በሱዳን ጦርነት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 413 መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የሱዳን ጦር በካርቱም ጎዳናዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለቀናት በቀጠለው የሱዳን ጦርነት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 413 መድረሱን የመንግሥታቱ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

በሱዳን መደበኛ ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃሉ መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ለሰባተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ከሟቾቹ በተጨማሪ 3 ሺህ 551 ሰዎች መጎዳታቸውም ተገልጿል።

በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው በሱዳን እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ያሉት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ናቸው።

የሱዳን ጦር በካርቱም ጎዳናዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ማሰማራቱ ተገልጿል።

“የካርቱምን ጎዳናዎች ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ የማጽዳት ዘመቻውን እቀጥላለሁ” ማለቱንም የሳዑዲው አል አረቢያን ጨምሮ በርካታ የዜና ድረገጾች ዘግበዋል።

ጦሩ በዛሬው ዕለት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከፍተኛ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን ገልጿል። ጥቃቱም መላውን ካርቱምንም እንደሚያካትምም ማስታወቁንም አል ማሻድ አል ሱዳኒ የተባለው የሱዳን ሚዲያ ዘግቧል።

“መዲናዋን ካርቱምንም ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለማጽዳት” በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መሰማራታቸውንም የገለጸው ጦሩ አርብ ማለዳም ሰራዊቱ በከተማው ጎዳናዎች ላይ ሲዘዋወሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎችንም በትዊተር ገጹ አጋርቷል።

አህመድ ማሞን የተባለ የካርቱም ነዋሪ ወታደሮች በመዲናዋ በርካታ ጎዳናዎች ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ቪዲዮዎች እና ፎቶዎችም በትዊተር ገጹ አጋርቷል።

ከካርቱም በስተምዕራብ በምትገኘው ኦምዱርማን በከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የሱዳን ሚዲያ ዘግቧል።

ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ዛሬም በካርቱም እየተሰማ ሲሆን የሱዳን መደበኛ ጦር በዋና ከተማዋ ላይ አስከፊ ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው ሲል ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሷል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ጎረቤት አገራት የኢድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ “የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ሲል የገለጸውን ጥቃት ለመመከትም “ራስን የመከላከል እርምጃ” ለመውሰድ መገደዱን ገልጾ ነገር ግን ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ታዛዥ እንደሚሆንም ገልጿል።

የጦር ኃይሉ አዛዥ ጄነራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በጦር ኃይሉ የፌስቡክ ገጽ ላይ በተለጠፈው መልዕክታቸው ስለ ተኩስ አቁም ስምምነቱ አላነሱም።

ሱዳንን ወደ ሲቪል አገዛዝ ለመመለስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የገለጹት ጄነራሉ አል ቡርሃን ሁሉም ሰው “አንድ ሰራዊት፣ አንድ ህዝብ” ለሚለው መፈክር እንዲታዘዝ ጠይቀዋል።