስ ዕለት ተፋላሚ ወታደራዊ መሪዎች እስከ ነገ እሁድ ድረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ተማጽነዋል።
ብሊንከን ግጭቱ ከቀጠለ በሰላማዊ ዜጎች፣ በሰብዓዊ እና ዲፕሎማቲክ ሰራተኞችም ላይ ያጠላውን አደጋ አስጠንቅቀዋል።
ጄነራል አል ቡርሃን ከቱርክ፣ ከደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ መሪዎች እንዲሁም ከብሊንከን፣ ከሳዑዲ እና ከኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጥሪ እንደደረሳቸው ጦሩ በመግለጫው አስታውቋል።
ሆኖም ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው አርብ እለት ያደረጉት ጄነራል ቡርሃን ስለ ተኩስ አቁም ስምምነት ያሉት ጉዳይ የለም።












